Site icon Ethiopian Legal Brief

ቅጣቶች እና የጥንቃቄ እርምጃዎች

. ቅጣቶች እና የጥንቃቄ እርምጃዎች

2.1. የወንጀል ቅጣቶች

ቅጣቶች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ተለይተው ሊታዩ ይችላሉ፣

     1/ ዋና ቅጣቶች፣ እና  2/  ተጨማሪ ቅጣቶች

2.1.1. ዋና ቅጣቶች

በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው ሊጣሉበት የሚችሉ ዋና ቅጣቶች የሚባሉት መቀጮ፣ የግዴታ ሥራ ፣የእስራት ቅጣት እና የሞት ቅጣት ናቸው፡፡

መቀጮ

መቀጮ ወይም የገንዘብ ቅጣት የወንጀል አድራጊውን የገንዘብ ወይም የንብረት ባለቤትነት መብት የሚነካ በፍትሐብሔር ጉዳይ ካለው ኃላፊነት ጋር የሚቀራረብ ቅጣት ነው፡፡ መቀጮ የሚከፈለው በጥሬ ገንዘብ ሲሆን ገቢ የሚደረገውም ለመንግሥት ነው፡፡ የገንዘብ ቅጣት በወንጀል የደረሰ ጉዳትን የማስተካከል ዓላማ የለውም፣ መጠኑም የሚለካው ከደረሰው ጉዳት አንጻር አይደለም፡፡ የሚለካው ከተፈፀመው ወንጀል ከባድነትና ከተቀጭው የመክፈል አቅም አንጻር ነው፡፡

መቀጮ ለብቻው ወይም ከሌሎች ቅጣቶች ጋር ሊወሰን ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ ሕጉ መቀጮን ከቀላል እስራት ጋር በአማራጭ የሚደነገግ ሲሆን በሕጉ ልዩ ክፍል የሚገኙ አንቀጾች በግልፅ ባይደነግጉም መቀጮ የእስራት አማራጭ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ ፍርድ ቤቱ አስፈላጊነቱን ካመነበት ሁለቱንም ዓይነት ቅጣት አጣምሮ መወሰን ይችላል (አንቀጽ 91)፡፡ አንዳንድ ጊዜ የመቀጮው ቅጣት የታች ወይም የላይ ወሰን በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል አንቀጾች ሊገለፅ የሚችል ሲሆን አንዳንድ ጊዜም የቅጣቱ ወሰን ሳይገለፅ ቅጣቱ መቀጮ መሆኑ ብቻ ይጠቀሳል፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት የመቀጮ ቅጣቱ መነሻ አንድ ብር የላይ ጣራው ደግሞ አምስት ሺህ ብር ነበር (ቁጥር 88)፡፡

       በአዲሱ የወንጀል ሕግ መሠረት ግን ጥፋተኛው ግለሰብ ሲሆን እና የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ሲሆን መቀጮው የተለያየ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በአዲሱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 34 መሠረት በሕግ የሰውነት መብት ያላቸው ድርጅቶች (የመንግስት አስተዳዳር አካላትን ሳይጨምር) ወንጀል ፈፅመው በተገኙ ጊዜ በወንጀል ይጠየቃሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ድርጅቶች የሚጣልባቸው ቅጣት በተፈጥሮ ሰው ላይ ከሚጣለው ቅጣት በተለዬ በመቀጮ ብቻ ነው፡፡

      በዚህም መሰረት ጥፋተኛው ግለሰብ ከሆነ ከአስር ብር እስከ አስር ሺህ ብር ሊቀጣ የሚችል ሲሆን፣ ጥፋተኛው የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ሲሆን ደግሞ የሚወሰንበት የገንዘብ ቅጣት ከአንድ መቶ ብር አስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ሊደርስ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

የወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል የእስራትን ቅጣት አስቀምጦ መቀጮን በአማራጭ በሚደነግግበትና ተቀጪው የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በሚሆንበት ጊዜ እስራት ወደ መቀጮ የሚለወጥበትን ሁኔታ የሚያመለክት አዲስ ድንጋጌም ተጨምሯል (አንቀጽ 9ዐ(3))፡፡ በዚህ መሠረት እስከ አምስት ዓመት ቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ አስር ሺህ ብር፣ እስከ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ሃያ ሺህ ብር፣ ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ሃምሳ ሺህ ብር፣ ከአስር ዓመት በላይ ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል በሕግ የሰውነት በተሰጠው ድርጅት ላይ የሚወሰነው የገንዘብ ቅጣት እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲሆን ተደርጓል፡፡

      እንዲሁም ወንጀልን በሚያቋቁመው የወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል ውስጥ መቀጮ ብቻ በተደነገገ ጊዜ እና ተቀጪው የሕግ ሰውነት ያለው አካል በሆነ ጊዜ ፍርድ ቤቱ የቅጣቱን መጠን የሚወስነው ለተፈጥሮው ሰው ከተቀመጠው ቅጣት አምስት እጥፍ በማድረግ ስለመሆኑ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ተደንግጓል፡፡

         የተፈጥሮ ሰውን በተመለከተ ወንጀሉ የተፈፀመው በአፍቅሮ ንዋይ የሆነ እንደሆነ ቅጣቱ እስከ 1ዐ ሺህ ብር ሊደርስ ይችላል ተብሎ በቀድሞው ሕግ ላይ ተደንግጎ የነበረው (ቁጥር 90) በአዲሱ የወንጀል ሕግ ቅጣቱ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ሊደርስ ይችላል ተብሎ ተሻሽሏል (አንቀጽ 92)፡፡

በመሠረቱ የገንዘብ ቅጣት ወዲያውኑ መከፈል ይኖርበታል፡፡ተቀጭው ገንዘቡን ወዲያው መክፈል ባይችል በቀድሞው ሕግ ከአንድ አስከ ሦስት ወር የመክፈያ ጊዜ ሊፈቀድለት ይችል የነበረ ሲሆን (ቁጥር 91(1))፣ በአዲሱ የወንጀል ሕግ የመቀጮው የመክፈያ ጣራ ወደ ስድስት ወር ከፍ እንዲል ተደርጓል(አንቀጽ 93(2))፡፡ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተቀጭው መቀጮውን በየጊዜው እየከፈለ እንዲጨርስ ፍርድ ቤቱ በቀድሞው ሕግ ከሁለት ዓመት ላልበለጠ የመክፈያ ጊዜ ሊሰጠው ይችል የነበረ ሲሆን(ቁጥር 91(1))፣ በአዲሱ የወንጀል ሕግ ይህ ለተቀጪው የሚሰጠው የመክፈያ ጊዜ ወደ ሶስት ዓመት ከፍ እንዲል ተደርጓል (አንቀጽ 93(2))፡፡

በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንድ ጥፋተኛ የተወሰነበትን መቀጮ መክፈል ካልቻለ ወደ እስራት እንደሚለወጥ ይደነግግ የነበረው /ቁጥር 94/ ተሠርዟል፡፡ ለመሠረዙ በምክንያትነት የተሰጠው ድሀውን ወገን የሚጐዳ የቅጣት አፈፃፀም በመሆኑ ፍትሐዊ አይደለም የሚል ነው፡፡[1]

2.1.1.2. የግዴታ ሥራ

የግዴታ ሥራ በወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ሰው ሰርቶ የሚያገኘውን ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ የሚያደርግበትን ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን ጥፋተኛው የፈፀመው ወንጀል የሚያስከትለው ቅጣት ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት የሆነ እንደሆነና ጥፋተኛውም ለህብረተሰቡ አደገኛነት የሌለው መሆኑ ከታመነበት ፍርድ ቤቱ በእስራቱ ምትክ ከአንድ ቀን እስከ ስድስት ወር ለሚደርስ ጊዜ ወንጀለኛው የግዴታ ሥራ እንዲሰራ ለመወሰን ይችላል (አንቀጽ 103)፡፡[2] በዚህም መሠረት እስራት ወደ ግዴታ ሥራ እንዲለወጥለት አንድ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው በይገባኛል የሚጠይቀው ጉዳይ ሳይሆን ፍርድ ቤቱ በሕግ የተቀመጠውን መመዘኛ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደ አግባብነቱ እስራቱ ወደ ግዴታ ሥራ እንዲለወጥ ወይም እስራቱ እንዲፈፀም የሚያደርግበት ነው፡፡

የግዴታ ሥራ የነገሩ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት የተቀጪውን ነጻነት ከመገደብ ጋር እንዲፈፀም ፍርድ ቤቱ ሊወስን የሚችል ሲሆን በተለይም ደግሞ ተቀጪው ነጻነቱ ሳይገደብ የግዴታ ስራ እንዲሰራ ቅጣት ተወስኖበት ይህን የተወሰነበትን ቅጣት በአግባቡ ሳይወጣ ከቀረ ተቀጪው ከአንድ የስራ ቦታ፣ ከአንድ አሰሪ ዘንድ፣ ከአንድ የስራ ተቋም ሳይለቅ ወይም ከመኖሪያ ሥፍራው ሳይወጣ ወይም በመንግሥት ባለሥልጣኖች ከሚጠበቅ ከአንድ የተወሰነ ሥፍራ ሳይለይ የግዴታ ሥራውን እንዲያከናውን ፍርድ ቤቱ ሊያደርግ ይችላል፡፡

በእስራት ምትክ በግዴታ ሥራ ጥፋተኛው እንዲቀጣ በፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ ከተቀጪው ገቢ ላይ እየተቀነሰ ለመንግሥት ገቢ የሚሆነውን የገንዘብ ልክ፣ የግዴታ ሥራው የሚፈፀምበትን ሥፍራ፣ ቅጣቱ የሚቆይበትን ጊዜ እንዲሁም በተቀጪው ላይ የሚደረገውን የቁጥጥር ዓይነት ማመልከት ያለበት ሲሆን ለመንግስት ገቢ እንዲሆን የሚወሰነው መጠን ከተቀጪው የድካም ዋጋ ወይም በሥራ ፍሬው ከሚያገኘው ጥቅም ከአንድ ሦስተኛ መብለጥ አይችልም፡፡ የቀድሞው ሕግ የሚከለክለው ተቀናሽ እተደረገ ለመንግስት ገቢ የሚሆነው መጠን ተቀጪው በሚሰራው ሥራ ከሚያገኘው ገቢ ከአንድ አራተኛ እንዳይበልጥ ነበር (ቁጥር 102(2))፡፡   

በእስራት ምትክ በግዴታ ሥራ እንዲቀጣ የተወሰነበት ወንጀለኛ በፍርድ ቤቱ የተጣለበትን ውሳኔ የጣሰ ወይም በውሳኔው መሠረት ለመፈፀም ፈቃደኛ ሳይሆን የቀረ እንደሆነ ሳይፈፀም የቀረው የግዴታ ሥራ ወደ ቀላል እስራት ተለውጦ ቅጣቱን እንዲፈፅም ይደረጋል (አንቀጽ 104(2))፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ ከተወሰነበት የግዴታ ሥራ ዘመን ውስጥ ግማሹን በትክክል ፈፅሞ ከሆነ ይኸው ተይዞለት ላልፈፀመው የግዴታ ሥራ ዘመን ብቻ የቀላል እስራት ቅጣት ይጣልበታል ማለት ነው፡፡

 በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 96 ድንጋጌ መሠረት አንድ ጥፋተኛ የተወሰነበትን መቀጮ መክፈል ካልቻለ ወደ እስራት የሚለወጥ ሲሆን ነገር ግን ጥፋቱ ቀላል ከሆነ የግዴታ ሥራ እንዲሠራ ሊወሰንበት ይችላል፡፡ በአዲሱ የወንጀል ሕግ መሠረት ግን ጥፋቱ ቀላልም ይሁን ከበድ ያለ፣ የመቀጮው መጠን አነስተኛም ይሁን ከፍ ያለ የተወሰነበትን መቀጮ መክፈል ያቃተው ሰው የግዴታ ሥራ ሊፈረድበት ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተቀጭው ለምን ያህል ጊዜ የግዴታ ሥራውን ሊሠራ እንደሚባው መግለፅ ያለበት ሲሆን የሚወሰነው ጊዜ በአዲሱ ሕግ መሰረት ከሁለት ዓመት ሊበልጥ አይችልም፡፡ በቀድሞው ሕግ ግን እንዲህ ዓይነት ገደብ አልተቀመጠም ነበር፡፡ በአዲሱ የወንጀል ሕግ ላይ የጊዜ ገደብ እንዲቀመጥ የተደረገው የጥፋተኛው ጉልበት ወይም አዕምሮ ለረጅም ጊዜ ያለአግባብ እንዳይበዘበዝ ለማድረግ እንዲሁም የተለያዬ የገንዘብ ማግኘት አቅም ባላቸው ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት የተቻለውን ያህል ለመቅረፍ ታቅዶ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡[3]

2.1.1.3. የእስራት ቅጣት

 እስራት በሦስት ይከፈላል፡፡ እነርሱም ፅኑ እስራት፣ ቀላል እስራት እና የማረፊያ ቤት እስራት ናቸው፡፡ የማረፊያ ቤት እስራት ደንብ ተላልፈው የተገኙ ሰዎች ሊጣልባቸው የሚችለው ዓይነት እስራት ነው፡፡ ይህ የእስራት ዓይነት በማረሚያ ቤት ሊፈፀም የማይችል ሲሆን ጠቅላላ አፈጻፀሙም ወንጀል ፈፅመው በእስራት እንዲቀጡ ከተፈረደባቸው ሰዎች የቅጣት አፈጻጸም የተለዬ ነው፡፡ ቀጥለን የምናያቸው ወንጀል አድራጊዎች መደበኛውን የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ጥሰው በመገኘታቸው ምክንያት እንደ አግባብነቱ ሊወሰኑ የሚችሉትን ቀላል ወይም የፅኑ እስራት ቅጣቶች ይሆናል፡፡

(ሀ) ቀላል እስራት

     ከባድነታቸው መካከለኛ ለሆኑ ወንጀሎችና ለሕብረተሰቡ አደገኛ ላልሆኑ ወንጀሎች የተደነገገ የቅጣት ዓይነት ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል የላይ እስራቱን የታች ወይም የላይ ወሰን በግልፅ የሚደነግግበት ጊዜ ያለ ሲሆን ይህ የማይሆንበት ሁኔታም አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የቀላል እስራት ቅጣቱ የታች ወይም የላይ ወሰን በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል አንቀጾች ሊገለፅ የሚችል ሲሆን አንዳንድ ጊዜም የቅጣቱ ወሰን ሳይገለፅ ቅጣቱ ቀላል እስራት መሆኑ ብቻ ይጠቀሳል፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግም ሆነ በአዲሱ የወንጀል ሕግ የቀላል እስራት ቅጣቱ መነሻ አስር ቀን የላይ ጣራው ደግሞ እስከ ሦስት ዓመ ይደርሳል፡፡ ምንም እንኳን በመርህ ደረጃ የቀላል እስራት ጊዜ ከአስር ቀን እስከ ሦስት ዓመት ቢሆነም በተለዩ ምክንያቶች የቀላል እስራት እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ እንደሚችል ተመልክቷል(አንቀጽ 1ዐ6(1))፡፡ እነዚህም ምክንያቶች፡-

  1. ከወንጀሉ ከባድነት የተነሳ በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል ተደንግጐ ሲገኝ ቀላል እስራት ከሶስት ዓመት ገደብ አልፎ እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ አንቀጽ 541ን ብንመለከት የአስገዳጅ ሁኔታን ወሰን በመተላለፍ ወይም ህጋዊ መከላከልን ከመጠን በማሳለፍ አንድ ሰው “ቀላል የሆነ የሰው ግድያ” የፈፀመ እንደሆነ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል ፡፡

 በቀድሞው ሕግም ቢሆን የግልፅነት ችግር ቢኖረውም “በሕጉ የተለዬ ድንጋጌ ከሌለ በቀር” የቀላል አስራት ቅጣት ከአስር ቀን እስከ ሦስት ዓመት እንደሚደርስ ተመልክቶ ነበር (ቁጥር 105)፡፡ ይህም የሚያሳየው ሕጉ በተለዬ በሚደነግግበት ጊዜ የቀላል እስራት ቅጣት ከሦስት ዓመት አይበልጥም በሚለው በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል ለእስራቱ ዓይነት በተደነገገው የቀላል እስራት የላይ ጣራ የማይገደብ መሆኑን ነው፡፡

ከቀላል እስራት ጋር በተያያዘ ሌላው ሊነሳ የሚገባው ነጥብ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ እስከ ሦስት ወር የሚደርስ የቀላል እስራት ቅጣት በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል ድንጋጌዎች ላይ ተመልክቶ በሚያጋጥምበት ጊዜ ሁሉ በቀላል እስራቱ ምትክ ፍርድ ቤቱ የግዴታ ሥራን መወሰን እንደሚችል ተመልክቶ የነበረ ሲሆን (ቁጥር 1ዐ6) በአዲሱ የወንጀል ሕግ እስከ ስድስት ወር የሚደርስ የቀላል እስራት ቅጣት በግዴታ ሥራ ሊተካ እንደሚችል ተመልክቷል (አንቀጽ 1ዐ7)፡፡

(ለ) ፅኑ እሥራት

ፅኑ እስራት ለከባድ ወንጀሎችና ለሕብረተሰቡ አደገኛ በሆኑ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰን የቅጣት ዓይነት ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል የእስራቱን ጣራ ወይም የእስራቱን የታች ወለል ወይም ሁለቱንም በግልፅ የሚደነግግበት ጊዜ ያለ ሲሆን ይህ የማይሆንበት ሁኔታም አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የፅኑ እስራት ቅጣቱ የታች ወይም የላይ ወሰን በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል አንቀጾች ሊገለፅ የሚችል ሲሆን አንዳንድ ጊዜም የቅጣቱ ወሰን ሳይገለፅ ቅጣቱ የፅኑ እስራት መሆኑ ብቻ ይጠቀሳል፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግም ሆነ በአዲሱ የወንጀል ሕግ የፅኑ እስራት ቅጣቱ መነሻ አንድ ዓመት የላይ ጣራው ደግሞ እስከ ሀያ አምስት ዓመ ይደርሳል፡፡ ሆኖም በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል በግልፅ ተደንግጎ በተገኘ ጊዜ የፅኑ እስራት ዘመን እስከ ወንጀለኛው የዕድሜ ፍፃሜ ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡ የዕድሜ ልክ እስራት ርዝመቱ አይታወቅም፡፡ እስረኛው በአመክሮ ካልተለቀቀ በቀር አርባ ወይም ሀምሳ አመት ታስሮ ሊቆይ የሚችለበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

በፅኑ እስራት የተቀጣ ወንጀለኛ አደገኛ ነው ተብሎ ስለሚገመት እስራቱ በተለይ በመጨቆንና በመጠበቅ ይፈፀማል በማለት የቀድሞው ሕግ ይደግግ የነበረ ሲሆን (ቁጥር 1ዐ7(1)) አዲሱ ሕግ ደግሞ የፅኑ አስራት ቅጣት የአፈፃፀም ሁኔታ ከቀላል እስራት የአፈፃፀም ሁኔታ በይበልጥ ይከብዳል በማለት ደንግጓል (አንቀጽ 1ዐ8(2))፡፡ በዚህም መሠረት በቀላል እስራት የተቀጣ ሰው በፅኑ እስራት ከተቀጣ ወንጀለኛ የተሻለ የመንቀሳቀስና ሌሎች መብቶች ባለበት ሁኔታ የተፈረደበትን እስራት እንዲፈፅም ይደረጋል ወይም ሊደረግ ይገባል፡፡

በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ቀላል እስራት የሚፈፀመው በእስር ቤቶች፣ ፅኑ እስራት የሚፈፀመው ደግሞ በወህኒ ቤቶች ስለመሆኑ ተመልክቶ የሚገኝ ሲሆን (ቁጥር 1ዐ5(2) እና ቁጥር 1ዐ7(2))፤ አዲሱ ሕግ ደግሞ እስረኞቹ በተለያዬ ሥፍራ መታሰር ያለባቸው መሆኑና በእስራቱ አፈጻጸም ላይ ልዩነት ያለ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀላልም ሆነ ፅኑ እስራት የተወሰነባቸው ወንጀለኞች ቅጣታቸውን የሚፈፅሙት ለዚሁ ሥራ በተሰናዱ ማረሚያ ቤቶች ስለመሆኑ ደንግጓል (አንቀጽ 106(2) እና አንቀጽ 108(2))፡፡

በቀላልም ሆነ በፅኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ወንጀለኞች የመስራት ግዴታ አለባቸው፡፡ በዚህም መሠረት ሥራ የየትኛውም ዓይነት የእስራት ቅጣት አፈጻጸም አካል ነው፡፡

 የታመመ እስረኛ ወደ ሀኪም ቤት ሲገባ ሆስፒታል የቆየበትን ጊዜ መቁጠርን በተመለከተ በቀድሞው ሕግ ቁጥር 115(1) ላይ እስረኛው በሀኪም ቤት ገብቶ የታከመው ከመታሰሩ በፊት በደረሰበት ህመም ወይም ሌላ ምክንያት ከሆነ ይህ ጊዜ ከእስራቱ ዘመን ውስጥ ላይታሰብለት እንደሚችል የሚደነግግ ሲሆን አዲሱ የወንጀል ሕግ ግን ህመሙ የደረሰበት በእራሱ ጥፋት እስካልሆነድረስ በሀኪም ቤት የቆየበት ጊዜ በሙሉ ከሚፈፅመው ቅጣት ጋር ሊታሰብለት ይገባል ይላል (አንቀጽ 116(1))፡፡

2.1.1.4. የሞት ቅጣት

የሞት ቅጣት የሰውን ህይወት የሚያሳጣ ፍርድ ነው፡፡ የሞት ፍርድ በአጠቃላይ በተለዬ ሁኔታ ከባድ ተብለው ለሚገመቱ ወንጀሎች የሚደነገግ የቅጣት ዓይነት ነው፡፡ የሞት ቅጣት ብቸኛ ቅጣት እንዲሆን በሕጉ ልዩ ክፍል ውስጥ ወንጀሉ በሞት ሊያስቀጣ የሚችል ስለመሆኑ ተደንግጎ መገኘት ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ የተለዩ ማክበጃ ምክንያቶች ተሟልተው መገኘት ያለባቸው ስለመሆኑ በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል ላይ ተመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት የሞት ቅጣት የሚወሰነው፡-[4]

በድሮው ዘመን የሞት ቅጣት በጎራዴ ጭንቅላትን በመቅላት፣ ብረት ላይ ወይም እንጨት ላይ አጋድሞ በመጋዝ በመቁረጥ፣ ከግንድ ጋር አስሮ በእሳት በማቃጠል፣ አንድን ሰው ከነሕይወቱ በመቅበር፣ በርሀብ ተሰቃይቶ እንዲሞት ጉድጓድ ውስጥ በመጣል እና በመሳሰሉት አሰቃቂ መንገዶች ይፈፀም እንደነበር ይነገራል፡፡[5] የሞት ቅጣትን አፈጻጸም በተመለከተ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 116 የሞት ቅጣት ያለአንዳች ጭካኔ፣ የአካል መቆራረጥ ወይም ሌላ ዓይነት የአካል ጉዳት መፈፀም አለበት ይላል፡፡ በሌላ በኩል ግን የሞት ቅጣት በሕዝብ ፊት ወይም በአደባባይ በስቅላት እንደሚፈፀም ይደነግግ ነበር፡፡

       አዲሱ የወንጀል ሕግ ግን ከቀድሞው ሕግ በተቃራኒ የሞት ቅጣት በሕዝብ ፊት፣ በአደባባይ በስቅላት ወይም በሌላ ኢሰብአዊ በሆኑ ዘዴዎች መፈፀም እንደሌለበት ደንግጓል(አንቀጽ 117(3))፡፡ የአፈፃፀም ዘዴው ግን ጉዳዩ በሚመለከተው የፌዴራል ወይም የክልል ማረሚያ ቤት የበላይ ሕግ አስፈፃሚ አካል እንዲወሰን ተደርጓል፡፡ ይህም የሆነው ጉዳዩ የሚመለከተው የማረሚያ ቤቶች የበላይ ሕግ አስፈፃሚ አካል በየአካባቢው ባሉት ሁኔታዎች መሠረት አቅም በፈቀደ መጠን ሰብአዊ በሆነ መንገድ የሞት ፍርድ የሚፈፀምበትን ዘዴ እንዲወስን ለማስቻል ታስቦ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡[6] 

       የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሰው በፍፁም ኢ-ኃላፊነት ወይም ከፊል ኃላፊነት ላይ የሚገኝ ከሆነ የአዕምሮ ሁኔታው እስኪስተካከል ማለትም የማመዛዘን ችሎታው እስኪመለስ ድረስ፣ በፅኑ የታመመ ሰው ከሆነ ሕመሙ እስኪሻለው (እስኪፈወስ) ድረስ፣ ያረገዘች ሴት ከሆነች እስክትወልድ ድረስ አፈጻጸሙ ታግዶ ይቆያል፡፡

       እንዲሁም የሞት ቅጣት ሊለወጥ የሚችላባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይኸውም ያረገዘች ሴት በእርግዝናዋ ወቅት ፍርዱ ሳይፈፀም ታግዶ የሚቆይ ብቻ ሳይሆን ህይወት ያለው ልጅ የወለደች እንደሆነና ልጁን መመገብና ማሳደግ የሚኖርባት የሆነ እንደሆነ ቀደም ሲል ተፈርዶባት የነበረው የሞት ቅጣት ወደ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ይቀየርላታል፡፡ ከዚህ በተለዬ ደግሞ የሞት ፍርድ በሚመለከተው አካል በሚሰጥ ይቅርታ ቅጣቱ ሊለወጥ ወይም ሙሉ በሙሉ ቀሪ ሊሆን የሚችል ሲሆን እንዲሁም ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ሰው በመንግስት የተሰጠ ምህረት ተጠቃሚ ከሆነ ቅጣቱ ሊቀርለትና ጥፋተኛ የተባለበትን ወንጀል ጭራሽ እንዳልፈፀመ ሊቆጠር ይችላል፡፡

2.1.2. ተጨማሪ ቅጣቶች

ተጨማሪ ቅጣቶች የሚባሉት ማስጠንቀቂያ፣ ወቀሳ፣ ተግሳፅ፣ ጥፋተኛው ተበዳዩን ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ፣ ከመብት መሻር እና ወታደራዊ ማዕረግን መግፈፍ ናቸው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 120 ለአንዳንድ ከባድ ወንጀሎች ግርፋት በተጨማሪ ቅጣትነት ተደንግጐ ነበር፡፡ እንዲሁም ግርፋት በተጨማሪነት ቅጣትነት ሊጣልባቸው የሚችሉ የወንጀል ዓይነቶችን ዝርዝር በድንጋጌ ቁጥር 45/1953 ወጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግርፋት በተግባር ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ተፈጻሚ ሳይደረግ የቆየ የቅጣት ዓይነት ነው፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ የግርፋት ቅጣትን ሰርዞታል፡፡ በወንጀል ሕጉ ሐተታ ዘምክንያት ላይ እንደተመለከተው የግርፋት ቅጣት ከአዲሱ የወንጀል ሕግ እንዲወጣ የተደረገው ተግባሩ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት ላይ የሰፈሩትን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የሚፃረር ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡[7] በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ቅጣት በሕገ መነግስቱ አንቀጽ 18 ላይ “ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው” በሚል የተደነገገውን ክልከላ የሚጥስ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ወይም የተቀበላቻውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና መግለጫዎች የሚጻረር ተግባር ነው፡፡

 በመሠረቱ ተጨማሪ ቅጣቶች ዋና ቅጣቶችን የሚተኩ አይደሉም፡፡ ስለዚህም በተከሳሹ ላይ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ቅጣቶችን ከመወሰኑ በፊት አስቀድሞ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ ለተገኘበት ወንጀል ተገቢ የሆነውን ዋና ቅጣት መወሰን አለበት፡፡

  ምንም እንኳን በመርህ ደረጃ ተጨማሪ ቅጣቶች ዋና ቅጣቶችን የሚተኩ ተደርገው የሚወሰዱ ባይሆንም ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘበት ወንጀል በጣም ቀላል የሆነ ዓይነት ወንጀል ከሆነ ፍርድ ቤቱ ለወንጀሉ የተመለከተውን ዋና ቅጣት በመተው ተግሳፅ፣ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ወይም ጥፋተኛው ይቅርታ ተበዳዩን እንዲጠይቅ በማድረግ ሊያልፈው ይችላል፡፡[8] ይህ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ውስጥ የነበረው አካሄድ በአዲሱ የወንጀል ሕግም የተካተተ ሲሆን ነገር ግን የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ “እጅግ ቀላል የሆኑ ወንጀሎች” የሚባሉት ምን ዓይነት ወንጀሎች ናቸው የሚለውን በሚመለከት በግልጽ ያስቀመጠው መስፈርት አልነበረም፡፡ በመሆኑም ከማስጠንቀቅ ጋር ፍርድ ቤቱ በየትኞቹ የወንጀል ዓይነቶች ጥፋተኛውን በወቀሳ ወይም በተግሳጽ ሊያልፈው እንደሚችል በሕግ ባለሙያዎች መካከል አከራካሪ የሆነ ጉዳይ ነበር፡፡

በአዲሱ የወንጀል ሕግ ግን “በጣም ቀላል የሆኑ ወንጀሎች” የሚባሉት የትኞቹ ዓይነት ወንጀሎች እንደሆኑ በዳኞች እንዲወሰን አልተተወም፡፡ በዚህም መሰረት “በጣም ቀላል የሆኑ ወንጀሎች የሚባሉት ከሦስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጡ ወንጀሎች ናቸው” ተብሎ በአንቀጽ 89 ሁለተኛ ፓራግራፍ ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

አንድ ወንጀል አድራጊ ለፈፀመው ወንጀል ከሚወሰንበት ዋና ቅጣት በተጨማሪ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሌሎች ተደራቢ ቅጣቶችም ሊወሰኑበት ይችላሉ፡፡ ማለትም ለተፈፀመው ወንጀል አግባብነት ያለው ድንጋጌ ላይ ባይመለከትም ፍርድ ቤቶች አስፈላጊ ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሁሉ ተጨማሪ ቅጣቶችን ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ “ፍርድ ቤቶች አስፈላጊ ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሁሉ” ሲባል በዘፈቀደ ዳኞች ተጨማሪ ቅጣቶችን መወሰን ይችላሉ ለማለት አይደለም፡፡ ዳኞች ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ ለተገኘበት ወንጀል ተገቢ የሆነውን ዋና ቅጣት ከወሰኑ በኋላ ተከሳሹ ጥፋተኛ በተባለበት አንቀጽ ላይ ባይመለከትም በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ተጨማሪ ቅጣቶች ሊወሰኑ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎችና መስፈርቶች ግምት ውስጥ በማስገባት “አስፈላጊ ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሁሉ” ከዋናው ቅጣት በተደራቢ ተጨማሪ ቅጣቶችን መወሰን ይችላሉ ለማለት ነው፡፡

 ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ሁሉም የወንጀል ጥፋቶች ተጨማሪ ቅጣቶችን አያስከትሉም፡፡ በተለይም ደግሞ አንድ ጥፋት የመብት መሻር ተጨማሪ ቅጣትን በአጥፊው ላይ ያስከትል እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ፍርድ ቤቱ የሚወስነው የጥፋቱን ዓይነትና ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት አጥፊው በመብቶቹ መገልገሉን ሊቀጥል የሚገባው ሰው መሆን አለመሆኑን በማመዛዘን ነው፡፡ ሆኖም ጥፋተኛው በፈፀመው የወንጀል ተግባር ምክንያት የሞት ወይም የፅኑ እስራት ቅጣት የሚጣልበት ከሆነ ጥፋቱ ከዋና ቅጣቱ በተጨማሪ ከሕዝባዊ መብት መሻር ውሳኔን በግድማስከተል አለበት (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 124(2))፡፡ ሌሎች ዋና ቅጣቶች ግን እንደ ሁኔታው ከሕዝባዊ መብት መሻርን ሊያስከትሉም ላያስከትሉም ይችላሉ፡፡ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የጥፋቱን ዓይነትና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ጥፋቱ እንደ አግባብነቱ የመብት መሻር ሊያስከትል ይገባ ወይም አይገባ እንደሆነ ይወስናል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሚወስነው ተጨማሪ ቅጣት መሠረት ሊሻሩ የሚችሉት የወንጀለኛው ሕዝባዊ መብቶች የሚባሉት በምርጫ በመምረጥ ወይም በመመረጥ ተካፋይ መሆን፣ ለሕዝብ አገልግሎት ወይም ለማዕረግ መመረጥ፣ በሰነድ ወይም የውል ስምምነት ላይ ምስክር ወይም ዋስ መሆን፣ ለፍርድ ሥራ ልዩ አዋቂ ወይም ነባሪ ሆኖ የመስራት መብቶችን ሁሉ የሚመለከት ሲሆን ሌሎች መብቶች ደግሞ አጥፊው ወላጅ በመሆኑ ያለው የወላጅነትና የአስተዳዳሪነት ሥልጣን፣ ሞግዚት የመሆን፣ በሙያው የመሥራት፣ ፈቃድ የሚያስፈልገውን የንግድ ድርጅት ወይም ኢንዱስትሪ አቋቁሞ የመስራት መብቶቹን ሁሉ ያካትታል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 123)፡፡

      ከመብት መሻር ጋር በተያያዘ በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 122(ለ) ላይ ወንጀለኛው በመብቶቹ ሊሠራባቸው ያልተገባ ሰው መሆኑ ሲታወቅ የአባትነት ሥልጣንን ከመያዝ ችሎታው ፍርድ ቤቱ ሊሽረው እንደሚችል ተመልክቶ የነበረ ሲሆን ወንጀለኛ አባት ብቻ ሳይሆን እናትም ልትሆን ስለምትችል በሁለቱም ሁኔታዎች ሊያስኬድ በሚችል አገላለጽ በአዲሱ የወንጀል ሕግ ላይ “የወላጅነት ሥልጣንን ከመያዝ ችሎታው” ተብሎ እንዲሻሻል ተደርጓል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 123(ለ))፡፡

  ማናቸውም ዓይነት ከመብት የመሻር ተጨማሪ ቅጣት ለጊዜው ወይም ለዘወትር ማለትም እስከ ጥፋተኛው በህይወት እስካለ ድረስ እንዲዘልቅ ተደርጎ ሊወሰን የሚችል ሲሆን የሞት ወይም የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ቅጣት ፍርድ የሚያስከትለው ከመብት መሻር ግን ለዘወትር ፀንቶ መቆየት ያለበት ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡[9] ይህ ሲባል ግን ለወንጀለኛው በመንግስት የሚሰጡ የይቅርታ ወይም የምህረት ውሳኔዎች እንዲሁም በፍርድ ቤት በኩል ሊሰጥ የሚችለው የመሰየም ውሳኔ ውጤት በጥፋተኛው ላይ በተሰጡ የመብት መሻር ተጨማሪ ቅጣቶች ላይ የሚኖረው ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡ በዚህም መሰረት በአንድ ጥፋተኛ ላይ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ቅጣት ቢፈረድና በሕጉ መሰረት እንዲህ ዓይነት ቅጣት የሚያስከትለው ከመብት መሻር ለዘወትር እንደሚሆን የተመለከተ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የተቀጪው መብት እስከ መጨረሻው እንዲሻር በተጨማሪ ቅጣትነት ቢወስንም መንግስት ለተቀጪው ይቅርታ ቢሰጠውና ይቅርታው ዋና ቅጣቱን ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ቅጣቶችን ጭምር የሚመለከት ቢሆን “ለዘወትር” ተብሎ በፍርድ ቤቱ የተጣለው ቅጣት ቀሪ ሆኖ ጥፋተኛው በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽረው በነበሩት መብቶች ይቅርታ ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ መጠቀም ይችላል፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይ ጥፋተኛው ላይ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ቅጣት ቢፈረድና በሕጉ መሰረት እንዲህ ዓይነት ቅጣት የሚያስከትለው ከመብት መሻር ለዘወትር እንደሚሆን የተመለከተ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የተቀጪው መብት እስከ መጨረሻው እንዲሻር በተጨማሪ ቅጣትነት ወስኖ እያለ ጥፋተኛው በአመክሮ ከእስር ተፈትቶ በሕጉ የተወሰነው ጊዜ (አምስት ዓመት ካለፈ) እና ሌሎች በሕጉ የተቀመጡትን መስፈርቶችን ካሟላ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሊሰየም የሚችል በመሆኑ  “ለዘወትር” ተብሎ በፍርድ ቤቱ የተጣለው ቅጣት ቀሪ ሆኖ ጥፋተኛው በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽረው በነበሩት መብቶቹ የመሰየም ውሳኔ ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ መጠቀም ይችላል፡፡          ለጊዜው ብቻ ተብለው በፍርድ ቤት በጥፋተኛው ላይ የሚጣሉ ከመብት የመታገድወይም የመከልከል ውሣኔዎች በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 123(1) ከአንድ ዓመት አያንስም ተብሎ የተደነገገው የጊዜ ገደብ በአዲሱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 124(1) ላይ ከስድስት ወር አያንስም በሚል ተተክቷል፡፡በሁለቱም ሕጎች ለጊዜው ብቻ ተብለው በፍርድ ቤት በጥፋተኛው ላይ የሚጣሉ ከመብት የመታገድወይም የመከልከል ውሣኔዎች ከእምስት ዓመት ደግሞ ሊበልጡ አይችሉም፡፡


[1] የወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት፣መስከረም 1998፣ገጽ 56(ያልታተመ)

[2] የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 102 ወደ ግዴታ ሥራ እንዲለወጥ የሚፈቅደው የተፈፀመው ወንጀል የሚያስከትለው ቅጣት ከሦስት ወር ቀላል እስራት የማይበልጥ ከሆነ የነበረ የግዴታ ሥራው ሊቆይ የሚችልበት የጊዜ እርዝማኔም እንዲሁ ከሦስት ወር ሊበልጥ አይችልም ነበር፡፡

[3] የወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት፣መስከረም 1998፣ገጽ 56(ያልታተመ)

[4] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 117፣1997

[5] ፋሲል ናሆም(ዶ/ር)፣ ቅጣትና ኅብረተሰብ፤ዕድገታዊ አመለካከት፣የኢትዮጵያ ሕግ መጽሔት፣ቮልዩም 12፣ 1974፣ ገጽ 16

[6] የወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት፣መስከረም 1998፣ገጽ 68(ያልታተመ)

[7] የወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት፣መስከረም 1998፣ገጽ 71(ያልታተመ)

[8] የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 87፣ 1949፤ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 89፣1997

[9] የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 123(2)፤ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 124(2)

Exit mobile version