Category: Articles

ይርጋ፡ ማንሳት መተው መቋረጥ እና መነሻ ጊዜ

ይርጋ

በህግ ተለይቶ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በኋላ በአንድ ጉዳይ ክስ ለማቅረብ የሚከለከልበት የህግ ፅንሰ-ሃሳብ

ይርጋ አንድ ሰው በጉዳዩ ላይ መብት ያለው ቢሆንም እንኳን ይህንን መብቱን ለመጠየቅ የማይችልበትን ገደብ የሚመለከት ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 44800 ቅጽ 10[1]

የይርጋ ህግ መሰረታዊ አላማ ተገቢውን ጥረት የሚያደርጉ ገንዘብ ጠያቂዎችን ወይም መብት አስከባሪዎችን መቅጣት ሳይሆን መብታቸውን በተገቢው ጊዜ ለመጠየቅ ጥረት የማያደርጉትን ሰዎች መቅጣት መሆኑ ይታመናል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 98358 ቅጽ 17[2]

የይርጋ መቃወሚያ ማንሳት

ክሱ በይርጋ ቀሪ እንደሚሆን በመግለጽ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ /በተከሳሽ/ ማቅረብ

የይርጋ ደንብ ተፈጻሚ የሚሆነው ክስ ከቀረበ በኋላ ተከሳሹ የይርጋ መቃወሚያ አንስቶ የተከራከረ ከሆነ ነው፡፡ ከሳሽ ክስ የማቅረብ መብቱ በይርጋ ቀሪ ከሆነ በኋላ ክስ አቅርቦ ተከሳሽ ክሱ በይርጋ ቀሪ መሆኑን በመግለጽ ካልተቃወመ ክሱ ተቀባይነት አግኝቶ መታየት ይቀጥላል፡፡ የጊዜ ገደቡ በማለፉ ብቻ ፍ/ቤት ይርጋውን በራሱ አነሳሽነት አንስቶ ክሱን ውድቅ ሊያደርግ አይችልም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 44800 ቅጽ 10[3]

በመርህ ደረጃ የይርጋ ጥያቄ በተከራካሪዎች ካልተነሳ ፍርድ ቤቱ በራሱ አነሳሽነት ሊያነሳው አይችልም፡፡ የይርጋን ጉዳይ የማንሳት ወይም ያለማንሳት ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የተከሳሽ ወገን ነው፡፡ ይህ አጠቃላይ መሰረተ ሀሳብ ግን ባልተነጣጠለ ኃላፊነት በተከሰሱ ተከሳሾች ላይ ተፈጻሚነት የለውም፡፡ በዚህን ጊዜ በአንደኛው ተከሳሽ የሚነሳ የይርጋ መቃወሚያ ክሱን በይርጋ ቀሪ የሚያደርገው ቢሆን መቃወሚያው በሁሉም ተከሳሾች እንደተነሳ ተቆጥሮ ክሱ ውድቅ መደረግ ይኖርበታል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 19081 ቅጽ 4፣[4] ፍ/ህ/ቁ. 1677፣ 1901

ተከራካሪዎች የይርጋ ጥያቄ እስካቀረቡ ድረስ ጥያቄውን በትክክለኛው አንቀጽ መሰረት እንዲመራ ማድረጉ የፍርድ ቤት ሃላፊነት ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 17937 ቅጽ 4፣[5] ፍ/ህ/ቁ. 1000፣ 1677፣ 1845

የይርጋ ደንብ አንድ ክስ በፍርድ ቤት ቀርቦ በስረነገር እንዳይታይ የሚከለክል ሲሆን የሕሊና ግምት (በ2024 የሰፈረው የመክፈል ግምትን ጨምሮ) በሌላ በኩል የማስረዳት ሸክምን ከአንድ ወገን ወደ ሌላው የማስተላለፍ ውጤት ብቻ ያለው በመሆኑ ከሣሽ ያቀረበውን ክስ ይዘት መርምሮ ውሣኔ መስጠትን የሚከለክል አይደለም፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉ ውስጥ የሰፈረውን ይርጋ ተከሣሹ ወገን ካላነሳው ፍርድ ቤቱ በራሱ ሊያነሳ እንደማይችል በፍትሐብሔር ሕግ ቁ.1856 የተጠቀሰ ቢሆንም ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚነት የሚኖረው ለይርጋ ድንጋጌዎች እንጂ በሕግ ግምት የማስረዳት ሸክም ከአንድ ተሟጋች ወደ ሌላው በሚዘዋወርባቸው ሁኔታዎች አይደለም፡፡

በመሆኑም ይርጋን (Period of limitation) ከሕግ ግምት (Presumptions) ጋር በማመሳሰል ለይርጋ ተፈፃሚ የሚሆነው ሕግ ለህግ ግምትም ተፈፃሚ መሆን ይገባዋል በማለት የሚቀርብ ክርክር የህጉን መንፈስ፣ ዓላማና ግልጽ ይዘት ያልተከተለ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 17068 ቅጽ 1[6]

ይርጋ መተው

አንድ ሰው የይርጋ ጊዜውን ትቶታል የሚባለው ለዕዳው ምንጭ የሆነውን ግዴታ በማመን አዲስ መተማመኛ ሰነድ የሰጠ እንደሆነ ነው፡፡ ይርጋን መተው ውጤቱ ይርጋን የሚያቋርጥ ሳይሆን አዲስ የይርጋ ጊዜ መቆጠር እንዲጀምር ያደርጋል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 90361 ቅጽ 6[7]

ይርጋ መቋረጥ

በፍ/ብ/ሕ/ቁ/1852 ድንጋጌ መሠረት ይርጋ በተቋረጠ ጊዜ ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ እንደገና አዲስ የይርጋ ዘመን መቁጠር እንደሚጀምር በዚሁ ድንጋጌ በንዑስ ቁጥር /1/ ሥር ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ በግልጽ መረዳት የሚቻለው ይርጋው በተቋረጠ ጊዜ ቀድሞ የነበረው የይርጋ ጊዜ እንደ አዲስ መቁጠር የሚጀምር መሆኑን ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 31185 ቅጽ 6[8]

በሕግ ተለይቶ የተወሰነ የይርጋ ጊዜ የመቋረጥ እና ያለመቋረጥ ጉዳይ አከራካሪ ነጥብ ሆኖ ሊነሳ የሚችለው የይርጋውን መቆጠር ያቋርጠዋል የተባለው ምክንያት የተከሰተው የይርጋው ጊዜ ከመሙላቱ በፊት በሆነ ጊዜ እንጂ የይርጋው ጊዜ የሞላ ወይም ያለፈ በሆነ ጊዜ ጭምር አይደለም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 90361 ቅጽ 6[9]

ክስ የማቅረብ ውጤት

ስልጣን ለሌለው የዳኝነት አካል ክስ ማቅረብ ይርጋን ያቋርጣል፡፡

(በመዝገብ ቁጥር 16648 ስለ ይርጋ ጊዜ አቆጣጠርና ስለ ይርጋ መቋረጥ የተሰጠው የሕግ ትርጉም ተለውጧል፡፡)

ሰ/መ/ቁ. 36730 ቅጽ 9[10]

ክስ የማቅረብ ውጤት /ሽያጭ ውል/

ይርጋ ከሚቋረጥባቸው ምክንያቶች አንደኛው ባለገንዘቡ መብቱ እንዲታወቅለት በፍ/ቤት ክስ አቅርቦ ለባለእዳው አስታውቆ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 43992 ቅጽ 10፣[11] ፍ/ህ/ቁ. 1851(ለ)

ክሱ የቀረበው መብቱን በሚጠይቀው ባለገንዘብ ባይሆንም ባለዕዳው በባለገንዘቡ ላይ ያቀረበው ክስ በይዘቱ የይርጋ መቃወሚያ ከተነሳበት ክስ ጋር ተያያዥነት ካለው ይርጋውን ያቋርጠዋል፡፡

የማይንቀሳቀስ ንብረት ገዢ ንብረቱን ለመረከብ (የሽያጭ ውሉ እንዲፈጸምለት) ያቀረበው ክስ ከሽያጭ ውሉ ቀን ጀምሮ ሲቆጠር በይርጋ የሚቋረጥ ቢሆንም ሻጭ ቀደም ብሎ የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስለት ክስ ካቀረበ በገዢው ላይ ተፈጻሚ የሚሆነውን የይርጋ ጊዜ ያቋርጠዋል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 43636 ቅጽ 10[12]

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1776 እና በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ድንጋጌዎች መሠረት የቤት ሽያጭ ውል ይፈጸምልኝ ክስ ሲቀርብ በሕግ የተደነገገው የይርጋ ሕግ የጊዜ ገደብ አልፏል ወይስ አላለፈም? የሚለውን ነጥብ ለመወሰን በመጀመሪያ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀጽ 3 ድንጋጌ ይዘት መንፈስና ዓላማ እንደዚሁም ድንጋጌው ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2875 መሠረታዊ መርህና ስለ ሽያጭ እና ጠቅላላ ውል ከተደነገጉ ድንጋጌዎች ጋር ሊኖረው የሚገባውን ተፈፃሚነት መመርመር ያስፈልጋል፡፡

 1. የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2893 ንዑስ አንቀጽ 3 “ስለሆነም ሻጭ ውሉን እንደውሉ ቃል ለመፈፀም መዘግየቱን ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ውሉ እንዲፈፀምለት ካልጠየቀ በቀር ገዢው ውሉ በግዴታ እንዲፈፀም የማድረግ መብቱን ያጣል” በማለት ይደነግጋል፡፡ እዚህ ላይ በአማርኛው “መዘግየቱን ከተረዳበት” በሚለውና በእንግሊዘኛው “ascertained” በሚለው ቃል መካከል ልዩነት ያለመሆኑን ለመገንዘብ እንችላለን፡፡ የድንጋጌው መንፈስ ገዥ በአንድ ዓመት ውስጥ ውሉ እንዲፈፀምለት ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ ያለበት ሻጭ በሽያጭ ውሉ መሠረት ለመፈፀም ፈቃደኛ አለመሆኑን ካረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ የእንግሊዘኛውን የቃል አጠቃቀም በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ የሚነሣው ጥያቄ ሻጭ በሽያጭ ውሉ መሠረት ለመፈፀም እንደማይፈልግ ገዥ ያረጋገጠ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ ያለበት ማን ነው? የሚለው ነው፡፡ ለዚህ መሠረታዊ ነጥብ እልባት ለመስጠት ስለውል እና ተዋዋይ ወገኖች በፍትሐብሔር ሕጉ የተቀመጠ የሕግ ግምቶችን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡

 1. በሕግ አግባብ የተቋቋሙ ውሎች ባቋቋሟቸው ሰዎች ላይ ሕግ ናቸው በማለት የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1731ንዑስ አንቀጽ 1 የደነገገ ሲሆን ውሎች በተዋዋይ ወገኖች መካከል ሊኖር የሚገባውን የቅንነት የመተማመን ግንኙነት መሠረት በማድረግ በቅን ልቦና ሊተረጎሙ እንደሚገባ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1732 ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ስናየው ተዋዋይ ወገኖች በተዋዋሉት የውል ቃል መሠት ውሉን የመፈፀም ፍላጎትና ቅን ልቦና ያላቸው መሆኑ የውል ሕግ ግምት የሚወስድበት ጉዳይ በመሆኑ ገዥ ሻጭ በሽያጭ ውሉ በገባው የውል ቃል መሠረት እንደሚፈጽም የተለያዩ የተስፋ ቃሎችን ሲሰጠው የቆየ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ የለበትም፡፡

በተቃራኒው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀጽ 3 ድንጋጌን ጠቅሶ የሚከራከር ሻጭ ከገዥ ጋር ባደረገው የቤት ሽያጭ ውል መሠረት ለመፈፀም ፍላጎት የሌለው መሆኑን ገዥ በማያሻማ ሁኔታ እንዲያውቅ እና እንዲረዳው ያደረገ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ ሻጭ በውሉ መሠረት ለመፈፀም እንደማይፈልግ በእርግጠኝነት ገዥ እንዲያውቅ ካደረገው ከአንድ ዓመት በኋላ የሽያጭ ውሉ በፍርድ ኃይል እንዲፈፀምለት የጠየቀ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ ስለሆነም የማይንቀሣቀስ ንብረት የሸጠ ሰው ሻጭ በሽያጭ ውሉ መሠረት የቤቱን ይዞታና የባለቤትነት ሰነዶች ለገዥ ያላስረከበ ከሆነ ውሉን ለመፈፀም ፈቃደኛ አለመሆኑንና በጽሑፍና በማያሻማ ሁኔታ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1789 ንዑስ አንቀጽ 3 በሚደነግገው አይነት ለገዠ ካሣወቀው ከአንድ ዓመት በኋላ የውል ይፈፀምልኝ ክስ ያቀረበ መሆኑን ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡

ሻጭ በውሉ መሠረት የቤቱን ይዞታና የባለቤትነት ሰነዶች ለገዥ አስተላልፎ ከሆነ ገዥ ሻጭ በውሉ መሠረት ይፈጽማል የሚለውን ዕምነት የሚያጠናክርና ውሉም በከፊል መፈፀም መጀመሩን የሚያሣይ መሆኑን ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2875 እና ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2274 ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ ሰለሆነም ሻጭ የቤቱን ባለሀብትነት ለገዥ ለማስተላለፍ እንደማይፈልግና የቤቱን ይዞታ ሻጭ በመልቀቅ እንዲያስረክበው የከፈለውንም ገንዘብ ገዥ እንዲወስድ በማያሻማ ሁኔታ የፍትብሔር ሕግ ቁጥር 1789 ንዑስ አንቀጽ 3 በሚደነግገው አይነት ለገዥ ያሣወቀ መሆኑን ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡

ሻጭ የቤቱን ሰነዶች ለገዥ አስተላልፎ የቤቱን ይዞታ ይዞ በሚገኝበት ጊዜ የቤቱን ሰነዶች ሻጭ እንዲመልስለት የከፈለውን ገንዘብ እንዲወስድ በማያሻማ ሁኔታና የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1789 ንዑስ አንቀጽ 3 በሚደነግገው አይነት ለገዥ ያሣወቀ መሆኑን ማስረዳት የሚጠበቅበት ሲሆን ከላይ ከተጠቀሱት ሁኔታዎች በአማራጭ ሻጭ ውሉ እንዲፈርስለት ወይም እንዲሰርዝለት በፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ በውሉ መሠረት የመፈፀም ፍላጎት የሌለው መሆኑን ገዥ እንዲረዳው ከተደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ የውል ይፈፀምልኝ ክስ ገዥ ያቀረበ መሆኑን ወይም በሕግ እውቅና ላለው የሽምግልና ተቋም ሻጭና ገዥ በነበራቸው ድርድር ሻጭ ውሉን ለመፈፀም እንደማይፈልግ ገዢ  እንዲረዳው ከተደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ ክሱን ያቀረበው መሆኑን የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ በአጠቃላይ ሻጭ በገባው የሽያጭ ውል ቃል መሠረት ለመፈፀም ፍላጎት የሌለው መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ለገዥ ካሣወቀውና ገዥም ይህንኑ ከተረዳና ካረጋገጠ ከአንድ ዓመት በኋላ የውል ይፈፀምልኝ ክስ ገዥ ያቀረበ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡

ሻጭ በውሉ መሠረት ለመፈፀም የማይፈልግ መሆኑን ገዥ ያረጋገጠ መሆኑን ገዥ ውሉ እንዲፈፀምለት ማስጠንቀቂያ መስጠቱንና ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ሻጭ በውሉ መሠረት አለመፈፀሙን በማየት ብቻ ለማረጋገጥ አይችልም፡፡ ሻጭ ገዥ ማስጠንቀቂያ ከሰጠው በኋላም ቢሆን የተለያዩ ችግሮችን እያነሣ በመካከላቸው ያለውን የመተማመንና የቅን ልቦና ግንኙነት ተጠቅሞ ከአንድ ዓመት በላይ ውሉን ሣይፈፅም የሚቆይበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡

ስለዚህ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀጽ 3 ይርጋ ተፈፃሚነት የሚኖረው ገዥ ለሻጭ ማስጠንቀቂያ የሰጠበትን ቀን መነሻ በማድረግና ጊዜውን በማስላት ሣይሆን ሻጭ በውሉ መሠረት የመፈፀም ፍላጎት የሌለው መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ገዥ እንዲያውቀው ያደረገበትን ቀን መነሻ በማድረግ መሆን ይገባዋል፡፡

 1. በሁለተኛ ደረጃ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀጽ 3 የተደነገገው የይርጋ ጊዜ ተፈፃሚነት የሚኖረው በሻጭና በገዥ መካከል የተደረገው ውል የማይፈፀምበት የመጨረሻ ቀን በጥብቅ የተወሰነ ከሆነ በውሉ የተወሰነ የጊዜ ገደብ ካለፈ ከአንድ ዓመት በኋላ ገዥ የውል ይፈፀምልኝ ክስ ማቅረቡን በማስረዳት እንደሆነ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2875 መሠረታዊ መርህና የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀጽ 3 ድንጋጌዎች ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2331ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ድንጋጌዎች ጋር አጣምሮ በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡
 2. በሶስተኛ ደረጃ የሚነሣው ጥያቄ በዚህ ጉዳይ ተጠቃሽና ተፈፃሚ መሆን ያለበት የይርጋ ሕግ ድንጋጌ የትኛው ነው? የሚለው ነው፡፡ ሻጭ በውሉ መሠረት የመፈፀም ፍላጎት የሌለው መሆኑን ለገዥ በማያሻማ ሁኔታ ያሣወቀ መሆኑን ባላስረዳበት ሁኔታ ወይም የሽያጭ ውሉ የሚፈፀምበትን ጥብቅ የጊዜ ገደብ ባልተገለፀበት ሁኔታ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀጽ 3 የተደነገገው የአንድ ዓመት የይርጋ የጊዜ ገደብ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ በልዩ የሕግ ድንጋጌ የተቀመጠዉ የይርጋ ጊዜ ገደብ ተፈፃሚነት በማይኖረው ጊዜ ወይም በልዩ ሁኔታ የተደነገገ የይርጋ የጊዜ ገደብ ከሌለ ውል ይፈፀምልኝ በሚል መነሻ የሚቀርቡ ክርክሮች ላይ ተፈፃሚት ያለው የይርጋ ሕግ ድንጋጌ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1845እንደሆነ ይህንን ድንጋጌ ይዘት በመመርመር ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 38935 ቅጽ 8[13]

ሻጭ የውል ይፍረስልኝ ክስ ለፍርድ ቤት ማቅረቡ ውሉን ለመፈፀም ፍላጎት የሌለው መሆኑን ለገዢ በማያሻማ መንገድ ከማሣወቅ ያለፈ ምክንያትና ውጤት ያለው ተግባር ነው፡፡ ሻጭ ውሉ እንዲፈርስ ሲጠይቅ ውሉ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለማቋቋም የማያስችሉ ጉድለቶች ያሉበት በሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች እንደ ሕግ ሆኖ ሊገዙበት የማይገባ መሆኑን የሚያሣዩ የውሉን ሕልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባና የውል ሕጋዊነት በፍርድ ቤት ተመርምሮ ፈራሽ እንዲባል ወይም እንዲሠረዝ የሚቀርብ ነው፡፡ የውሉ ሕጋዊነትና ሕልውና ጥያቄ ተነስቶበት በፍርድ ቤት በሚመረመርበት ጊዜ ሂደት ገዢ ውሉ ሕጋዊ መሆኑን ከማሣየትና ከማስረዳት አልፎ ውሉ በግዳጅ እንዲፈጽምለት የመጠየቅ ግዴታ አይኖርበትም፡፡

ከዚህ አንፃር ውሉ በፍርድ ቤት ፈራሽ እንዲሆን ወይም እንዲሰረዝለት በውሉ የሚገደድበት ሁኔታ ይቋረጣል፡፡ በሌላ በኩል በክርክሩ ከተረታ ገዢ ሕጋዊ ተፈፃሚነትና አስገዳጅነት ባለው ውሉ ንብረቱን የገዛ መሆኑ ከሻጭ ጋር ባደረገው የውል ሰነድ ብቻ ሣይሆን በፍርድ ቤት ውሣኔ የተረጋገጠለት የፍርድ ባለመብት ይሆናል፡፡ ስለሆነም ገዢ ፍርድ ቤቱ ሕጋዊነቱንና አስገዳጅነቱን መርምሮ በፍርድ ያረጋገጠውን ውል እንዲፈጽምለት ሻጭን የመጠየቅ መብቱ በፍርድ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 384/ሀ/ በተደነገገው አስር ዓመት ጊዜ ውስጥ እንጂ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀጽ 3 በተደነገገው የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ የሚገደብ አይደለም፡፡ ስለዚህ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2892 ንዑስ አንቀስ 3 የተቀመጠው የጊዜ ገደብ በዚህ ጉዳይ አግባብነት የለውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 39725 ቅጽ 8[14]

ይርጋ መነሻ ጊዜ(የ—)

ይርጋ መቆጠር የሚጀምርበት ጊዜ

የይርጋ ቀን መቆጠር የሚጀምረው ግዴታውን ለመጠየቅ ተገቢ ከሆነው ወይም ውሉ የሚሰጠው መብት ከተሰራበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

የሥራ ውል የተቋረጠበትና የስንብት ደብዳቤ የተሰጠበት ቀን ከተለያየ ይርጋ መቆጠር የሚጀምረው ደብዳቤው ለሠራተኛው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 94931 ቅጽ 16፣[15] ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1846

በፍትሐ ብሔር ስነ-ስርዓት ህጉ የሚገኙት የጊዜ ገደቦች አቆጣጠር የሚመራው በፍትሐ ብሔር ህግ ባሉት የጊዜ አቆጣጠር ደንቦች ነው፡፡

ጉዳዩ በሌለበት ታይቶ ውሳኔ የተሰጠበት ወገን ውሳኔው እንዲነሳለት በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 78/1/ መሰረት በአንድ ወር ውስጥ የሚያቀርበው ጥያቄ የአንድ ወር ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው ውሳኔ መሰጠቱን ከተረዳበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ ሆኖም የመጀመሪያው ቀን ለይርጋው ጊዜ መቆጠር መነሻ አይሆንም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 76601 ቅጽ 13፣[16] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 78/1/

በወራሾች መካከል ውርስ እንዲጣራ አቤቱታ መቅረብ ያለበት በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ይህም ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው አንደኛው ወራሽ የውርሱን ንብረት በእጁ ካደረገበት እንጂ ስመ ሀብቱን በስሙ ካዞረበት ጊዜ ጀምሮ አይደለም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 52407 ቅጽ 11፣[17] ፍ/ህ/ቁ. 1000/1/

ከውርስ ሃብት ጋር በተያያዘ ወራሽ የሆነና አካለ መጠን ያልደረሰ ሰው ላይ የይርጋ ጊዜ ሊቆጠር የሚገባው አካለ መጠን ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 57114 ቅጽ 11[18]

ይዞታን አስመልክቶ ከሚነሳ የሁከት ይወገድልኝ አቤቱታ ጋር በተያያዘ ተፈፃሚ የሚሆነው የይርጋ ጊዜ መቆጠር ያለበት አቤቱታ አቅራቢው የይዞታ መብቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከሚመለከተው አካል ካገኘበት ቀን ጀምሮ እንጂ አቤቱታ የቀረበበት ድርጊት መፈፀም ከጀመረበት ዕለት አይደለም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 60392 ቅጽ 11፣[19] ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1140፣ 1149፣ 1146/1/፣ 1144/2/

[1] አመልካች አቶ አብደራዛቅ ሀሚድ እና ተጠሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥቅምት 05 ቀን 2002 ዓ.ም.

[2] አመልካች አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ እና ተጠሪ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጥር 05 ቀን 2007 ዓ.ም.

[3] አመልካች አቶ አብደራዛቅ ሐሚድ እና ተጠሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥቅምት 05 ቀን 2002 ዓ.ም.

[4] አመልካች አሊ ቃሌብ አህመድ እና ተጠሪ እነ አቶ ሚሊዮን ተፈራ /3 ሰዎች/ መጋቢት 18 ቀን 1999 ዓ.ም.

[5] አመልካች ወ/ሮ ድንቄ ተድላ እና ተጠሪ እነ አቶ አባተ ጫኔ መጋቢት 20 ቀን 1999 ዓ.ም.

[6] አመልካች የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት እና መልስ ሰጪ ሚ/ር ቢሮኒ አቲክፖ ሐምሌ 19 ቀን 1997 ዓ.ም.

[7] አመልካች የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ተጠሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግንቦት 12 ቀን 2000 ዓ.ም.

[8] አመልካች የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ተጠሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግንቦት 12 ቀን 2000 ዓ.ም.

[9] አመልካቾች እነ ወ/ሮ አለዊያ ዑመር /7 ሰዎች/ እና ተጠሪ አቶ ሐሺም ሁሴን የካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም.

[10] አመልካች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይሌ ኮርፕሬሽን እና ተጠሪ አቶ አማረ ገላው ሀምሌ 30 ቀን 2002 ዓ.ም.

[11] አመልካች እነ አቶ ይሌማ አንበሴ /4 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ እመቤት መንገሻ /5 ሰዎች/ መጋቢት 6 ቀን 2002 ዓ.ም.

[12] አመልካች ወ/ሮ አሌማዝ ተሰማ እና ተጠሪ እነ አቶ በየነ ወ/ሚካኤሌ/2 ሰዎች/ መጋቢት 22 ቀን 2002 ዓ.ም.

[13] አመልካች እነ አቶ ወልደፃድቅ ብርሃኑ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ አቶ ስንታየሁ አያሌው መጋቢት 3 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም.

[14] አመልካቾች እነ ወ/ሮ ዓለምሸት ካሣሁን /3 ሰዎች/ እና ተጠሪ አቶ ሽመልስ እንዳለ ሐምሌ 23 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም.

[15] አመልካች ወ/ሮ ጥሩወርቅ መንግስቴ ተጠሪ የተገጣጣሚ ህንፃ አካላት ማምረቻ ድርጅት የካቲት 14 ቀን 2006 ዓ.ም.

[16] አመልካች አቶ ሽመልሽ አማረ እና ተጠሪ አቶ አማረ መኮነን ሰኔ 18 ቀን 2004 ዓ.ም.

[17] አመልካቾች እነ ወ/ሮ ውልታ ደስታ ወ/ማሪያም /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ ወ/ሮ እቴቴ ደስታ ኅዳር 27 ቀን 2003 ዓ.ም.

[18] አመልካች ወ/ሮ ሃና ፀጋዬ እና ተጠሪ ወ/ት ጣዕሙ ደስታ ግንቦት 3 ቀን 2003 ዓ.ም.

[19] አመልካች አቶ ጌትነት የኔው እና ተጠሪ አቶ ኢዩብ ቢንያም ወ/ቢኒያም ታህሣሥ 26 ቀን 2003 ዓ.ም.

ይርጋ የማያግደው ክስ-የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

ፍቺ

በይርጋ ቀሪ የማይሆን፣ ክስ ለማቅረብ በህግ የጊዜ ወሰን ያልተቀመጠለት የመብት ጥያቄ

አደራ

ወራሾች በአደራ የተያዘ የሟች ንብረት ለማስመለስ የሚያቀርቡት ክስ በይርጋ አይታገድም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 48048 ቅጽ 10፣[1] ፍ/ህ/ቁ. 2779፣ 2781፣ 2989(1)

የውርስ ሀብት ክፍፍል

የውርስ ክፍያ ጊዜን በተመለከተ የፍ/ብ/ሕጉ በአንቀጽ 1062 ስር የደነገገ ሲሆን የድንጋጌው ይዘትም ውርሱ በተጣራ ጊዜ በማናቸውም ጊዜ ቢሆን እያንዳንዱ የጋራ ወራሾች ውርሱን እንከፋፈል ብለው ለመጠየቅ እንደሚችሉ መደንገጉን የሚያሳይ ነው፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1060 ድንጋጌ ስር ደግሞ የውርስ አከፋፈል እስካልተፈፀመ ድረስ ውርሱ በወራሾች መካከል ሳይነጣጠል እንደሚቆይ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም ወራሽ የሟች ወራሽቱን በሕጉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ አረጋግጦ ከቆየ በኋላ የሚያቀርበው የውርስ ንብረት የክፍፍል ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1000/1/ እና /2/ ስር በተመለከተው የይርጋ ድንጋጌ የሚታገድ ሳይሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1062 ድንጋጌ መሠረት በማናቸውም ጊዜ የሚቀርብ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 38533 ቅጽ 10፣[2] ፍ/ህ/ቁ. 1000(1) እና (2)፣ 1060

የመፋለም ክስ

የማይንቀሳቀስ ንብረት የመፋለም ክስ በይርጋ ቀሪ አይሆንም፡፡ ከባለቤትነት መብት ጋር ተያየዥነት ያላቸው ነገር ግን ከመፋለም መብት ውጪ ያሉ ሌሎች ክሶች እንደሚጠየቀው መፍትሔ እና ለክሱ ምክንያት እንደሆነው ጉዳይ ዓይነት /ጋብቻ፣ ውርስ፣ ሽያጭ፣ ወዘተ…/ በሌሎች ልዩ የይርጋ ህግ ደንቦች የሚተዳደሩ ናቸው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 43600 ቅጽ 10[3]

የንግድ ማህበር እንዲፈርስ

የንግድ ማህበር ይፍረስልኝ ጥያቄ በውል ከተቋቋመ የማህበርተኝነት መብት የሚመነጭ እና በማህበሩ እንቅስቃሴ ሂደት የሚፈጠሩ የተለያዩ ችግሮችን መሰረት አድርጐ የማህበሩ ህልውና እስካለ ድረስ በማንኛውም ጊዜ ሊቀርብ የሚችል ነው ከሚባል በቀር በታወቀ የይርጋ ጊዜ የሚታገድ ስለመሆኑ የንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች አያመለክቱም፡፡ የማህበር ይፍረስልኝ ክስ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር. 1845 በተመለከተው ጠቅላላ የይርጋ ጊዜ ይታገዳል ሊባል ይችል የነበረውም የይፍረስልኝ ጥያቄው የቀረበው ተለይቶ በታወቀ ቀን የተፈጠረ ክስተትን ጠቅሶ ወይም መሰረት አድርጐ ቢሆን ኖሮ እና ክሱ የቀረበው ክስተቱ ከተፈጠረ አስር ዓመት ካለፈው በኋላ ቢሆን ኖሮ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 94278 ቅጽ 17፣[4] ን/ህ/ቁ. 218(1)፣ 542(!)፣ ፍ/ህ/ቁ. 1835

[1] አመልካች ወ/ሮ ገብርኤላ ኒካላ ቶማስ ናክሶ ተጠሪ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ሐምሌ 22 ቀን 2002 ዓ.ም.

[2] አመልካቾች እነ ወ/ሮ ጽጌ ወልደመስቀሌ /6 ሰዎች/ እና ተጠሪ አቶ ስዩም ክፍሌ ህዳር 08 ቀን 2002 ዓ.ም.

[3] አመልካች ዳዊት መስፍን እና ተጠሪ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ጥር 5 ቀን 2002 ዓ.ም.

[4] አመልካች አቶ ሐሰን መሐመድ እና ተጠሪ ማጂ አግሮ ፎረስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.

አጼ ቴዎድሮስ እና የአስተዳደር ህግ

ስለ ኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ብሎም ውልደቱ፣ አነሳሱና ታሪካዊ ዕድገቱ ለመጻፍ ብዕሩን የሚያሾል ጸሐፊ ጭብጥ እንዳጣ የልብለወለድ ደራሲ ከየት ልጀምር? በሚል ጭንቀት ተውጦ ጣራ ላይ ማፍጠጥ አይቀርለትም፡፡ ስራውን ፈታኝ የሚያደርገው በህዝብ አስተዳደር እና በአስተዳደር ህግ ላይ የተጻፉ የታሪክ መዛግብት፣ የምርምር ጽሑፎችና መጻህፍት አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥ ለጀማሪ አጥኚ ይህ በራሱ ራስ ምታት ነው፡፡ ከመነሻ ምንጭ እጥረት ባሻገር ሌሎች ዐቢይ ምክንያቶች የአገሪቱን የአስተዳደር ህግ ጉዞ መዘገብ አድካሚ ያደርጉታል፡፡ ለመጥቀስ ያህል፤

 • የጥናት አድማሱ ወጥነት እና ትኩረት ማጣት[1]
 • የዲሞክራሲና ህገ መንግስታዊ ዳራው[2]
 • የፖለቲካና አ[3]ስተዳደር መደበላለቅ
 • የህግ አውጭውና የፍርድ ቤቶች ሚና ማነስ[4]

ባደጉት አገራት የአስተዳደር ህግ ዕድገት ጥርት ባለ መልኩ ወጥነትና ስርዓት እየያዘ ራሱን የቻለ የህግ ክፍል ሆኖ ብቅ ማለት የጀመረው የዘመናው የአስተዳደር (Administrative State) ወይም የማህበራዊ ዋስትና መንግስት (Welfare State) መከሰት ተከትሎ ስለመሆኑ ብዙዎች የመስኩ አጥኚዎች ይስማሙበታል፡፡ በተመሳሳይ ቅኝት ስለ አገራችን አስተዳደር ህግ ታሪካዊ ገጽታዎችና መገለጫዎች ከዘመናዊ አስተዳደር ማቆጥቆጥ ጋር አስታኮ አጠቃላይ ገለጻ መስጠት ይቻላል፡፡

በርካታ የአገራችን ሆኑ የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በአገራችን ዘመናዊ አስተዳደር የተተከለው የኃይለስላሴ ዙፋን ላይ መውጣት ተከትሎ በነበሩት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ይስማሙበታል፡፡ በተለይም ከኢጣሊያ ወረራ ማብቃትና የንጉሱ ዙፋን መልሶ መረከብ አንስቶ ዘመናዊ አስተዳደር ፈጣን ለውጦች አሳይቷል፡፡

ስለ ኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር እና አስተዳደር ሲመራበት ስለነበረው ህግ ሲነሳ የአጼ ቴዎድሮስ ውጥን እና ጥረት ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ብሔራዊ ጦር ለማደራጀት፣ የቤተክስርስትያን የመሬት ይዞታ ለመቆጣጠር፣ የአካባቢ የጦር አበጋዞች በማዕከላዊ መንግስት ስር ለማዋቀር እንዲሁም የመንገድ ግንባታና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ለመዘርጋት ያደረጓቸው ጥረቶች ለቀጣይ ነገስታት መሰረት ጥለዋል፡፡ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለማቆም እና ዘመናዊ አስተዳደር ለመትከል የነበራቸውን ህልም፣ ውጥን እና ፖሊሲ እንዲሁም እነዚህን ለመተግበር የወሰዷቸው ስር ነቀል እርምጃዎች የለውጥና የስልጣኔ በር ከፍተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ውልደት ከቴዎድሮስ ይጀምራል፡፡ አስተዳደራዊ ብልሹነት እንዲቀረፍና ሹመኞች በህዝብ አገልጋይነታቸው በደል እንዳይፈጽሙ በጊዜው ሲያደርጉት የነበረው ክትትል እና የስልጣን ቁጥጥር በኢትዮጵያ የታሪክ መጻህፍት ጎልቶ ባይወጣም በአንዳንድ ጽሁፎች ተዘግቦ ይገኛል፡፡ በደርግ ወታደራዊ መንግስት ልዩ ፍርድ ቤት ይዘጋጅ የነበረው ሕግና ፍትሕ መጽሔት በመጋቢት 1987 እትሙ አጼ ቴዎድሮስ ሙስና እና የአስተዳደር ብልሹነት እንዲወገድ ሲያደርጉት የነበረውን ተጋድሎ ሌላ ምንጭ ጠቅሶ እንደሚከተለው ዘግቦታል፡፡[5]

ቴዎድሮስ ወዘልውጥ በመሆንና አልባሌ ልብስ በመልበስ በመንግስቱ ውስጥ ያለው የአስተዳደር መበላሸት መቆጣጠር፣ ጉቦኞች ሹማምንቶቻቸውን መከታተልና ማጋለጥ ያዘውትሩ ነበር፡፡ በሕዝብ ችግር የጨከኑትን፣ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የመንግስቱን ስራ የሚበድሉትንና ኅብረተሰቡን ያጉላሉትን ሹማምንት ከስልጣን ወንበራቸው ገልብጠዋል፡፡ አባ ታጠቅ ስልጣን በጨበጡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ የጯሂ ጠባቂ (የህዝብ ዕንባ ጠባቂ) ሹማቸው ጉቦ መቀበሉን በማወቃቸውና ራሳቸውም ሲቀበል በማየታቸው በአደባባይ አጋልጠው ሽረውታል፡፡…የጯሂ ጠባቂነቱንም ሥራ ራሳቸው ይዘዋል፡፡

አጼ ቴዎድሮስ የመንግስት ስልጣን በህግና በስርዓት እንዲገራ የነበራቸው ቆራጥ አቋም በታሪክ በተዘገቡ ጥቂት የጊዜው ፍርዶች ላይም ይታያል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው በጳውሎስ ኞኞ አጤ ቴዎድሮስ መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ተዘግቧል፡፡[6]

ቴዎድሮስ ጋይንት ላይ ሰፍረው ሳለ ወታደሮቻቸውን በባላገሩ ላይ ተሰሪ አስገቡ፡፡ ባለገሩ እንዲቀልብ በየቤቱ ማስገባት ማለት ነው፡፡ ተሰሪ ከገቡት ወታደሮች መሀል አንዱ ወታደር አንዱን ባላገር ገደለው፡፡ የሟች ወገንም ከቴዎድሮስ ዘንድ መጥቶ አመለከተ፡፡ ቴዎድሮስም ወታደራቸውን ሁሉ አፈርሳታ አስቀምጠው ገዳዩን አውጣ ብለው ያዙ፡፡ ወታደሩም በመላው አድሞ ገዳዩን አላየንም እያለ በቄስ እየተገዘተ ወጣ፡፡ የሟች ገዳይ ወታደር በመጥፋቱ ቴዎድሮስ ተናደው ‘ወታደር ብላ፤ ባላገር አብላ ያልሁ እኔ ነኝ፡፡ ደመኛህም እኔ ነኝና እኔን ግደል’ ብለው ተነስተው ለከሳሹ ነገሩት፡፡ ከሳሹም ‘እኔ ንጉስ መግደል አይቻለኝም’ አለ፡፡ ቴዎድሮስም ደም በከንቱ አይቀርም ብለው ለሟቹ ወገን የደም ገንዘብ ዋጋ ሰጥተው ሸኙት፡፡

በሌላ ፍርድ ላይ እንዲሁ ለሁለት ወታደሮቻቸው የሰጡት እርስ በርሱ የሚጋጭ ትዕዛዝ የአንደኛውን ወታደር ሞት በማስከተሉ ለሞቱ መከሰት ተጠያቂ ተደርገው ስለተፈረደባቸው በዚያ ንጉስ በማይከሰስበት፤ ሰማይ በማይታረስበት ዘመን ቅጣታቸውን ተቀብለው ፍርዱን ፈጽመዋል፡፡ ታሪኩ በአጭሩ እንደዚህ ነው፡፡

ቴዎድሮስ አንዱን ወታደራቸውን ‘በፍርቃ በር በኩል እርጉዝ ሴት እንኳን ብትሆን እንዳታልፍ ጠንክረህ ጠብቅ’ ብለው ካዘዙት በኋላ በሌላ ቀን ደግሞ ሌላውን ወታደር ጠርተው ‘ፈረስ እያለዋወጥህ ይህን ወረቀት የጁ ሰጥተህ በአስቸኳይ በስድስት ቀን ውስጥ ተመልሰህ እንድትመጣ’ ብለው ሲልኩት እየጋለበ ሄዶ ፍርቃ በር ላይ ሲደርስ ጠብቅ ከተባለው ወታደር ጋር ‘አልፋለው! አታልፍም!’ እሰጥ አገባ ገጥሙ፡፡ በግዴታ ለማለፍ መንገድ ሲጀምር ዘበኛው ተኩሶ ገደለው፡፡ የንጉስ ትዕዛዝ ሲፈጽም የነበረ የንጉስ መልዕክተኛ በዚህ መልኩ መገደሉ ያንገበገባቸው የሟች ወገኖች ገዳዩን በመክሰስ ከቴዎድሮስ ዘንድ አቀረቡት፡፡ ቴዎድሮስም ችሎት አስችለው ፍርድ እንዲፈረድ አደረጉ፡፡

በችሎት የተቀመጠው ፈራጅ ሁሉ እየተነሳ ገዳዩን ‘በደለኛ ነህ እምቢ አልፋለው ቢልህስ ለንጉስ ታሰማ ነበር እንጂ ራስህ ፈርደህ እንዴት የንጉስ መልዕክተኛ ትገድላለህ? አሁንም ስትሞት ይታየናል’ እያሉ ፈረዱ፡፡ አንደኛው ፈራጅ ግን ከተቀመጡበት ተነስተው ከሌሎቹ ፈራጆች በመለየት ሁለት ተቃራኒ ንጉሳዊ ትዕዛዝ መስጠት አግባብ ስላልሆነ ጥፋቱ የሚመለከተው ንጉሠ ነገሥቱን እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ ‘ነገር ግን እሳቸው ብርሀን ስለሆኑ ምን ይደረግ?’ በማለት የፍርድ ሀሳባቸውን አሳርገው ተቀመጡ፡፡ አጤ ቴዎድሮስም ይህን የልዩነት የፍርድ ሀሳብ አድንቀው ከተቀመጡበት ተነስተው በተከሳሹ ወታደር ቦታ ወርደው ቆሙ፡፡ በመጨረሻም ፈራጆች በፈረዱት መሰረት በጊዜው የሚከፈለውን የደም ዋጋ አጠፌታውን ብር 500 ከፍለው ጉዳዩ በስምምነት አለቀ፡፡[7]

እነዚህ ሁለት ፍርዶች በጊዜው የነበረውን አጠቃላይ የፍትሕና የዳኝነት ስርዓት እንደማያንጸባርቁ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ሆኖም አንድ መሰረታዊ ነጥብ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ፍርዶቹ የተሰጡበት ዘመን ፍጹማዊ በነበረው የንጉስ ስልጣን ላይ ገደብ እና ተጠያቂነት ሰማይን የማረስ ያክል በተግባር ሊታይ ቀርቶ ከነጭራሹ አይታሰብም፡፡ እውነቱን ለመናገር እስከአሁኑ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ምድር የተፈራረቁት ነገስታትና መሪዎች አንዳቸውም ‘ተጠያቂው እኔ ነኝ!’ ብለው በገሀድ በማወጅ የድርጊታቸውን ውጤት አሜን ብለው የተቀበሉበት አጋጣሚ የለም፡፡ ሌላው ደግሞ የፍርድ አሰጣጡ (በተለይ የሁለተኛው ፍርድ) በራሱ ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ በልዩነት ሀሳብ ጥፋቱ የንጉሱ እንደሆነ ያለፍርሃት የተናገሩት ፈራጅ ንጉሱን ተጠያቂ ለማድረግ በውስጣቸው የተፈጠረው ነጻነትና ድፍረት ድንገታዊ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ አስተዳደራዊ ብልሹነት ለማስወገድና የመንግስት ተጠያቂነት የሰፈነበት መልካም አስተዳደር ለመትከል ያደረጉት ጥረትና የያዙት ጠንካራ አቋም በጊዜው የነበረውን የአገዛዝ ስርዓት መንፈስ ያንጸባርቃል፡፡ ይህንን ለመረዳት ከቴዎድሮስ ቀጥሎ የተነሱትን ገዢዎች በአደባባይ በጥፋተኝነት መፈረጅ የሚያስከትለውን መዘዝ ማሰብ ብቻ ይበቃል፡፡ የዳኝነት ነጻነት ባልሰፈነበት ስርዓት ውስጥ የአገር መሪ ላይ ጣት መቀሰር ጣት ያሳጣል፡፡ ባስ ሲልም ህይወት ያሳጣል፡፡

ንጉስ ሊከሰስ መቻሉ በኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ታሪክ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ድንበር ደፍረው ሊያጠቋቸው የመጡትን እንግሊዞች ሳይቀር ማስደመሙ አይቀርም፡፡ እርግጥ ነው በዚያን ዘመን እንግሊዝ በኅይል አሰላለፍ፣ በጦር መሳሪያ ብዛትና ጥራት ብሎም በኢኮኖሚ ዕድገት ከኢትዮጵያ መጥቃ ሄዳለች፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስ በእንግሊዝ ምድር ‘ንጉስ አይከሰስም፣ ሰማይ አይታረስም’ ነበር፡፡ በዚሁ ዓመተ ምህረት የወጣው Crown Proceedings Act 1947 ያለመከሰስ መብትን እስኪያስወግድ ድረስ በእንግሊዝ አገር መንገስት ከውል ውጭ ኃላፊነት ላደረሰው ጉዳት ዜጋው በቀጥታ ክስ አቅርቦ ዳኝነት ማግኘት አይችልም፡፡ አንድ የአገሬው ምሁር በጊዜው የነበረውን ሁኔታ እና ያለመከሰስ መብት በህግ ቀሪ መደረጉን እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡

There is one public authority that was immune from torts at common law: the Crown. ‘The King can do no wrong’ is an old slogan of the common law. And a tort is a wrong. So at common law the Crown was not liable in tort.  … ‘the King can do no wrong’ can mean either ‘it is not unlawful if the King did it’, or ‘if it was unlawful, it was not the King who did it’… But the Crown Proceedings Act 1947 abolished the immunity. For most purposes, the Crown is liable in tort and breach of contract in the same way as a private individual.[8]

የጊዜው ርዝመት ስንለካው አጼ ቴዎድሮስ ንጉስ የሚከሰስበትን ስርዓት በይፋ በመቀበል እንግሊዞችን በአንድ ክፍለ ዘመን ቀድመዋል፡፡

[1] በበርካታ የህግ ትምህርት ቤቶች የአስተዳደር ህግ ትኩረት ያላገኘና መምህሩ በ assignment የሚገላገለው ኮርስ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችም በቁጥር በጣም ውስን ናቸው፡፡

[2] የአስተዳደር ህግ የአንዲት አገር ፖለቲካዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ነፀብራቅ ነው፡፡ የላይኛው ካላማረ የታችኛውም አያምርም፡፡

[3] አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካና አስተዳደር መሀላቸው ንፋስ አይገባም፡፡ ፖለቲከኛ አስተዳዳሪ ነው፡፡ አስተዳዳሪም ፖለቲከኛ ነው፡፡ ሙያተኝነት (professionalism) በታማኝነት ተውጧል፡፡

[4] ፓርላማና ፍርድ ቤቶች ስራ አስፈጻሚውን ከመቆጣጠር ይልቅ በተገላቢጦሹ ይቆጣጣራቸዋል፡፡ በስልጣን ቁጥጥር ረገድ ሚናቸው አንድም ‘ምንም’ ወይም አሊያም ‘ከምንም የሚሻል’ ዓይነት ዝቅተኛ ነው፡፡

[5] መዝገቡ ምትኬ “በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ወንጀልና ሕግ: በኢትዮጵያ አንዳንድ ሐሳቦች” ሕግና ፍትሕ፡ በኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ልዩ ፍርድ ቤት ቅ.3 ቁ 1. መጋቢት 1978 ዓ.ም. ገፅ 26-55

[6] ጳውሎስ ኞኞ, አጤ ቴዎድሮስ (አዲስ አበባ 1985 ዓ.ም.) ገፅ 146

[7] አበራ ጀምበሬ፤ የኢትዮጵያ ሕግና የፍትሕ አፈጻጸም ታሪክ፡ 1426 እስከ 1996 .. (ሻማ ቡክስ 2006 ዓ.ም.) ገፅ 149-150

[8] Timothy Endicott, Administrative Law (2nd. edn, Oxford University Press, 2011) ገፅ 531

የአስተዳደራዊ ድንጋጌዎች ህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲፈጠር መፍትሔ የመሻት ቀዳሚ ኃላፊነት የተጣለባቸው በየዘርፉ የተቋቋሙ የአስተዳደር መ/ቤቶች ናቸው፡፡ ከትምህርት አሰጣጥ ወይም ጋር ጥራት ጋር የተያያዘ ወይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ችግር ሲከሰት የትምህርት ሚኒስቴር እንቅስቃሴ ይጀምራል፡፡ በጉምሩክ ህግ አፈጻጸም አቤቱታዎች ሲጎርፉ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መፍትሔ ያፈላልጋል፡፡ በግንባታ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ጉዳት ሲደርስባቸው የሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ላይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ትኩረት ሰጥቶ ስራ ይጀምራል፡፡ ችግሮችን ለመቅፍ መላ መዘየድ ችግር የለውም፤  እንዲያውም ይበረታታል፡፡

ይሁን እንጂ በአንድ አገር ውስጥ በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮች ሊቀረፉ የሚገባው በህግና በህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ከፊል ጉዳዮች የተወካዮች ም/ቤትን ጣልቃ ገብነት ይሻሉ፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች ችግር ፈቺነት አቅም በህግ ከተፈቀደላቸው ስልጣን በላይ ሊለጠጥ አይችልም፡፡ አዋጅ ሊመልሰው የሚገባውን መመሪያ ከቀደመው መ/ቤቶች ችግር ፈቺ መሆናቸው ቀርቶ ችግር ፈጣሪ ይሆናሉ፡፡ የአስተዳደር ድንጋጌዎች መመዘኛ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ህጋዊነት ነው፡፡ የቄሳርን ለቄሳር እንዲሉ ተወካዮች ሊመክሩበትና ሊፈቱት የሚገባውን ችግር ተሿሚዎች በመመሪያ ለመቅረፍ መሽቀዳደም የለባቸውም፡፡ የሚከተለው አጭር ዳሰሳ መመሪያ እና ደንብ እያስከተሉት ያለውን የህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት አደጋ በአጭሩ ያስቃኛል፡፡

 1. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአምልኮ ስርዓት

በትምህርት ተቋማት የአምልኮ ስርዓትን በሚመለከት የትምህርት ሚኒስቴር በ2000 ዓ.ም. መመሪያ አውጥቷል፡፡[1] መመሪያው ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ድረስ በሁሉም የትምህርት ተቋማት ተፈጻሚ የሚሆነውን የአምልኮ፣ የአለባበስ እና የአመጋገብ ስርዓት ይደነግጋል፡፡ በአንቀጽ 6.2 እስከ 6.6 ድረስ ከተፈቀዱና ከተከለከሉ ተግባራት መካከል እንደ ቅደም ተከተሉ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

 • 2 የተማሪ ደንብ ልብስ በማያስፈልጋቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሁኔታው በወርክሾፕ፣ በላቦራቶሪ፣ ወይም በህክምና ትምህርት ተቋማት ሙያው ወይም ስልጣናው የሚፈልገው አይነትና የአንዱን ወይም የሌላውን እምነት የማይጋፋ የአለባበስ ስርዓት መከበር ይኖርበታል፡፡
 • 3 የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎች ከዩኒፎርም ጋር የሚመሳሰል “ሂጃብ” ማድረግ ይችላሉ፤ ከሂጃብ በቀር ሙሉ ጥቁር ልብስ ሙሉ በሙሉ ፊትንም ጨምሮ የሚሸፍን ወይም “ኒቃብ” በትምህርት ተቋማት መልበስ አይፈቀድም፡፡
 • 4 የክርስትና እምነት ተከታይ መነኮሳት፤ መነኮሳያይት እና ካህናት እንዲሁም የእስልምና ተከታይ ሼኮች ብቻ በትምህርት ተቋማት ቆብ ሊያደርጉ ወይም ሻሽ ሊጠመጥሙ ይችላሉ፡፡
 • 5 በተራ ቁጥር 6.2፤ 6.3፤ 6.4 የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆነው፤ የትምህርት ተቋማት በሚያዘጋጁት ክብረ በዓል ወይም ተመሳሳይ ጉዳዮች ምክንያት በተቋሙ አስተዳደር ሃይማኖታዊ አለባበሶች ካልተፈቀዱ በስተቀር በማንኛውም መልኩ የማንኛውንም የሃይማኖት የአለባበስ ስርዓት በትምህርት ተቋማት መልበስ አይፈቀድም፡፡
 • 6 በተራ ቁጥር 6.2፤ 6.3፤ 6.4 የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተለየ ሁኔታ የትምህርት ተቋሙ አስተዳደር (በሀዘን፣ በህመም ወዘተ) ከሚፈቅደው በስተቀር ተማሪዎች በመማሪያ ክፍል ውስጥ ነጠላ፣ ጋቢ ወዘተ… መልበስ ሻሽ መጠምጠምና ቆብ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያውን ለማውጣት የስልጣኑን ምንጭ በጊዜው ፀንቶ የነበረውን የኢትዮዽያ ፌደራላዊ ዲሞከራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁ. 471/1998 እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 14 የትምህር ሚኒስቴር የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ተሰጥቶታል፡፡

 1. የትምህርት ስልጠና ስታንዳርድ ያወጣል፡፡ ሥራ ላይ መዋሉንም ያረጋግጣል፡፡
 2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ፣

ሀ) አጠቃላይ የስርዓተ ትምህርት ማእቀፍ ያዘጋጃል፡፡

ለ) ለአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን አነስተኛውን የትምህርት ብቃት መለኪያ ያወጣል፡፡

ሐ) በሙያና ቴክኒክ ዘርፍ የሙያ ስልጠና ደረጃና የብቃት ማረጋገጫ ደረጃ ያወጣል፡፡

መ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊያሟሉ የሚገባቸውን አነስተኛውን ደረጃ ያወጣል፡፡

 1. የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ያቋቁማል፣ ያስፋፋል፤ ዕውቅና ይሰጣል፣ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት መስጠታቸውን ይቆጣጠራል፡፡
 2. ትምህርትና ስልጠናን በተመለከተ አገራዊ የአህዝቦት (በእንግሊዝኛው ቅጂ ‘popularization’) ተግባሮችን ያከናውናል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት ስልጣንና ተግባራት መመሪያውን ለማውጣት ስልጣን እንደሚያጎናጽፉ ድምዳሜ ከመያዙ በፊት አንድ መሰረታዊ ነጥብ መነሳት ይኖርበታል፡፡ ይኸውም፤ ማንኛውም መ/ቤት ከተቋምነቱ ወይም ከአጠቃላይ ስልጣንና ተግባራቱ የመነጨ መመሪያ የመደንገግ ስልጣን (inherent rulemaking power) የለውም፡፡ እያንዳንዱ ተቋም የስልጣኑ ምንጭ የተወካዮች ም/ቤት ውክልና እንደሆነ መቼም መዘንጋት የለበትም፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ሊጠቅስ የሚገባው ውክልና የሰጠውን የህግ ድንጋጌ ነበር፡፡ ስለሆነም ውክልና በሌለበት በትምህርት ተቋማት የአምልኮ ስርዓትን በሚመለከት መመሪያ መደንገግ ከስልጣን በላይ የሆነ ተግባር በመሆኑ መመሪያው የህጋዊነት መስፈርት አያሟላም፡፡

በተጨማሪም የአዋጅ ቁ. 471/1998 አንቀጽ 14 ድንጋጌ ይዘት የአምልኮ ስርዓት በትምህርት ሚኒስቴር እንዲወሰን አይፈቅድም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መመሪያው በክልል መንግስታት ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ጭምር አካቷል፡፡ በመመሪያው የትርጓሜ ክፍል የትምህርት ተቋማት የተባሉት ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ያሉትን በሙሉ ያጠቃልላል፡፡ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን አመራርና አስተዳደር፣ የትምህርት አሰጣጥ፣ የመምህራን አቀጣጠርና አስተዳደር በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር ስልጣን የትምህርት ቤቶችን አመራርና አስተዳደር ለማጠናከር በወጣ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁ. 217/1992 አንቀጽ 1 ተሽሮ ለብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት እና የአዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳድሮች ተላልፏል፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የአምልኮ ስርዓቱን በተመለከተ በህግ መወሰን/ያለመወሰን ስልጣኑም የእነዚህ አካላት ነው፡፡

 2. የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኞች አስተዳዳር

ፍትህ የማግኘት መብትን የሚደነግገው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀፅ 37/1/ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሰራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 በልዩ ሁኔታ ሰራተኞችን ማሰናበትን በተመለከተ በአንቀጽ 37 እንደሚከተለው ደንግጓል፡፡

1) በዚህ ደንብ በሌላ ሁኔታ የተደነገገው ቢኖርም ዋና ዳይሬክተሩ በሙስና የተጠረጠረንና እምነት ያጣበትን ሰራተኛ መደበኛውን የዲስፕሊን አፈፃፀም ስርዓት ሳይከተል ከስራ ማሰናበት ይችላል

2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ስራ መመለስ አይችልም

የህገ መንግስቱና የደንብ ቁ. 155/2000 ድንጋጌዎች በስም (አንቀጽ ቁጥር) ይመሳሰላሉ፡፡ በተግባር ግን ተጻራሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መብት ያናጽፋል፤ ሁለተኛው ይነፍጋል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህገ መንግስቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ ከተጣለባቸው አካላት መካከል አንደኛው ነው፡፡ በዚህ ግዴታው የህግ አውጭነት ስልጣኑ ምንጭ የሆነው ህግ ያሰመረለትን ወሰን ሊያከብር ይገባል፡፡ ምክር ቤቱ ደንብ ቁ. 155/2000 ለማውጣት ህግ እንደፈቀደለት የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ አዋጅ ቁ. 587/2000 አንቀጽ 19/1/ ለ ድንጋጌ ነው፡፡ ይዘቱ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

[የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን] ሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይመራል፡፡

በስልጣን ምንጭነት የተጠቀሰው ህግ ም/ቤቱ በሠራተኞች አስተዳደር በተመለከተ ደንብ እንዲያወጣ ይፈቅድለታል፡፡ ይሁን እንጂ ሠራተኞች በጥርጣሬ እንዲሰናበቱና በየትኛውም የፍርድ አካል መብቸውን እንዳይጠይቁ የሚከለክል ኢ-ህገ መንግስታዊ ደንብ እንዲያወጣ ስልጣን አልሰጠውም፡፡

 3. የህብረህዋሳት ልገሳና ንቅለ ተከላ

የመድሀኒት፣ የምግብና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ደንብ ቁ. 299/2006 አንቀጽ 58-62 ድንጋጌዎች ስለ ደምና ደም ተዋጾ እና የሰውነት አካል ክፍሎችና የህብረህዋሳት ልገሳና ንቅለ ተከላ (donation of blood and blood products and donation and transplantation of organs and tissues) የሚከናወንባቸውን ሁኔታዎች ይደነግጋሉ፡፡ ደንቡ የወጣው የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁ. 661/2002 አንቀጽ 55/1/ እና አሁን በአዋጅ ቁ. 916/2008[2] በተተካው አዋጅ ቁ. 691/2003[3] አንቀጽ 5 ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በተሰጠ ስልጣን እንደሆነ በመግቢያው ላይ ተመልክቷል፡፡ አዋጅ ቁ. 661/2002 የአካላት ልገሳና ንቀለ ተከላ የሚመለከት ድንጋጌ አልያዘም፡፡ አንቀጽ 55/1/ ም/ቤቱ የሰጠው ስልጣን አዋጁን ለማስፈጸም የሚረዱ ደንቦች እንዲያወጣ ብቻ ነው፡፡ አዋጁ በዝምታ ያለፈውን ለዛውም ንቀለ ተከላን የሚያክል ትልቅ አገራዊ ጉዳይ በማስፈጸም ሰበብ በደንብ መወሰን የፓርላማን ቦታ መቀማት እንጂ በውክልና ህግ የማውጣት ተግባር (delegated legislation) አይደለም፡፡

እንደ ተጨማሪ የስልጣን ምንጭ የተጠቀሰው የአዋጅ ቁ. 691/2003 አንቀጽ 5 ትንሽ አግራሞት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ይዘቱ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77 የተመለከተው ይሆናል፡፡

ህገ መንግስት ጠቅሶ ህግ ማውጣት የሚችለው የተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ነው፡፡ በአንቀጽ 77 ንዑስ አንቀጽ 13 እንደሰፈረው የሚኒስትሮች ም/ቤት የተወካዮች ም/ቤት በሚሰጠው ስልጣን መሰረት ደንብ የማውጣት ስልጣን አለው፡፡ ስልጣን በማስተላለፍ የሚፈጠረው የወካይ-ተወካይ ግኝኑነት ሚኒስትሮችን ከአስፈጻሚነት በተጨማሪ የህግ አውጭነት ሚና ያላብሳቸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በውክልና የተላለፈ ስልጣን በሌለበት የሚወጣ ማንኛውም ደንብ የህጋዊነትና ህገ መንግስታዊነት ገደቦችን ይጥሳል፡፡

ከላይ በምሳሌነት የተጠቀሱት አስተዳደራዊ ድንጋጌዎች አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የህጋዊነትና የህገ መንግስታዊነት ችግር ያንጸባርቃሉ፡፡ ውጤታማ የቁጥጥር ስልቶች ባልተረዘጉበት ሁኔታ በየጊዜው የሚወጡት መመሪያዎችና ደንቦች በስም ‘የበታች ህጎች’ በተግባር ግን ‘የበላይ ህጎች’ መሆናቸው አይቀርም፡፡

 4. የባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ አባልነት

በሰ/መ/ቁ. 44226 (አመልካች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ተጠሪዎች እነ ህብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ /3 ሰዎች/ ታህሳስ 15 2003 .. ቅጽ 11) የአመልካች መመሪያ ከፊል ድንጋጌዎች ስልጣን የሰጠውን አዋጅ ስለሚቃረኑ ተፈጻሚነት እንዳይኖራቸው በተጠሪዎች ክስ ቀርቦ በፌደራል መጀመሪያ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲሻሩ ተወስኗል፡፡ ተቃውሞ የቀረበበት መመሪያ እ.ኤ.አ. 2006 ዓ.ም. የወጣው Directive No. SBB/39/2006 Licensing and Supervision of Banking Business፡ Amendment for New Bank Licensing and Approval of Directors and CEO ሲሆን የባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ አባል በተመሳሳይ ጊዜ በሌላ የገንዘብ ተቋም የቦርድ አባል ሆኖ እንዳያገለግል፣ 75 ፐርሰንት አባላት የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲኖራቸው እንዲሁም በድጋሚ መመረጥ እንዳይችሉ የተለያዩ ገደቦችን ይጥላል፡፡ ባንኩ መመሪያውን ያወጣው በጊዜው ጸንተው በነበሩት የገንዘብና ባንክ አዋጅ ቁ. 83/1986 አንቀጽ 41 እና የባንክ ስራ ፈቃድና ቁጥጥር አዋጅ ቁ. 84/1986 አንቀጽ 36 እንደሆነ በመመሪያ መግቢያ ላይ ተገልጿል፡፡

ጉዳዩ በሰበር ሲታይ ባንኩ መመሪያውን ለማውጣት ስልጣን እንዳለው በተደረሰበት ድምዳሜ መሰረት የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔዎች ተሽረዋል፡፡ ሆኖም ለስልጣኑ ምንጭ ችሎቱ የጠቀሳቸው ድንጋጌዎች ባንኩ ራሱ በመመሪያው ላይ ካሰፈራቸው ይለያሉ፡፡ ችሎቱ ለህግ ትርጉሙ ድጋፍ ያደረገው የባንኩን የመቆጣጠር ስልጣን እና በሁለቱም አዋጆች በጥቅል የተነገው ባንኩ አዋጆቹን ለማስፈጸም የተሰጠው መመሪያ የማውጣት ስልጣን ነው፡፡

የማስፈጸም ዓለማ ያለው መመሪያ በሚያስፈጽመው አዋጅ ላይ ከተደነገጉ ጉዳዮች በላይ አልፎ ሊሄድ አይችልም፡፡ የመቆጣጠር ስልጣን እንዲሁ በህጉ ከተዘረጋው የቁጥጥር ማዕቀፍ ሊያፈነግጥ አይገባም፡፡ የመቆጣጠርና የማስፈጸም ስልጣን ብቻውን መመሪያውን ህጋዊ የሚያደርገው ከሆነ በባንኩ መመሪያ የማውጣት ስልጣን ላይ ምንም ዓይነት ገደብ ማስቀመጥ አይታሰብም፡፡ በዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ላይ የሚደረጉ ገደቦችን በመመሪያ ለመወሰን መጀመሪያ ዋናው ህግ መሰረታዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ሊደነግግ ይገባል፡፡ የሰበር ችሎት ያንጸባረቀው አቋም ማናቸውንም የባንኩን መመሪያዎች ህጋዊነት ያለጥያቄ አስቀድሞ የማጽደቅ ያክል ነው፡፡

[1] በትምህርት ተቋማት የአምልኮ ስርዓትን በሚመለከት የወጣ መመሪያ፡ የትምህርት ሚኒስቴር ህዳር 2000 ዓ.ም.

[2] የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ስራ አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁ. 916/2008

[3] የኢትዮዽያ ፌደራላዊ ዲሞከራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁ. 691/2003

የጠ/ሚኒስቴር ጽ/ቤት፡ የስልጣን ምንጭ እና ህጋዊነት

ከ10 ዓመት በላይ ማንሳትና መጣል በኋላ ‘የአስተዳደር ህግ መግቢያ’ የሚለው መጽሀፌ እነሆ 2010 ላይ ሲጠናቀቅ ትልቅ እፎይታ ተሰምቶኛል፡፡ የህትመት ነገር ከተሳካ በቅርቡ ገበያ ላይ ይውላል፡፡ የሚከተለው ጽሁፍ የተወሰደው ከመጽሐፉ ረቂቅ ላይ ነው፡፡

የጠ/ሚኒስቴር ጽ/ቤት፡ የስልጣን ምንጭ እና ህጋዊነት

በተለምዶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት (አንዳንዴ ቢሮ) እየተባለ የሚታወቀው አካል ስልጣንና ተግባሩ በህግ ተወስኖ አልተቋቋመም፡፡ በአቋሙ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል ቢሮ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገ መንግስቱ የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት በአግባቡ እንዲያከናውን ለማገዝ የሚረዱ የቢሮ ስራዎችን ከማከናወን በስተቀር በማናቸውም መንግስታዊ ሆነ አስተዳደራዊ ጉዳዮች የመወሰን ሆነ ለበታች አካላት መመሪያ የማስተላለፍ ስልጣን የለውም፡፡

ጽ/ቤቱ በታሪካዊ አቋሙ ከነበረው የቆየ ስም እንዲሁም የደርግ መውደቅን ተከትሎ በሽግግሩ መንግስት ጊዜ በዘልማድ በሚያከናውናቸው መንግስታዊ ተግባራት (በተለይ ቅሬታ ሰሚ በመሆን) የተነሳ በህግ ሳይሆን በዕውቅና (de facto) ህልውና ያገኘ የመንግስት ተቋም ለመሆን በቅቷል፡፡

በሰ/መ/ቁ. 16195[1] ተጠሪዎች በመንግስት ለተወረሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው አበል እንዲከፈላቸው የሥራና ከተማ ልማት ሚ/ር በወሰነላቸው መሰረት ይከፈላቸው ዘንድ በአመልካች ላይ ክስ አቀረቡ፡፡ ከክርክሩ በኋላ ክሱ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ ያለው አበል እንዲከፈላቸው ተፈረደላቸው፡፡ ፍርዱም በከፍተኛው ፍ/ቤት ፀና፡፡ ሆኖም የሰበር ችሎት ሻረው፡፡ በመዝገቡ ላይ የሥራና ከተማ ልማት ሚ/ር ውሳኔ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ እንደተሻረ ተመልክቷል፡፡ በዚህ መልክ መሻሩ ለስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ለመሻር ምክንያት ሆኗል፡፡ ችሎቱ ህገ መንግስቱን በማጣቀስ ለማብራራት እንደሞከረው፤

[በኢ.ፌ.ዲ.ሪ.] ህገ-መንግስት አንቀጽ 74/4/ ሁሉም ሚኒስቴሮች የሚገኙበትን የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚመራ፣ እንደሚያስተባብርና እንደሚወክል ተመልክቷል፡፡ እንዲሁም…የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አ/ቁ 4/87 አንቀጽ 11/1/ ሥር እያንዳንዱ ሚኒስትር፣ የሚመራውን ሚኒስቴር መ/ቤት የሚመለከቱ ሥራዎች ፕሮግራሞችና ህጎች አፈፃፀም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከነዚህ ህጎች አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስቴር መ/ቤቶችን በበላይነት የመምራትና ስራቸውንም የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም ሚኒስቴር መ/ቤቶቹ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የፈፀሙትን ስህተት ማረምና ማስተካከል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ስር የሚወድቅ ነው፡፡

የሥራና ከተማ ልማት ሚ/ር ውሳኔን የሻረው ጽ/ቤቱ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይደለም፡፡ ሆኖም የሰበር ችሎት የውሳኔውን ህጋዊነት ያጣራው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህገ መንግስታዊ ስልጣን በማመሳከር ነው፡፡ ሁለቱ እንደ አንድ አምሳል፣ አንድ አካል ተቆጥረዋል፡፡ ይህ የማደባላለቅ ስህተት በሌሎች የህግ ባለሞያዎች ላይም ይታይል፡፡ በቅርቡ የጠቅላይ ዓቃቤ ባጠናቀረው የተጠቃለሉ ህጎች ማውጫ ላይ ‘ለጠ/ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ አካላትን ማቋቋሚያ ህጎች’ የሚል ርዕስ እናገኛለን፡፡

ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር የግል ቢሮ ነው፡፡ የግል የሆነበት ምክንያት እንደ አገሪቱ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት በህግ አልተቋቋመም፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 131/1991 ጽ/ቤቱን ህጋዊ ሰውነት አላብሶ አቋቁሞታል፡፡ ለጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ግን ተመሳሳይ የህግ መሰረት የለም፡፡ በስልጣኑ ላይ የሚነሳው ህጋዊና ህገ መንግስታዊ ጥያቄ የማቋቋሚያ አዋጅ አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ ከጊዜ በኋላ ጽ/ቤቱን የሚያቋቁም አዋጅ ቢወጣም እንኳን ከጽህፈት ስራ የዘለለ በማናቸውም መንግስታዊ ጉዳዮች ውሳኔ የማስተላለፍ ሚናና ተግባር ሊኖረው አይችልም፡፡

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከህገ መንግስቱ የሚመነጩት ስልጣናት ከእርሱ በቀር ወደ ሌላ አይተላለፉም፡፡ ከምክትል ጠ/ሚኒስትሩ በቀር ሚስት/ባል፣ ልጅ፣ ወላጅ፣ ጽ/ቤት ሆነ ሌላ ማናቸውም አካል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን መጋራት አልተፈቀደላቸውም፡፡ በህግ የተቋቋመ የሚኒስቴር መ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ጽ/ቤቱ መሻር ይችላል ማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ ተመሳሳይ የመሻር ስልጣን አለው የማለት ያክል ነው፡፡

የሰበር ችሎት ይህን ግዙፍ ህገ መንግስታዊ ስህተት በሰ/መ/ቁ. 34665[2] ላይም ደግሞታል፡፡ በመዝገቡ ላይ የተነሳው የህግ ጥያቄ የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት (ደብተር) የመሰረዝ ስልጣን ህጋዊነት ሲሆን የፍሬ ነገሩ መነሻ ታሪክ አስደማሚና አስገራሚ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በወቅቱ ማለትም በ1991 ዓ.ም. ላይ የስራና ከተማ ልማት ሚ/ር በመስሪያ ቤቱ ይገኙ የነበሩ የቤት ጉዳዮችን ከሰራተኞቹ ጋር ለአዲስ አበባ መስተዲድር ምክር ቤት ስራና ከተማ ልማት ቢሮ እንዲያስረክብ ከጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት ትእዛዝ ደረሰው፡፡ በትዕዛዙ መሰረት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጉዳዮቹንና ሰራተኞቹን አስረከበ፡፡ የአ/አበባ መስተዳድ ቤት ስራና ከተማ ልማት ቢሮ ከየካቲት 1 ቀን 1991 ዓ.ም ጀምሮ የቤት ጉዳዮቹን ተረክቦ ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ቢሮው በዚህ ሁኔታ የአመልካቾችን ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር በመሰረዙ ምክንያት በስር ፍ/ቤት ክስ አቅርበው ጥያቄያቸው ተቀባይነት አጣ፡፡ ይግባኝ ቢሉም አቤቱታቸው ውደቅ በመደረጉ ጉዳዩ ወደ ሰበር ችሎት አመራ፡፡ አመልካቾች በሰበር ክርክራቸው ደብተሩ ስልጣን በሌለው አካል እንደተሰረዘ በመጥቀስ የቢሮውን ተግባር ህጋዊነት ሞግተዋል፡፡

በህግ የተቋቋ የመንግስት መ/ቤት ስልጣን፣ መብትና ግዴታ ወደ ሌላ የሚተላለፈው ህግ አውጭው አምኖበት በአዋጅ ሲያጸድቀው ብቻ ነው፡፡ አንድ መ/ቤት በበላይ ትዕዛዝ (ያውም በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት) የሚበተን ከሆነ፣ ስልጣኑን ተቀምቶ ወደ ሌላ የሚተላለፍ ከሆነ ያኔ ህጋዊነትና ስርዓት አልበኝነት አንድ ሆነው ተዋህደዋል፡፡ የሰበር ችሎት ይህ አስደንጋጭ እውነት  አልተገለጠለትም፡፡ የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሲያጸና በሰ/መ/ቁ. 16195 ያሰፈረውን (የተሳሳተ) ትንተና በመድገም ነገሩን በአጭሩ ቋጭቶታል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 34665 የተለየ ነጥብ የሚስተዋለው ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጽ/ቤቱ ቦታ ተቀያይረዋል፡፡ ለንፅፅር ይረዳ ዘንድ ሙሉ ዓረፍተ ነገሩ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

የጠቅላይ ሚ/ጽ/ቤት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ስራ የመከታተልና በበላይነት የመቆጣጠር ስልጣን ያለው እንደመሆኑ መጠን የስራና ከተማ ልማት ሚ/ር ቤቶችን የሚመለከት ጉዳይ ለአ/አበባ ስራና ከተማ ልማት ቢሮ እንዲያስተላልፍ በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ስራውንና ሰራተኞቹን ለቢሮው አስተላልፏል፡፡ (ሰረዝ የተጨመረ)

 

[1] አመልካች የኪራይ ቤቶች ድርጅት እና ተጠሪ እነ ልዕልት ተናኘወርቅ ኃ/ስላሴ /6 ሰዎች/ ቅጽ 4 ሚያዝያ 11 ቀን 1999 ዓ.ም.

[2] አመልካች እነ አቶ ናትናኤሌ ዘውገ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ እግዜሩ ገ/ሕይወት /2 ሰዎች/ ሰ/መ/ቁ. 34665 ቅጽ 10 ጥቅምት 12 ቀን 2002 ዓ.ም