Category: Articles

በአገራችን የአስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የቋንቋ፣ የህትመት እና ተያያዥ ችግሮች

በህግ አውጭው የወጣ አንድ አዋጅ ስጋና ደም ለብሶ በተጨባጭ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ብዙውን ጊዜ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎች ያስፈልጉታል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ያየን እንደሆነ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በተወካዮች ም/ቤት ከሚወጣው አዋጅ ይልቅ በየጊዜው ስለሚደነገጉት መመሪያዎች የተለየ ቅርበትና እውቀት አለው፡፡ በእያንዳንዱ አስተዳደር መ/ቤት ውስጥ የመንግስት ስራ የሚሰራው ‘በህጉ መሰረት’ ሳይሆን ‘በመመሪያው መሰረት’ ስለመሆኑ እውነትነት ያለው ሀቅ ነው፡፡

ስልጣን በሰጠው አዋጅ መሰረት እስከወጣ ድረስ በመመሪያ መስራቱ ባልከፋ ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ‘መመሪያ’ ሲባል ከስልጣን በላይ ለሆነ ድርጊት፣ ለህገ ወጥነትና ለኢ-ፍትሐዊነት የሚሰጥ የሽፋን ልብስ ነው፡፡ ዋና ችግሩ ከውክልና ሰጪው ከተወካዮች ም/ቤት ይጀምራል፡፡ በተለያዩ አዋጆች ላይ ለሚኒስትሮች ም/ቤትና ለአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና የሚተላለፈው ስልጣን እንደሰማይ የሰፋ ቢሆንም ጥያቄው የህግ የበላይነትና የህገ-መንግስታዊነት ሆኖ ተመክሮበት አያውቅም፡፡

ከዚህ ባሻገር አነስተኛ ስነ-ስርዓት ፈጽሞ አለመኖሩ መመሪያዎች ‘የስርቻው ስር ህጎች’ ሆነው እንዲቀሩ አድርጐታል፡፡ በተጨማሪም ህጋዊነታቸውንና በህግ አውጭው ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ አለማለፋቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ውጤታማ የቁጥጥር ስልት አልተዘረጋም፡፡

     መመሪያ የሌለው መመሪያ

አስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ስርዓት (Rule–Making Procedure) ግልፅነትና የህዝብ ተሳትፎን በማሳካት ረገድ ካለው ወሳኝ ሚና በተጨማሪ በዘፈቀደ በሚወጡ ደንብና መመሪያዎች አማካይነት የዜጐች መብትና ነፃነት እንዳይጣስ ከለላና ውጤታማ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡ በአገራችን በሚኒስትሮች ም/ቤትና በአስተዳደር መ/ቤቶች የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ለየትኛውም አይነት አስገዳጅ ስነ-ስርዓት አይገዙም፡፡ እስከ አሁን ድረስ ህግ አውጭው አንድ ደንብ በሚኒስትሮች ም/ቤት የሚወጣበትን ስነ-ስርዓት በአዋጅ ደንግጐ አላስቀመጠም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአስተዳደር መ/ቤቶች መመሪያ ሲያወጡ ሊከተሉት ስለሚገባ ስነ-ስርዓት የሚደነግግ አስገዳጅ ህግ የለም፡፡

ከመሰረታዊ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው አስተዳደራዊ ድንጋጌ ቀላል በሆነ መንገድ ታትሞ መሰራጨት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ በተግባር ያለው እውነታ እንደሚያሳየን መመሪያዎች በአስተዳደር መ/ቤቱ ውስጥ ተደብቀው የሚቀሩ የጓዳ ህጐች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ መመሪያዎች በ3ኛ ወገን ላይ አስገዳጅነት ቢኖራቸውም ሊታወቁና ሊከበሩ የሚችሉበት አንዳችም አማራጭ መንገድ የለም፡፡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በመመሪያው መሰረት እርምጃና ቅጣት ሲወሰድባቸው መመሪያዎቹ ባልታወቁበትና ባልታተሙበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህም የግልፅነትን መርህ የሚጥስ፣ ለሙስናና ከስልጣን በላይ ለሆነ ድርጊት እና በስልጣን አለአግባብ መገልገል በአጠቃላይ ለአስተዳደራዊ ብልሹነት የሚያጋልጥ አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ ማንም ዜጋ ላልታተመ፣ ለማያውቀው እና ሊያውቀው ለማይችል ህግ የመገዛት ግዴታ የለበትም፡፡

የመመሪያዎች አለመታተም ተፈጻሚነት (ውጤት) የሚያገኙበትን ጊዜ ለመወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ለመሆኑ አንድ መመሪያ ውጤት የሚኖረው ከመቼ ጀምሮ ነው? በተለምዶ በመ/ቤቱ ኃላፊ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ውጤት ያገኛል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ያልተፈረመ መመሪያ በተግባር ተፈጻሚ የሚደረግበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በአንዳንድ መመሪያዎች ላይ ደግሞ ተፈጻሚ የሚሆንበት ቀን በግልጽ ቢመለከትም የመ/ቤቱ ኃላፊ ፊርማ የለውም፡፡

በስነ-ስርዓት አለመኖር ምክንያት በየአስተዳደር መ/ቤቱ የሚወጡት መመሪያዎች ቅርጽና ይዘት ወጥነት አጥቷል፡፡ መመሪያ ለአውጭውም አካል ሳይቀር አስገዳጅ ህግ እንደመሆኑ አነስተኛ የሚባሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የመመሪያው መለያ ቁጥር፣ የተሻረ መመሪያ ካለ ቁጥሩና የወጣበት ጊዜ አንዲሁም ስልጣን የሰጠውን አዋጅ ቁጥርና አንቀጽ መጥቀስ ይገባል፡፡ እንዲሁም መመሪያው በምእራፍ፣ በክፍልና በአንቀጽ (ቁጥር) ተከፋፍሎ አስገዳጅነት ያለው ድንጋጌ ሊያስቀምጥ ይገባል፡፡ ይዘቱ ጥናት፣ ጥቆማ ወይም ምክር ወዘተ… መምሰል የለበትም፡፡

ህትመትና የሰበር ችሎት አቋም

መመሪያዎች በይፋ አለመታተማቸው በፍትሐብሔር እና የወንጀል ክርክሮች የሚረጋገጡበትን መንገድ ያወሳስበዋል፡፡ አውጭው አካል በተከራካሪነት ሲሰለፍ መመሪያ ጠቅሶ የሚያቀርበው ክርክር መመሪያውን እንደ አንድ የማስረጃ ዓይነት ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ከእርሱ በስተቀር ፍርድ ቤቱ ሆነ ባለጋራው ተከራካሪ ስለመኖሩ ሊያውቁ አይችሉም፡፡ ስራ ላይ መዋሉ ሊታወቅና ሊረጋገጥ የሚችለው የተባለውን መመሪያ እንዳወጣ የሚከራከረው የመንግስት ተቋም እንደ ሰነድ ማስረጃ ከመዝገቡ ጋር ማያያዝ ሲችል ነው፡፡

አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጠረው መመሪያውን ያወጣው አካል ተሳታፊ በማይሆንባቸው ክርክሮች ይዘቱ በአንደኛው ወገን መከራከሪያ ሆኖ ሲቀርብ ነው፡፡ ለምሳሌ ይህ ተከራካሪ ትክክለኛውን የመመሪያ ቁጥር መለየት ሳይችል ሲቀርና መኖሩ በተቃራኒ ወገን ሲካድ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው አቅጣጫ ምንድነው? በመመሪያው መኖር ተጠቃሚነቱን ገልጾ የሚከራከረው ወገን የማስረዳት ግዴታውን ስላልተወጣ ክርክሩን ውድቅ ማድረግ አንደኛው አማራጭ ነው፡፡ ሆኖም ይህ አካሄድ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል፡፡ መሰረታዊ የማስረጃ ህግ ደንቦችንም አያሟላም፡፡ አንድ ተከራካሪ አስገዳጅነት ያለውን የህግ ድንጋጌ ጠቅሶ ከመከራከር ባለፈ ‘ህግ እንደማስረጃ’ እንዲያቀርብ አይገደድም፡፡

‘መመሪያ ህግ ነው’ እስከተባለ ድረስ ካለበት ቦታ ማስቀረብ ዞሮ ዞሮ ፍርድ ቤቱ ጫንቃ ላይ ያርፋል፡፡ ሆኖም ያልታተመ መመሪያ ፍርድ ቤቶች ግንዛቤ እንዲወስዱበት አይገደዱም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ. 40804[1] በሰጠው የህግ ትርጉም፤

…በመንግስት የሚወጡ ሕጏች እና መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ወዘተ በግልጽ የሚታወቁ እንደመሆናቸው ፍ/ቤቶች (ዳኞች) ግንዛቤ የሚወስዱባቸው ናቸው፡፡

ችሎቱ ያንጸባረቀው አቋም ዳኞች ያልተጻፈ እንዲያነቡ የማስገደድ ያክል ነው፡፡ እንደ ችሎቱ ከሆነ መመሪያ-ጠቀስ ክርክር በተከራካሪ ወገኖች ባይቀርብም ለውሳኔ አሰጣጥ የሚረዳ መመሪያ ካለ ፍርድ ቤቱ መኖሩን ማወቅ አለበት (በይግባኝ ደረጃ ደግሞ ማወቅ ነበረበት) ማለት ነው፡፡

የነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ዳኞች ያልታተሙ መመሪያዎችን ግንዛቤ እንዲወስዱባቸው አያስገድድም፡፡ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/3/ ህግ ተርጓሚውን ጨምሮ ማናቸውም የፌደራልና የክልል የመንግስት አካላት እንዲሁም ህጋዊ ሰውነት ያገኘ ማንኛውም ድርጅት በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጣን ህግ የመቀበል ግዴታ (shall take judicial notice of Laws published in the Federal Negarit Gazeta) አለበት፡፡ ስለሆነም ችሎቱ በሰ/መ/ቁ. 40804 ያንጸባረቀው አቋም ከነጋሪት ጋዜጣ ህጉ ጋር አይስማማም፡፡

ችሎቱ በከፊል የተለሳለሰ አቋም የያዘው በሰ/መ/ቁ. 83060[2] ሲሆን በመዝገቡ በሰፈረው የህግ ትርጉም መሰረት ክርክር የቀረበበት መመሪያ ይዘት ለውሳኔ አሰጣጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፍርድ ቤት በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 145(1) እና 345(1)(ለ) ማስቀረብ ይገባዋል፡፡ ይህም ማለት አንደኛው ተከራካሪ መመሪያ ጠቅሶ ካልተከራከረ ወይም የመዝገቡ አካል እንዲሆን ካላሳሰበ በስተቀር የማስቀረብ ግዴታ አይኖርም፡፡ ፍርድ ቤትም በዚህ መልኩ ያልተነሳን ወይም በክርክሩ ያልተጠቀሰን መመሪያ በውሳኔው ከግምት ውስጥ ባለማስገባቱ ብቻ ውሳኔው በህግ ስህተት በይግባኝ ወይም በሰበር ሊሻር አይገባውም፡፡

የነጋሪት ጋዜጣ የህትመት ቅድመ ሁኔታ

ለመመሪያዎች አለመታተም ዋናው ምክንያት ልማድ እንጂ ህግ አይደለም፡፡ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ማናቸውም የፌደራል መንግስት ህግ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣ ያስገድዳል፡፡[3] አዋጁ መታተም ያለባቸውን የፌደራል መንግስት ህጎች በትርጓሜ አሊያም በዝርዝር አልለየም፡፡ ‘መመሪያ’ ከአዋጅና ደንብ ቀጥሎ አስገዳጅ ውጤት ያለው አንደኛው የፌደራል መንግስት ህግ እንደሆነ ክርክር አያስነሳም፡፡ ስለሆነም መመሪያዎች አለመታተማቸው የቆየ ልማድ እንጂ ህጉ በልዩ ሁኔታ ከህትመት ነጻ ስላደረጋቸው አይደለም፡፡

የአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና በተሰጣቸው ስልጣን የሚያወጡት አስተዳደራዊ ድንጋጌ በልዩ ሁኔታ ከህትመት ነጻ ባለመደረጉ የማሳተም ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ግዴታቸውን ካልተወጡ መመሪያዎቻቸው ውጤት ኖሯቸው ሊጸኑም አይገባም፡፡ ያልታተመ አዋጅና ደንብ ረቂቅ ሆኖ እንደሚቀር ሁሉ የመመሪያ ዕጣ ፈንታም ከዚህ አይለይም፡፡

የቋንቋ ጉዳይ

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መመሪያዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ የተጻፉት በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነው፡፡ ባለስልጣኑ እንግሊዝኛውን ሲያስቀር ቋንቋውን አንብበው የማይረዱ በርካታ የውጭ አገር ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ዘንግቶታል ለማለት ይከብዳል፤ ችላ ብሎታል እንጂ፡፡ የዚህ የቆየ ልማድ ተገላቢጦሹን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እናገኛለን፡፡ ባንኩ በመመሪያ አወጣጥ ሂደት አማርኛ አይጠቀመም፤ እንግሊዝኛ ብቻ እንጂ፡፡ ይህ የልማድ አሰራር በግልና በመንግስት ባንኮች የህግ አተገባበር መሰረታዊ ችግር ላይፈጥር ይችላል፡፡ ሆኖም በህግ ተርጓሚው ላይ የሚፈጥረው ችግር ቀላል ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ እንግሊዝኛ የማወቅ ያለማወቅ አይደለም ቁምነገሩ፡፡

በእንግሊዝኛ ተረቆ የተዘጋጀ ህግ በአማርኛ ወይም በሌላ የክልል ቋንቋ ሲተገበር ውስብስብ ችግር ያስከትላል፡፡[4] በአንደኛው የሚገኝ ቃል በሌላኛው አይኖርም፡፡ አንደኛው በአግባቡ የገለጸውን ሀሳብ አንዳንዴ ሌላኛው ያዛባዋል፡፡ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ እንዲታተም ያስገድዳል፡፡ በመካከላቸው የሚፈጠረውን የይዘት ልዩነት ለማስታረቅ አማርኛውን ብቻ ገዢ አድርጎ መጠቀም ውጤታማ አማራጭ ባይሆንም የአማርኛው የበላይነት ህጋዊ ዕውቅና አግኝቷል፡፡[5]

ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በነጋሪት ጋዜጣ መታተም ያለባቸው ሁሉም የፌደራል መንግስት ህጎች ናቸው፡፡ ሆኖም በተግባር ሲታይ መመሪያዎች ለብቻቸው አፈንግጠው አይታተሙም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚዘጋጁበት መንገድ በውክልና ስልጣን የሰጣቸው ህግ የያዘውን መልክና ቅርጽ ሊያንጸባርቁ ይገባል፡፡ የህግ አውጭነት ስልጣናቸው ምንጭ የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ የሚጻፈው በአማርኛና በእንግሊዝኛ እስከሆነ ድረስ መመሪያዎችም ይህንኑ ተከትለው በሁለቱም ቋንቋዎች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በአንደኛው ቋንቋ ብቻ የተዘጋጀ መመሪያ አስገዳጅ ውጤት ሊኖረው አይገባም፡፡

የአስተዳደር መ/ቤቶች እየተከተሉት ያለው ዝብርቅርቅ የቋንቋ አጠቃቀም ከሚያስነሳው የህግ ጥያቄ በተጨማሪ ወደ አገራችን የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎችና ባለሀብቶች የአገሪቱን ህግ አክብረው ለመንቀሳቀስና ለመስራት የሚያደርጉትን ጥረት ከማገዝ ይልቅ ተጨማሪ ጫና ይፈጥርባቸዋል፡፡ ሆኖም የቋንቋ ጉዳይ ለሰበር ችሎት ብዙም አሳሳቢ ሆኖ አለመገኘቱ ሲታይ የተለመደው አሰራር ከህግ አውጭው አዋጅ በስተቀር የዳኝነት አካሉ ፍርድ መቼም የሚያስተካክለው አይመስልም፡፡

በሰ/መ/ቁ. 43781[6] ብሔራዊ ባንክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ያዘጋጀው መመሪያ በአማርኛ ተተርጉሞ ባለመገኘቱ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውጤት ቢነፈገውም የሰበር ችሎት፤

በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚወጡት የበታች ሕጎች… በተወሰነ ቋንቋዎች እንዲጻፉ የሚያስገድድ ሕግ የለንም፡፡

በሚል ምክንያት የመመሪያውን አስገዳጅነት ተቀብሎታል፡፡ ችሎቱ ‘ህግ የለም’ ይበል እንጂ ህጉስ አለ፡፡ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 መመሪያዎች እንዲታተሙ ከዚያም አልፎ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንዲዘጋጁ ያስገድዳል፡፡ የአዋጁ ተፈጻሚነት በፌደራል መንግስቱ ህጎች ላይ እንጂ በተወካዮች ም/ቤት አዋጅ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ችሎቱ ‘መመሪያ በፌደራል መንግስት ህጎች ውስጥ አይጠቃለልም’ የሚል አቋም ከያዘ በመዝገቡ ላይ ‘መመሪያ ተላልፏል’ በሚል የወንጀል ክስ ቀርቦበት በይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ነጻ የተደረገውን ተጠሪ በወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ ሊለው ባልተገባ ነበር፡፡

[1] አመልካች ዳንዲቦሩ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ እና ተጠሪ እነ ተክሉ ኡርጋ ኢደኤ /2 ሰዎች/ ጥር 26 ቀን 2001 ዓ.ም. ቅጽ 8

[2] አመልካች ገ/ማሪም ገ/መድህን እና ተጠሪ ጣዕመ ወ/ስላሴ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅጽ 15

[3] የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/2/

[4] የችግሮቹን መልክና ገፅታ በተለይ የተጠናቀሩት (Codified) ህጎቻችን በፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ መረቀቃቸው ያስከትሉትን ችግር ለመረዳት Roger Briottet “French, English, Amharic: The Law in Ethiopia.” Mizan Law Review 3 (2): 331-340 (2009) ይመለከቷል፡፡

[5] አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/4/ ይመለከቷል፡፡

[6] አመልካች የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እና ተጠሪ አቶ ዳንኤል መኮንን ሐምሌ 14 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 10

‘ሁከት ይወገድልኝ’ – የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

የአንድ ንብረት ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን ለመንጠቅ ወይም በይዞታው ላይ ሁከት ለመፍጠር የሚፈፀምን ማንኛውንም ድርጊት እንዲቆም ወይም ንብረቱ እንዲመለስለት የሚያቀርበው የይዞታ ክስ

በፍ/ሕ/ቁ. 1149/1/ መሰረት የሁከት ይወገድልኝ ክስ መቅረብ የሚችለው አቤቱታ አቅራቢው ለክርክሩ መነሻ በሆነው ነገር በቀጥታ ወይም በጠባቂ ይዞታ ሲኖረው ነው፡፡ እንዲሁም የይዞታ ክስ የሚቀርበው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ንብረት በወቅቱ ለመያዝ ምንም ዓይነት መብት በሌለው ሰው ላይ ስለመሆኑም የድንጋጌው መንፈስ ያስረዳል፡፡ የሁከት ይወገድልኝ አቤቱታ አቅራቢ በማስረጃ ማረጋገጥ ያለበት ንብረቱ በይዞታው ስር የነበረና የሁከት ድርጊት ፈፃሚው የኃይል ተግባር በመጠቀም ወይም በሚስጢር ንብረቱን የወሰደበት መሆኑን ነው፡፡ ሁከት ተፈጥሯል የሚባለው ባለይዞታ የሆነው ሰው በይዞታው ስር በሚገኘው ንብረት እንዳይገለገልበት ሌላ ሰው ጣልቃ ገብቶበት መሰናክል ሲፈጥርበት ወይም ረብሻ ሲፈጥርበት ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 80241 ቅጽ 15፣[1] ፍ/ህ/ቁ. 1149(1)

የሁከት ይወገድልኝ ክስ ለማቅረብ ከሳሹ ማስረዳት ያለበት ባለቤትነት ወይም የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዳለው ሳይሆን ክስ ያቀረበበት ንብረት ህጋዊ ባለይዞታ መሆኑ በሌላ አነጋገር ሁከት የተፈጠረበትን ነገር በእጁ አድርጎ በእውነት ሲያዝበት እንደነበር ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 38228 ቅጽ 9[2]

ሁከት እንዲወገድ በቀረበ ክስ ተከሳሽ የሚያነሳው የባለቤትነት ክርክር እራሱን የቻለ ባለቤትነት የመፋለም ክስ /petitory action/ በሚመለከተው ላይ አቅርቦ ከሚታይ በስተቀር ሁከት ተፈጥሯል ወይስ አልተፈጠረም ተብሎ ለሚያዘው ጭብጥ ተገቢነት የለውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 27506 ቅጽ 6[3]

የሁከት ይወገድልኝ ክስ ሲቀርብ በፍርድ ቤት በጭብጥነት ተይዞ መፈታት የሚገባው ጉዳይ ሁከት አለ ወይንስ የለም? የሚለው ነው፡፡

የውሉ ተገቢውን የአጻጻፍ ሥርዓት ተከትሎ አለመደረግ ይዞታው በተጨበረበረ መንገድ ስለመያዙ ወይንም በማናቸውም ሕገወጥ ሁኔታ ስለመያዙና ሁከት እንዲወገድለት ክስ ያቀረበው ከሳሽ በይዞታው በእውነት ሊያዝበት እንደማይችል አያረጋግጥም፡፡ በዚህ ረገድ ውሉ ጉድለት አለበት ከተባለ በፍ/ብ/ሕ/ቁ/1808(2) ላይ እንደተመለከተው ውሉ ፈራሽ ነው እንዲባል የክስ ምክንያት ከሚሆን በስተቀር ሁከት ይወገድልኝ ተብሎ በቀረበ ክስ ላይ ሊስተናገድ የሚችል አይሆንም፡፡

ሰ/መ/ቁ 36645 ቅጽ 9[4]

በአብላጭ ድምፅ የተሰጠ

[1] አመልካች ጽናት የሆቴል ቱሪዝም ስራዎች ኃ.የተ. የግል ማህበር እና ተጠሪ አቶ ዳመነ ነጋ /5 ሰዎች/ የካቲት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

[2] አመልካች ሐጂ መሀመድ አወል ረጃ እና ተጠሪ እነ አቶ ዲኖ በሺር /2 ሰዎች/ ታህሣሥ 7 ቀን 2001 ዓ.ም.

[3] አመልካች እነ ሣሙኤል ውብሸት እና ተጠሪ ብዙነህ በላይነህ ሐምሌ 19 ቀን 1999 ዓ.ም.

[4] አመልካች ረዳት ሳጂን አያኖ አንጀል እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ ዓሇሚቱ ህዳር 11 ቀን 2001 ዓ.ም.

Selected Cassation decisions on Women

The Federal Supreme Court, in co-operation with Network of Ethiopian Women’s Association (NEWA) has published selected Cassation decisions related to women’s rights and women litigants.

Click the link below to download the publication.

cassation on women

በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮች

በፍርድ የማይዳኙ ጉዳዮችን (justiciability) በተመለከተ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ያለው አረዳድ የፅንሰ ሀሳቡን ትክክለኛ ይዘት አያንጸባርቅም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 51790 ቅጽ 12[1] በሰፈረው የሚከተለው ማብራሪያ መሰረት በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ከፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ውጪ የሆነ ጉዳይ ማለት ነው፡፡

ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ. ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37/1/ ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳየው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚሁ የሕገ መንግስት ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻለው ደግሞ ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ (አቤቱታ) ተቀብለው ውሳኔ መስጠት የሚችለት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለሌላ አካል ያልተሰጠ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ መሆኑን ነው፡፡ በሕግ ተለይተው በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲቋጩ በተባሉ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ፍርድ ቤት የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን ስለሌለው በሕጉ መሰረት ለአንድ አስተዳደር አካል ቀርቦ አስተዳደራዊ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ወይም ለአስተዳደር መቅረብ የሚገባውን ጉዳይ ፍርድ ቤት ሊያስተናግደውም ሆነ አከራክሮ ውሳኔ ሊሰጥበት አይችልም፡፡

ይኸው አቋም ጉዳዩ በፍርድ እንደሚዳኝ ድምዳሜ ላይ በተደረሰባቸው ውሳኔዎች ላይም ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ. 80202 ቅጽ 15[2] በተሰጠ የህግ ትርጉም መሰረት ግንባታ በጊዜው አለመጠናቀቁን ወይም የገንዘብ አቅም ማነስን አሊያም በሌላ ምክንያት አስተዳደሩ በሚወስዳቸው የኪራይ (lease) ይዞታ ማቋረጥ እርምጃዎች ላይ ባለይዞታው ቅሬታ ሲያድርበት ጉዳዩን ለማየት በሕግ በግልጽ የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ሌላ አካል እስከሌለ ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን ይገባዋል፡፡

በእርግጥ በአረዳድ ረገድ የሚታየው ብዥታ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በአውስትራሊያ የአስተዳደር ህግ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ በሚከተሉት ሀሳቦች ዙሪያ ይዋልላል፡፡

  • ጉዳዩ ከፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ውጪ ነው፡፡
  • ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን ክልል ውስጥ ቢወድቅም ሕዝባዊ የስልጣን መገልገልን አይመለከትም፡፡
  • ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስልጣን አለው ነገር፡፡ ግን ጉዳዩን ለመፍታት ተቋማዊ ብቃት የለውም፡፡
  • ፍርድ ቤቱ ስልጣንም ብቃትም አለው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን በዳኝነት ለመጨረስ ህገ መንግስታዊ ተገቢነት የለውም፡፡
  • ጉዳዩ ገና ያልበሰለ ነው፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤት ጣልቃ አይገባበትም፡፡
  • ፍርድ ቤቱ ህጋዊነትን ከማጣራት አልፎ የጉዳዩን ይዘት (merit) ሳይፈትሽ በአጣሪ ዳኝነት ሊመረምር የሚችልበት በቂ ምክንያት (grounds of judicial review) የለም፡፡
  • ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመወሰን የሚያስችል ቅቡልነት ያለው ማስረጃ ማግኘት ወይም ማስቀረብ አልቻለም፡፡[3]

ከዝርዝሮቹ መካከል በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ በሚገባ የተገለጸው በ3ኛ እና 4ኛ ላይ ነው፡፡ የዳኝነት ስልጣን ጉዳዩን ለመዳኘት ካለመቻል የሚመነጭ ባህርይ ሳይሆን በፍርድ ቤቶች ስልጣን ላይ በህግ የተቀመጠ ገደብ ነው፡፡ አንድን ጉዳይ እንዲያይ ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ወይም የይግባኝ ስልጣኑ ለሌላ አካል ከተሰጠ የስረ-ነገር የዳኝነት ስልጣን ያጣል፡፡ በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ በከፊል ስልጣን አግኝቶ ከሆነም በፍሬ ነገር ረገድ የሚደርስበት ድምዳሜ የስልጣኑን ልክ ያልፋል፡፡ ወጣም ወረደ ግን የዳኝነት ስልጣን አለመኖር ራሱን ችሎ የቆመ ሀሳብ በመሆኑ ከጉዳዩ ለመዳኘት አለመቻል ጋር ሊቀላቀል አይገባውም፡፡

በዝርዝሩ 2ኛ ላይ የተጠቀሰው ‘ህዝባዊ ስልጣን’ ጉዳዩ የአስተዳደር ህግ ጥያቁ እንደማያስነሳ ያመለክታል፡፡ ሁለት የተለያየ የአስተዳር ህግ እና የፍትሐ ብሔር ስርዓት ላለቸው አገራት ይህ ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይ መነሻው መንግስት እንደ ግለሰብ ያሉትን መብቶች ተጠቅሞ የፈጸመው ድርጊት ከሆነ በአጣሪ ዳኝነት አይስተናገድም፡፡ ከውል ውጪ ኃላፊነት ወይም ከውል በሚመነጭ ግዴታ መንግስት ተጠያቂነት ካለበት ጉዳዩ ከመነሻው የአጣሪ ዳኝነት ጥያቄ አያስነሳም፡፡

የጉዳዩ አለመብሰል እና የይዘት ጥያቄ የአስተዳደር ህግ ወሰንን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች አስተዳደሩ ገና ውሳኔ ላይ ያልደሰበትን ጉዳይ የማያዩት ህጋዊነቱን የሚመዝኑበት በቂ ምክንያት ስለማያገኙ ነው፡፡ የውሳኔው ይዘት ማለትም ትክክለኛነቱ እንዲሁ ከህግ አንጻር የሚጣራበት መሰረት የለም፡፡ በመጨረሻም ማስረጃ ሊገኝ አለመቻሉ ወይም እንዲቀርብ የታዘዘው ማስረጃ ሚስጥራዊ ተብሎ በመፈረጁ የተነሳ ፍርድ ቤቱ እልባት ለመስጠት አለመቻሉ ጉዳዩ ከመነሻው በፍርድ እንደማይዳኝ አያመለከትም፡፡

በዝርዝሮቹ 3ኛ እና 4ኛ ላይ የሰፈረውን ሀሳብ በከፊል በሚያቅፍ መልኩ በፍርድ የማይዳኝ ጉዳይ ማለት ምን እንደሆነ ትክክለኛ ትርጓሜ የተሰጠው በሰ/መ/ቁ. 42150 ቅጽ 12[4] ከአብላጫው ድምጽ በተለየው ሀሳብ ላይ ነው፡፡ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው የሚባለው የክርክሩ መሠረታዊ ባህሪ በፍርድ ለመጨረስ አመች የሆነ ሲሆንና ተከራካሪዎቹ የሚከራከሩበት ጉዳይ ንድፈ ሃሳባዊ ወይም ምናባዊ የፈጠራ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሣይሆን በነባራዊ ዕውነታና ተጨባጭ በሆነ ችግር ወይም ክስተት መሠረት ያደረገ የመብት ወይም የሃላፊነት ጥያቄ ሲሆን እንደሆነ ነው፡፡

በአብላጫው ድምጽ ላይ ግን ፅንሰ ሀሳቡ ከክስ ምክንያት ጋር ተምታቷል፡፡ በአብላጫው አስተያየት አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ነው ሊባል የሚችለው፤

…የክርክሩ መሠረት በሕግ ጥበቃ ያገኘ መብት ወይም ግዴታ ሲሆን ወይም ለመብቱ ወይም ግዴታው መሠረት የሚሆን ውል መኖሩ ሲረጋገጥ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ‘ያለመዳኘት’ ከጉዳዩ ባህርይ እንጂ ከተከራካሪ ወገኖች መብት አይመነጭም፡፡ ከባህርያቱ አንጻር ሲቃኝ አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊዳኝ አይችልም የሚባለው አንድም ከፍርድ ቤቱ ተቋማዊ ብቃት አንጻር በፍርድ ለማለቅ አመቺ ባለመሆኑ አሊያም ከህግ መንግስታዊው የስልጣን ክፍፍል አንጻር ዳኝነት መስጠት ተገቢ ስለማይሆን ነው፡፡

ከተቋማዊ ብቃት አንጻር አንዳንድ ጉዳዮች የብዙ ወገኖች ተጻራሪና ተነጻጻሪ ጥቅም ያዘሉ (polycentric) በመሆናቸው በባህርያቸው በፍርድ ቤት ሙግት ለማለቅ አያመቹም ወይም አይመቹም፡፡ እንደ ፒተር ኬን ገለጻ፤

A polycentric issue is one which involves a large number of interlocking and interacting interests and considerations.[5]

የፍርድ ቤት የሙግት ስርዓት ተጻራሪ የጥቅም ግጭት ያለባቸውን ጉዳዮች በወጉ ለመፍታት አያመችም፡፡ ፍርድ ቤቶች የሚከተሉት ጥብቅ የሙግት ስነ ስርዓት ብሎም የሚመደብላቸው ውስን የገንዘብና የሰው ኃይል ቴክኒካልና ሳይንሳዊ መረጃና ማስረጃ ለማሰባሰብ ሆነ ተጻራሪ ጥቅሞችን በማቻቻል ዘላቂ መፍትሔ ለመቀየስ አያስችልም፡፡ በአጭር አነጋገር እነዚህን ጉዳዮች ለመዳኘት ተቋማዊ ብቃታቸው አይፈቅድላቸውም፡፡

በፍርድ ለመዳኘት ህገ መንግታዊ ተገቢነት የሌላቸው ጉዳዮች በፈራጆች ውሳኔ ሳይሆን በተመራጮችና ፖለቲከኞች ጥበብና ብልሀት ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጣቸው የፖሊሲ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዳኞች ተሿሚዎች እንጂ ተመራጮች አይደሉም፡፡ ለመራጩ ህዝብም ቀጥተኛ ተጠያቂነት የለባቸውም፡፡ ስለሆነም አገራዊ ፋይዳ ባላቸው የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ ዳኝነት ለመስጠት የሚያስችል ህገ መንግስታዊ ስልጣን የላቸውም፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ፣ መከላከያ እንዲሁም የብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ዳኝነት መስጠት ከፍርድ ቤቶች ህገ መንግስታዊ ሚና አንጻር ተገቢነት የለውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት መዋዋል፣ የሚኒስትሮች ሹመትና ሽረት፣ ፓርላማ የመበተን ስልጣን፣ ለህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረግ፣ መንግስት በአንድ አካባቢ መሰረት ልማት ለመዘርጋት የሚደርስበት ውሳኔ በአጠቃላይ የመንግስት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ውሳኔ ፖለቲካዊ ተገቢነት መዝኖ ፍርድ ማሳረፍ የዳኝነት አካሉ ሚና አይደለም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዳኝነት ማየት የስልጣን ክፍፍል መርህን ይጥሳል፡፡

በውሳኔ ሰጪው ፈቃደ ስልጣን የሚወሰኑ ጉዳዮች እንዲሁ በፍርድ ለማለቅ አመቺ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የስራ ፈቃድ ወይም የግንባታ ቦታ ጥያቄዎች ተገቢነት በፍርድ ቤት ጭብጥ ተይዞበት የሚወሰን አይደለም፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችና ሁኔታዎች አንድ ጉዳይ በፍርድ የማይዳኘው የክሱ ምክንያት በይዘቱ ዳኝነት ለመስጠት አመቺ ሳይሆን እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ተገቢነት ሳይኖረው ሲቀር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለክርክሩ መነሻ የሆነው አስተዳደራዊ ውሳኔ ወይም ድርጊት ‘የጀርባ ምክንያት’ ፖለቲካዊ ነክ መሆኑ ፍርድ ቤቶች አከራክረው ውሳኔ ከመስጠት አያግዳቸውም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 48217[6] አመልካች በህጋዊ መንገድ ተመርተው የሰሩት ቤት በ1ኛ ተጠሪ ተነጥቀው ለ2ኛ ተጠሪ እንደተሰጠባቸው በመግለጽ እንዲመለስላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የቤቱ አሰጣጥ መነሻ አመልካች በጦርነት ምክንያት ቤትና ንብረት ስለወደመባቸው ለተፈናቃዮች ምትክ ቦታና ገንዘብ እንዲሰጥ መንግስት ባስተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ አመልካች በዚሁ መሰረት የራሳቸውን ገንዘብ ጨምረው ቤቱን ሰርተው ከጨረሱ በኋላ ‘ኤርትራዊ ነሽ’ በሚል ምክንያት 1ኛ ተጠሪ ቤታቸውን ነጥቆ ለ2ኛ ተጠሪ ሰጥቷል፡፡ ክሱ በቀረበበት ፍርድ ቤት 1ኛ ተጠሪ የቤቱ አሰጣጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዳይዳኝ የመጀሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያነሳ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሆኖም ክርክሩን በይግባኝና በሰበር ያዩት ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ በአስተዳደር እንጂ በፍርድ እንደማያልቅ አቋም በመያዛቸው የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸሯል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት በበኩሉ በድርጊቱ ይዘት ላይ በማተኮር የአመልካች የክስ ‘አለአግባብ ቤቴን ተነጠቅኩኝ’ በሚል የቀረበ እንደሆነ በመጠቆም ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ እንደሚችል ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

የአገራችን ፍርድ ቤቶች በፍርድ አይዳኙም በሚል በራቸውን የሚዘጉባቸው ጉዳዮች አብዛኞቹ የተቋማዊ ብቃት ሆነ የፖሊሲ ጥያቄ አያስነሱም፡፡ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞባቸው በሰበር ችሎት ከታረሙ አንዳንድ ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በግለሰብና በመንግስት መካከል የሚነሱ አስተዳደራዊ ክርክሮችን ‘በፍርድ የማይዳኙት’ ውስጥ የመፈረጅ አዝማሚያ በፍርድ ቤቶቻችን ዘንድ ሰፍኖ ይታያል፡፡

በሰ/መ/ቁ. 75414 ቅጽ 14[7] የባለቤትነት ምስክር ወረቀት እንዲሰረዝ የቀረበ አቤቱታ ‘በፍርድ አይዳኝም’ በሚል በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ የተደረገ ቢሆንም የሰበር ችሎት የሚከተለውን ሐተታ በማስፈር ሽሮታል፡፡

የንብረት ባለሀብትነት መብት ከአንዱ ወገን ወደ ሌላው እንዴት መተላለፍ እንዳለበት በህጉ የተመለከተውን ደንብና ሥርዓት ሳይከተል ስለሆነ የንብረቱ ባለሀብት ስለመሆኑ የህግ ግምት መውሰጃ የሆነው የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ቀሪ ነው፤ ሊሰረዝ ይገባል በማለት የሚቀርብ ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195፣ 1196 እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ እና 231/1/ሀ/ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት በፍ/ቤት ሊረጋገጥ የሚችል የዳኝነት ጥያቄ እንጂ ጉዳዩ በፍርድ ሊያልቅ የሚችል ጉዳይ አይደለም ለማለት የሚያበቃ አይደለም፡፡

በሰ/መ/ቁ. 97948 ቅጽ 17[8] የቀበሌ ቤት የተከራይነት መብት ተከራይ ሲሞት ለወራሾቹ ወይም ለቤተሰቦቹ የሚተላለፍ መሆን ያለመሆኑ በፍ/ብ/ሕጉ ስለማይንቀሳቀስ ንብረት የኪራይ ውል የተመለከቱትን ድንጋጌዎች፣ የቀበሌ ቤትን የኪራይ መብትና ግዴታ ለመግዛት በሚመለከተው አካል በወጡት ደንብና መመሪያዎች አንጻር ታይቶ በፍርድ ቤት ዳኝነት የሚሰጥበት እንጂ የቤቱ አስተዳዳሪ የሆነ ቀበሌ ለፈለገው ሰው የሚያከራየው ነው ተብሎ በፍርድ እንዳያልቅ የሚደረግ ጉዳይ እንዳልሆነ የህግ ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፡

[1] አመልካች እነ ወልዲይ ዘሩ (61 ሰዎች) ተጠሪ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ግንቦት 16 ቀን 2003 ዓ.ም. በተጨማሪ አመልካች እነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ባለስልጣን /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ ድንቅ ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሰ/መ/ቁ. 54697 ቅጽ 12 መስከረም 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ይመለከቷል፡፡

[2] አመልካች እነ አቶ ሐጎስ ሽጎዕ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ የመሸነ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የካቲት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

[3] Chris Finn, “The concept of ‘justiciability’ in administrative law.” In Australian administrative law: Fundamentals, principles and doctrines, Matthew Groves and H. P. Lee (eds.) (Cambridge University Press, 2007) ገፅ 143-145

[4] አመልካች የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እና ተጠሪዎች እነ አቶ ዳንኤሌ ካሣ /ሃያ ሁለት ሰዎች/ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም.

[5] Peter Cane, Administrative Law, (5th edn፡ Oxford University Press, 2011) ገፅ 274

[6] አመልካች ወ/ሮ አባዲት ለምለም እና ተጠሪ እነ የዛላንበሳ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት /2 ሰዎች/ ጥቅምት 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 11

[7] አመልካች ወ/ሪት ሄለን ተክሌ እና ተጠሪ ወ/ሮ ዘይድ አብርሃ ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም.

[8] አመልካች ወ/ሮ ዋሪቴ ሱቡሳ እና ተጠሪ እነ የጎልጆታ ከተማ አስተዳደር /2 ሰዎች/ ጥቅምት 22 ቀን 2005 ዓ.ም.

የእምነት ቃል —የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

በወንጀል ተጠርጣሪ ግለሰብ በምርመራ ሂደት ወይም ደግሞ ተከሳሽ በክሱ ሂደት የራሱን አጥፊነት በመቀበል የሚሰጠው ቃል

አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በምርመራ ሂደትም ሆነ ክስ ከቀረበበት በኃላ ክሱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት የሚሰጠው የእምነት ቃል በሕግ ተቀባይነት ካላቸው የማስረጃ ዓይነቶች ውስጥ የሚካተት መሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 27፣ 35 እና 134 ድንጋጌዎች ተመልክቷል፡፡ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ የዚህ ዓይነቱን የእምነት ቃል የሚሰጠው የራሱን አጥፊነት አምኖ በመቀበል እንደሆነ የሚገመት በመሆኑ ሌሎች ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾች ወይም ማናቸውም ሌላ ሰው በወንጀሉ አደራረግ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ በእምነት ቃሉ ውስጥ የሚገልጻቸው ፍሬ ነገሮች ምናልባት ለቀጣይ ምርመራ ፍንጭ ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል ከሚባል በቀር በማናቸውም ሰው ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም፡፡

በሌላ አነጋገር አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በምርመራ ሂደትም ሆነ ክሱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት የሚሰጠው የእምነት ቃል ውጤት በራሱ በቃል ሰጪው ላይ ተወስኖ የሚቀር ከመሆኑ ውጪ ወደሌሎች ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች ሊተላለፍ የሚችል አለመሆኑን ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች አነጋገር እና ይዘት መገንዘብ የሚቻል ከመሆኑም በላይ ወንጀሉን የፈጸሙት በጋራ ወይም በመተባበር መሆኑን በማመን አንደኛው ተከሳሽ የሚሰጠው የእምነት ቃል ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ በሚከራከረው ሌላኛው ተከሳሽ ላይ ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትል የማይችል ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 94450 በ25/07/2006 ዓ.ም. የሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በተያዘው ጉዳይ ላይ ተፈጻሚነት ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 96310 ቅጽ 17፣[1] ወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 27፣35 እና 134

በወንጀል ጉዳይ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 134(1) እንደተደነገገው ተከሣሹ የተከሰበበትን የወንጀል ክስ ይዘት በሚገባ ተረድቶ አድራጐቱን እንደቀረበበት የወንጀል ክስ ዝርዝር መፈፀሙን አምኖ የእምነት ቃል በሰጠ ጊዜ ይህ የእምነት ቃል ለቀረበበት የወንጀል ክስ ማስረጃ ሆኖ በዚሁ ማስረጃ መሠረት የጥፋተኝነት ውሣኔ መስጠት የሚቻልበት ሥርዓት ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አኳኋን ተከሣሹ የሚሰጠው የእምነት ቃል በማስረጃነቱ ተይዞ የሚሰጠው የጥፋተኛነት ውሣኔ ውሣኔውን በሰጠው ፍ/ቤቱ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም፡፡ በዚህ ውሣኔ ቅሬታ የተሰማው ወገን በህገ-መንግስቱም አንቀጽ 20(6) ሆነ በዝርዝር በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕጉ መሠረት ከታች ወደ ላይ በይግባኝ የመከራከር መብቱን ለማስጠበቅ የይግባኝ አቤቱታ የሚያቀርብበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡

በዚህ መሠረት በይግባኝ በሚቀርበው መከራከሪያ ነጥብነቱ እንደ ወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 134(1) ድንጋጌ አነጋገር የወንጀሉን አድራጐት ለመፈፀሙ የእምነት ቃል አልሰጠሁም፤ ነገር ግን እንዳመንኩ ተደርጎ ጥፋተኛ ነህ ተብያለሁ በማለት ቅሬታ የቀረበ እንደሆነ ተከሳሹ ተላልፎታል በሚል የተጠቀሠበት ድንጋጌ ሥር የተቋቋመውን የወንጀል ዝርዝር ተከሣሹ በአፈፃፀሙ ረገድ የሰጠውን ዝርዝር የአፈፃፀም ሁኔታ በማገናዘብ በእርግጥም እንደ ክሱ የወንጀሉን አድራጐት ፈጽሞታል ወይስ አልፈፀመውም የሚለውን ለመለየት ተከሣሹ ሰጠ የተባለው ዝርዝር የእምነት ቃል በመዝገቡ ላይ ሠፍሮ ካልተገኘ በቀር የበላይ ፍ/ቤቶች ተገቢውን ዳኝነት ለመስጠት አያስችላቸውም፡፡

ሰ/መ/ቁ 77842 ቅጽ 14፣[2] ወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 134/2/

በወንጀል የተከሰሰ ሰው ጥፋተኛ ተብሎ የሚቀጣው በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 134(1) መሠረት በሰጠው የእምነት ቃል መሰረት ከሆነ ፍርድ ቤቶች ተከሳሹ ከሰጠው የእምነት ቃል ውስጥ ተከሳሹን የሚጠቅመውን ክፍል በመተው፤ በዕምነት ቃሉ ያላስመዘገበውን ፍሬ ነገር መሰረት በማድረግ ቅጣት ሊያከብዱ አይገባም፡፡

ሰ/መ/ቁ 96954 ቅጽ 16[3]

[1] አመልካች አቶ ጉዲና ለማ ገዛኸኝ እና ተጠሪ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት የስ/ፀ/ሙስና ኮሚሽን ዐ/ሕግ ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም.

[2] አመልካች አቶ ሳሚ ሁሴን እና ተጠሪ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ታህሣስ 03 ቀን 2005 ዓ.ም.

[3] አመልካች ዘፈሩ ወልደ ትንሣኤ አብርሃ እና ተጠሪ የፌዴራል ዐቃቤ ህግ ሚያዚያ 24 ቀን 2006 ዓ.ም.