Site icon Ethiopian Legal Brief

ተደራራቢ ወንጀሎች እና ቅጣት አወሳሰን

ተደራራቢ ወንጀሎች እና ቅጣት አወሳሰን

     3.2.1. የተደራራቢ ወንጀሎች ምንነት

ተደራራቢ ወንጀሎች (Concurrence offences) በአጠቃላይ በአንድ ሰው ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ወንጀሎች ተፈፅመው ሲገኙ ያለውን ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን ሁለት ወይም ቁጥራቸው ከዚያ በላይ የሆኑ ወንጀሎች ተደራራቢ ናቸው ሊባሉ የሚችሉት ሁለተኛው ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት መጀመሪያ በተፈፀመው ወንጀል ላይ ፍርድ አልተሰጠ እንደሆነ ነው፡፡ የወንጀሎች መደራረብ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡

ግዙፍ የሆነ (ቁሳዊ) መደራረብ

/Material concurrence/-አንድ ሰው ተመሳሳይ ድርጊቶችን በተለያዩ ጊዜያት በመፈጸም እንደ አንድ ወንጀል የማይቆጠሩ ወንጀሎችን ሲፈፅም ወይም ተመሳሳይ ያልሆኑ ማለትም የተለያዩ ድርጊቶችን በተለያዩ ጊዜያት በመፈጸም በተለያዩ የወንጀል ድንጋጌዎች ሥር የሚወድቁ ወንጀሎችን የፈፀመ እንደሆነ ግዙፍ የሆነ (ቁሳዊ) መደራረብ አለ ይባላል፡፡ የእንዲህ ዓይነት ተደራራቢ ወንጀሎች ዓይነተኛ መለያ የድርጊቶች መደጋገም ነው፡፡ የድርጊት መደጋገም እስካለ ድረስ የተፈፀሙት ወንጀሎች ዓይነታቸው አንድ ቢሆንም ወይም ባይሆንም የተደራረቡ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ማለትም እንደ አንድ ወንጀል የማይቆጠሩ ነገር ግን በአንድ አንቀጽ ስር የሚወድቁ በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ተመሳሳይ ድርጊቶችም ቢሆኑ ግዙፍ የሆኑ ተደራራቢ ወንጀሎች ናቸው፡፡

   ለምሳሌ፡- አንድ ሰው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተደብቆ እየገባ የተለያዩ ንብረቶች ቢሰርቅ ወይም ደግሞ ዛሬ ጠዋት አንድ ሰው ቢገድል እና ማታ ላይ ደግሞ አንዲት ሴት አስገድዶ ቢደፍር የወንጀል ድርጊቶቹ ተመሳሳይ ቢሆኑም ባይሆኑም እንደ አንድ ወንጀል ተቆጥረው በአንድ አንቀጽ ብቻ አንድ የወንጀል ክስ የማይቀርብበት እስከሆነ የተደራረቡ ወንጀሎችን ፈጽሟል፡፡ እንዲህ ዓይነት መደራረብ የድርጊትን መደጋገም የሚያመለክት በመሆኑ ግዙፍ የሆነ ወይም ቁሳዊ መደራረብ በመባል ይጠራል፡፡ 

ሐሳባዊ (ጣምራዊ) መደራረብ /Notional concurrence/ – አንድ ሰውበአንድድርጊት ግዙፍነት ያላቸው ወይም የሌላቸው ውጤቶችን በማስከተል ከአንድ በላይ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎችን የጣሰ እንደሆነ ሐሳባዊ መደራረብ አለ ይባላል፡፡ የሐሳባዊ መደራረብ መለያ ባህሪ በአንድ ነጠላ ድርጊት ከአንድ በላይ የሆኑ ወንጀሎች መፈፀማቸው ነው፡፡ በድርጊት ደረጃ የተፈፀመው ተግባር አንድ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የተፈፀመው አንድ ድርጊት ከአንድ በላይ የሆኑ ግዙፍ የሆኑ ውጤቶችን ካስከተለ ወይም ደግሞ ድርጊቱ ከአንድ በላይ የሆኑ ግዙፍ ውጤቶችን ባያስከትልም ከሕግ አንጻር በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የሆኑ የህግ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ተግባር ሆኖ ከተገኘ የተደራረቡ ወንጀሎችን ፈጽሟል፡፡

      ለምሳሌ፡- አንድ ሰው በአንድ ጥይት አስቦ አንድ ሰው ቢገድል እና በዚያው ጥይት ደግሞ ሌላ ሰው ቢያቆስል በድርጊቱ ላደረሰው ሞት በግድያ ወንጀል እና በዚያው ድርጊት ላደረሰው ማቁሰል በመግደል ሙከራ ወንጀሎች ሊጠየቅ የሚችል ሲሆን በዚህም መሰረት የተፈፀመው ድርጊት አንድ ብቻ ቢሆንም ያስከተላቸው ውጤቶች ግን ሁለት የሚታዩ ግዙፍነት ያላቸው ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ባለትዳር የሆነ ሰው አንዲት ሴት አስገድዶ ቢደፍር በአንድ ድርጊት የአመንዝራነት /የሴሰኝነት/ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን ፈፅሟል፡፡ እዚህ ላይ ለማንኛውም ሰው ግልፅ ሆኖ የሚታየው የድርጊቱ ውጤት በሴትዮዋ ላይ በማስገደድ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የተፈፀመባት መሆኑ ነው፡፡ ሌላ የሚታይ ግዙፍ ውጤት የለም፡፡ ሆኖም ከሕግ አንጻር ሲታይ ግለሰቡ በፈፀመው አንድ ድርጊት ከአንድ በላይ የወንጀል ድንጋጌዎችን በመጣስ የተደራረቡ ወንጀሎችን ፈፅሟል፡፡ በዚህም መሠረት በሁለቱም ምሳሌዎች ላይ ከአንድ ድርጊት የተነሳ ከአንድ በላይ ወንጀሎች በመፈፀማቸው የተደጋገመው ድርጊቱ ሳይሆንወንጀሎቹ ናቸው፡፡

3.2.2. ወንጀሎች በተደራራቡ ጊዜ ስለሚኖረው የቅጣት አወሳሰን

3.2.2.1. ለተደራራቢ ወንጀሎች የቅጣት አወሳሰን ዘዴዎች

ከዚህ በላይ ባለው የጽሑፉ ክፍል ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ወንጀሎች ተደራረቡ የሚባለው አንድ ሰው የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን አከታትሎ በመፈፀም ግዙፍነት ያላቸውን የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈፅም ወይም በአንድ ድርጊት ከአንድ በላይ የሆኑ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ ጣምራ ወንጀሎችን ፈፅሞ ሲገኝ ነው፡፡ የወንጀሎች መደራረብ በሚኖርበት ጊዜ ቅጣትን ለመወሰን የሚያገለግሉ መሠረታዊ ዘዴዎች ሦስት ናቸው፡፡

የመጀመሪያው የቅጣት አወሳሰን ዘዴ የማዳመር (cumulation) ዘዴ ሲሆን ይህ ዘዴ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ተደራራቢ ወንጀሎችን አንድ ሰው ፈጽሞ በሚገኝበት ጊዜ በመጀመሪያ ለእያንዳንዱ ወንጀል በተናጠል ተገቢ ነው ተብሎ የሚታመነውን ቅጣት በመወሰን በመጨረሻ ሁሉም ቅጣቶች አንድ ላይ እንዲደመሩ የሚደረግበት አሰራር ነው፡፡ ይህን ዘዴ የሚከተሉ አንዳንድ አገሮች የቅጣቶች አጠቃላይ ድምር በሕጉ ላይ ለቅጣቱ ዓይነት የተቀመጠውን ጣራ እንዳያልፍ ገደብ የሚያደርጉ ሲሆን ሌሎች አገሮች ደግሞ ቅጣቶቹ ያለገደብ እንዲደመሩ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ገደብ በማያስቀምጡ የማዳመር የቅጣት አወሳሰን ዘዴን በሚከተሉ አገሮች አንድ ሰው ለፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ሁለት መቶ ዓመት ወይም ሦስት መቶ ዓመት እስራት ሊፈረድበት ይችላል፡፡

ሁለተኛው የቅጣት አወሳሰን ዘዴ የማጠቃለል (absorption) ዘዴ ሲሆን ይህ ዘዴ በ1923 ዓ.ም ወጥቶ በነበረው የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ ተካትቶ የነበረ አሰራር ነው፡፡ በዚህ ዘዴ መሠረት ወንጀለኛው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘባቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ ከባድ (ከፍተኛ) ለሆነው ወንጀል የሚጣለው ቅጣት ለሌሎች ወንጀሎች ይወሰን የነበረውን ቅጣት አጠቃልሎ እንዲሸፍን ይደረጋል፡፡

ሦስተኛው ለተደራራቢ ወንጀሎች ቅጣት የሚወሰንበት ዘዴ የማክበድ (aggravation) ዘዴ የሚባለው ሲሆን ይህ ዘዴ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን የማዳመር እና የማጠቃለል ዘዴዎችን በማጣመር የሚሰራበት ዘዴ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በዚህ የቅጣት አወሳሰን መርሕ መሰረት በወንጀለኛው ከተፈፀሙት ተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ ከባድ ለሆነው ወንጀል ቅጣት ከተወሰነ በኋላ ለቀሪዎቹ ወንጀሎች በሕግ በተወሰነው መጠንና ገደብ መሰረት የመጀመሪያው ቅጣት እንዲከብድ ይደረጋል፡፡

3.2.2.2. ለተደራራቢ ወንጀሎች የቅጣት አወሳሰን ዘዴ በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ

ተደራራቢ ወንጀሎች ስለሚያስከትሉት ቅጣት አወሳሰን ከሚደነግጉት ድንጋጌዎች አንዱ የሆነው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 189(1)(ሀ) ድንጋጌ ላይ ወንጀለኛው ከፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ “በአንደኛው ምክንያት የሞት ቅጣት የሚወሰን ከሆነ ይህ የቅጣት ውሳኔ ስለሌሎቹ ተደራራቢ ጥፋቶች የሚወሰነውን ቅጣት ሁሉ አጠቃሎ(ደርቦ) ይይዛል” ተብሎ ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት ለከባዱ ወንጀል የሚወሰነው ቅጣት የሞት ፍርድ ከሆነ ሌሎች ቅጣቶችን ስለሚያጠቃልል ወንጀለኛው ጥፋተኛ የተባለባቸውን ሌሎች ወንጀሎች ግምት ውስጥ በማስገባት የእስራት ቅጣት መወሰን አይቻልም ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሕጉ ለተደራራቢ ወንጀሎች የማጠቃለል (absorption) የቅጣት አወሳሰን ዘዴን ተከትሏል ማለት ነው፡፡

በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 189(1)(ለ) እንደተደነገገው ደግሞ ሌሎች ነጻነትን የሚያሳጡ ወንጀሎችን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ቅጣትን የሚወስነው በመጀመሪያ ከሁሉም ተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ ከባድ ለሆነው ወንጀል የሚገባውን ቅጣት በወንጀለኛው ላይ ይወስንና በመቀጠል ሌሎችን ጥፋተኛው የፈፀማቸውን ተደራራቢ ወንጀሎች ግምት ውስጥ በማስገባት ቅጣቱን ያከብዳል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህን የማክበድ የቅጣት አወሳሰን ዘዴ ተከትሎ ተደራራቢ ወንጀሎችን በፈፀመው ወንጀለኛ ላይ ቅጣት ሲጥል ለከባዱ ወንጀል በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ልዩ ክፍል የተመለከተውን የቅጣት ጣራ ማለፍ የሚችል ሲሆን የከባዱን ወንጀል ቅጣት ጣራ አጋማሽ ያህል እስኪሆን ድረስ ቅጣቱን ማክበድ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ ነገር ግን የከባዱን ወንጀል ቅጣት ጣራ በማለፍ የቅጣቱን አጋማሽ ያህል በማሳደግ ፍርድ ቤቱ መቅጣት የሚችል ቢሆንም በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ለቅጣቱ ዓይነት የተመለከተውን ከፍተኛ ጣራ በማለፍ መወሰን አይችልም፡፡ በዚህም መሠረት ወንጀለኛው የፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች በቀላል እስራት የሚያስቀጡ ከሆነ በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ቁጥር 105 ላይ ለቀላል እስራት ከተደነገገው ጣራ ማለትም ከሦስት ዓመት ቀላል እስራት በላይ አሳልፎ ቅጣት ፍርድ ቤቱ ለመወስን አይችልም፤ ወንጀለኛው የፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች በፅኑ እስራት የሚያስቀጡ ከሆነ ደግሞ በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ቁጥር 107 ላይ ለፅኑ እስራት ከተደነገገው ጣራ ማለትም ከሀያ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት በላይ አሳልፎ ፍርድ ቤቱ ቅጣት ለመወስን አይችልም ማለት ነው፡፡

በገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ ፍርድ ቤቱ ለእያንዳንዱ ወንጀል የሚገባውን ቅጣት ለየብቻው ቢወስን ኑሮ ከሚጣለው ቅጣት ሳያልፍ ከወሰነ በኋላ አንድ ላይ እንዲደመር በማድረግ አንድ ጠቅላላ መቀጮ በወንጀለኛው ላይ ይጥላል፡፡ በዚህ ጊዜ ሕጉ ለተደራራቢ ወንጀሎች የማዳመር (cumulation)) የቅጣት አወሳሰን ዘዴን ተከትሏል ማለት ነው፡፡ ሆኖም የቅጣቶች አጠቃላይ ድምር በሕጉ ላይ ለቅጣቱ ዓይነት የተቀመጠውን ጣራ እንዳያልፍ ገደብ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ወንጀለኛው ለፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ቁጥር 88 ላይ ከተደነገገው ጣራ ማለትም ከብር አምስት ሺህ ብር በላይ አሳልፎ ቅጣት ፍርድ ቤቱ ሊወስን አይችልም ማለት ነው፡፡ የገንዘብ መቀጮው የአምስት ሺህ ብር ከፍተኛ ጣራውን በማለፍ እስከ ብር አስር ሺህ ብር ድረስ ሊጣል የሚችለው ወንጀሎቹ የተፈፀሙት በአፍቅሮ ንዋይ ከሆነ ነው፡፡[1]  

   እዚህ ላይ የእስራት ቅጣቶችን ለማክበድ “በተወሰነው” ቅጣት ላይ እስከ ግማሽ ድረስ መጨመር ነው የሚለው የሕጉ አቀራረብ ላይ ይነሱ ከነበሩት ክርክሮች አንደኛው “በተወሰነው” ሲባል ዳኛው የወሰነውን ቅጣት ለማመልከት ነው ወይስ ለወንጀሉ በሕጉ ልዩ ክፍል የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት ለማመልከት ነው የሚለው ጉዳይ ሲሆን ነገር ግን በብዙ የህግ ባለሙያዎች ዘንድ በሕጉ ልዩ ክፍል የተመለከተውን ለማለት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰድ ነበር /ይወሰዳል፡፡

አንድ ሰው የፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ከፊሎቹ የሚያስቀጡት በቀላል እስራት ከፊሎቹ ደግሞ በፅኑ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች በሚሆኑበት ጊዜ የቅጣት አወሳሰኑ በምን ዓይነት መንገድ እንደሚሰላ የ1949 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በግልፅ የደነገገው ነገር አልነበረም፡፡

በሌላ በኩል ግን ነጻነትን በመቀነስ (በቀላል ወይም በፅኑ እስራት) የሚያስቀጣ ወንጀል እና የገንዘብ መቀጮ የሚያስፈርድ ወንጀል ተደራራቢ በሚሆኑበት ጊዜ ቅጣቱ እንዴት እንደሚወሰን የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 189(1)(ሐ) ድንጋጌ ያስቀምጣል፡፡ በንዑስ አንቀጹ ላይ እንደተደነገገው ወንጀለኛው ከፈፀማቸው ወንጀሎች ውስጥ አንዱ በእስራት ሁለተኛው ደግሞ በመቀጮ የሚያስቀጣ የሆነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ዓይነት ቅጣት በማጣመር ውሳኔ ለመስጠት ይችላል፡፡

ከዚህ በላይ ለማንሳት የተሞከረው አንድ ሰው ከአንድ በላይ የወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎችን በሚፈፅምበት ጊዜ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ የተመለከተውን የቅጣት አወሳሰን ዘዴን ሲሆን በአንድ የወንጀል ተግባር ከአንድ በላይ የወንጀል ድንጋጌዎችን በመጣስ ተደራራቢ ወንጀሎችን በሚፈፅምበት ጊዜ የሚኖረው የቅጣት አወሳሰንን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ የሚወስነው በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 192 ላይ የተቀመጠውን መስፈርት በመመልከት ነው፡፡

በዚህም መሠረት አንድ ሰው በአንድ ድርጊት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ድንጋጌዎችን ከጣሰ (ጣምራ ወንጀሎችን ከፈፀመ) በመርህ ደረጃ ከጣሳቸው የወንጀል ድንጋጌዎች ውስጥ ከባድ ለሆነው ወንጀል ተገቢ የሆነውን ቅጣት ፍርድ ቤቱ ከጣለ በኋላ ወንጀለኛው የጣሳቸውን ሌሎች የወንጀል ድንጋጌዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ቅጣቱን የሚያከብድ ሲሆን በመጨረሻ የሚወሰነው ቅጣት ግን ለከባዱ ወንጀል ከተደነገገው ከፍተኛ ቅጣት ጣራ ማለፍ አይችልም፡፡ ማለትም ፍርድ ቤቱ የሚወስነው ቅጣት ከሁሉም ይልቅ ከባድ ለሆነው ወንጀል በማስቀጫው አንቀጽ ላይ እስከተወሰነው ከፍተኛ ቅጣት ድረስ ብቻ ነው፡፡ ለከባዱ ወንጀል በማስቀጫው አንቀጽ ከተወሰነው ከፍተኛ ቅጣት በማለፍ ሊወስን የሚችለው “… የነገሩ አካባቢ ሁኔታና ይልቁንም በተለይ የተገለፀው አድራጎትና ሆነ ብሎ በአሳብ የተሰራው ወንጀል ወይም ግልጽ የሆነው የወንጀለኛው መጥፎነት ጉዳይ በቂ ምክንያት የሚያስገኝ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በገመተው ጊዜ…” ስለመሆኑ በተጠቀሰው ድንጋጌ ላይ ተመልክቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎችን በሚመለከት በተቀመጠው(በቁጥር 189) ዓይነት በወንጀለኛው ላይ ቅጣቱ እንዲከብድበት ተደርጎ ይወሰናል፡፡

ከዚህ በላይ ከተገለፀው ለመረዳት የሚቻለው ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች ተፈፅመው ሲገኙ ፍርድ ቤቶች በቁጥር 189 መሠረት በወንጀለኛው ላይ ቅጣት አክብደው የመወሰን ግዴታ ያለባቸው ሲሆን በአንድ የወንጀል ድርጊት ከአንድ በላይ የሕግ ድንጋጌዎች በመጣሳቸው ምክንያት ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈፅመው ሲገኙ ግን ፍርድ ቤቶች በወንጀለኛው ላይ ቅጣቱን አክብደው የሚወስኑት እንደሁኔታው መሆኑን ነው፡፡ ከሀሳባዊ መደራረብ የተነሳ ወንጀል የሚፈፅም የፈፀመው ድርጊት አንድ ብቻ በመሆኑና ከሁኔታዎች አጋጣሚ የተነሳ ከአንድ በላይ የሆኑ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎችን በመጣሱ በተደጋጋሚ በፈፀማቸው ድርጊቶች ከአንድ በላይ ወንጀሎችን ከፈፀመ ሰው ጋር እኩል አደገኛ ነው ተብሎ አይገመትም፡፡ ስለዚህም ከሀሳባዊ መደራረብ የተነሳ ቅጣት ሊከብድ የሚችለው የወንጀሎቹ አፈጻጸም የወንጀል አድራጊውን አደገኛነት የሚያመለክት ከሆነ ብቻ ነው፡፡   

3.2.2.3. ለተደራራቢ ወንጀሎች የቅጣት አወሳሰን ዘዴ በአዲሱ የወንጀል ሕግ

በተደራራቢ ወንጀሎች ቅጣት አወሳሰን ዙሪያ አዲሱ የወንጀል ሕግ ከቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የሚለይባቸው የተለያዩ ጉዳዮች ቢኖሩም መሠረታዊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ልዩነት ግን የተደራረቡ ወንጀሎች በተፈፀሙ ጊዜ ቀደም ሲል ይሰራበት የነበረው መሠረታዊ መርህ መለወጡ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አካሄድ ለከባዱ ወንጀል ቅጣት ከተወሰነ በኋላ ለሌላው ወንጀል እስከ መጀመሪያው (የከባዱ) ወንጀል ማስቀጫ አንቀጽ የቅጣት ጣራ አጋማሽ ድረስ ቅጣት ይጨመር የነበረበት የማክበድ (aggravation) መርህ ቀርቶ ለየቅጣቱ ዓይነት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተደነገገውን የቅጣት ጣራ እስካላለፈ ድረስ ለሁሉም ወንጀሎች የሚወሰኑ ቅጣቶች እንዲደመሩ ሆኗል፡፡ በተደራራቢ ወንጀሎች ቅጣት አወሳሰን ዙሪያ በአዲሱ የወንጀል ሕግ የተካተቱትን ነጥቦች ቀጥለን በአጭሩ እንመለከታቸዋለን፡፡

ሀ. ከተደራራቡት ግዙፍ ወንጀሎች ውስጥ ለአንደኛው የሚጣለው ቅጣት የቀሪዎችን ወንጀሎች ቅጣት የሚያጠቃልል በሆነ ጊዜ፣

      ከተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ በአንደኛው ምክንያት የሞት ወይም የዕድሜ ልክ እስራት ወይም ወንጀሎቹ ተመሳሳይ ዓይነት የእስራት ቅጣት የሚያስቀጡ ሆኖ በአንደኛው ምክንያት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተደነገገው ከፍተኛ ቅጣት ከተወሠነ ይህ ውሳኔ ለሌሎች ተደራራቢ ወንጀሎች የሚወሠነውን ቅጣት ሁሉ አጠቃሎ ይይዛል (አንቀጽ 184(1)(ሀ))፡፡ ይህም ማለት ከተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ በአንዱ ምክንያት የሞት ቅጣት ወይም የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት፣ የ25 ዓመት ፅኑ እስራት ወይም የአምስት ዓመት ቀላል እስራት ከተወሠነ በሌሎች ተመሣሣይ ዓይነት ቅጣት በሚያስፈርዱ ወንጀሎች ምክንያት ከተገለፀው ቅጣት በላይ መወሠን አይቻልም፡፡ (በአንቀጽ 184/1//ሀ/ የተደነገገው ሁኔታ ቅጣቱ ቢከብድም ከተደራረቡት ወንጀሎች በአንደኛው ውስጥ በሕጉ ልዩ ክፍል ቅጣቱ ተካትቶ /ተሸፍኖ/ የምናገኝበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው)፡፡

      ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ከባድ ለሆነው ለአንደኛው ወንጀል የሞት ቅጣት፤ የዕድሜ ልክ እስራት ወይም ለእስራቱ ዓይነት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት መወሰኑን ትቶ ዝቅ ያለ ቅጣት ከወሠነ፤ በሌሎቹ ተደራራቢ ወንጀሎች ምክንያት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል እስከተደነገገው ከፍተኛ ቅጣት ድረስ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን አክብዶ መወሠን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጥፋተኛ ከሚፈረድበት ወንጀሎች ውስጥ በአንደኛው ምክንያት የሀያ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት የሚወሰንበት ከሆነ በሌሎች አነስተኛ ወንጀሎች ምክንያት የእስራት ቅጣት ሊወሰንበት አይችልም፡፡ ምክንያቱም ለፅኑ እስራት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተቀመጠው ከፍተኛ የቅጣት ጣራ ሀያ አምስት በመሆኑ ከዚያ አልፎ ሰላሳ ዓመት ወይም ደግሞ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ፍርድ ቤቱ ሊወስን ዓይችልም፡፡ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ሊወሰን የሚችለው ወንጀለኛው ከፈፀማቸው ወንጀሎች ውስጥ ቢያንስ አንዱ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን ወንጀለኛው የፈፀመው ከባዱ ወንጀል በሀያ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት ሊያስቀጣ የሚችል ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የተለያዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ከቅጣት ጣራው ዝቅ በማድረግ ለከባዱ ወንጀል ቅጣት የሚጥል ከሆነ ሌሎች ጥፋተኛው የፈፀማቸው ወንጀሎች ግምት ውስጥ ገብተው ቅጣቱ እንዲከብድ ይደረጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለተደራራቢዎቹ ወንጀሎች የሚወሰነው ቅጣትም  ለሁሉም ወንጀሎች ለየራሳቸው ቅጣቶችን በመጣል እንዲደመሩ በማድረግ ይሆናል፡፡     

ለ. በእስራት የሚያስቀጡ ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ፣

     ጥፋተኛው ከፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ውስጥ የየትኛውም ወንጀል ቅጣት የቀሪዎችን ወንጀሎች ቅጣት የሚያጠቃልል ካልሆነና ወንጀሎቹ በእስራት የሚያስቀጡ ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች ከሆኑ ለእያንዳንዱ በተደራራቢነት ለተፈፀመው ወንጀል ተገቢ የሆነው ቅጣት ተወስኖ ሁሉም እንዲደመር ይደረጋል፡፡ ሆኖም ምንጊዜም ቢሆን ለእስራቱ ዓይነት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ከተደነገገው ጣራ ቅጣት ማለፍ አይቻልም/አንቀጽ 184/1//ለ/፡፡

      አንድ ሰው የፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ከፊሎቹ የሚያስቀጡት በቀላል እስራት ከፊሎቹ ደግሞ በፅኑ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች በሚሆኑበት ጊዜ የቅጣት አወሳሰኑ በምን ዓይነት መንገድ እንደሚሰላ በአዲሱ የወንጀል ሕግ ላይ በግልፅ ተደንግጓል፡፡ ይኸውም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ቅጣቶችን ለመደመር እንዲያመች ሁለት ዓመት ቀላል እስራት እንደ አንድ ዓመት ፅኑ እስራት ይቆጠራል፡፡ ይህ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 184 ላይ በፅኑ እስራትና በቀላል እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ተደራርበው /ተቀላቅለው/ ከተገኙ የእስራት ቅጣቶችን ለመደመር እንዴት እንደሚቻል የሚያመለክተው ድንጋጌ በ1949 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ያልነበረ አዲስ የተጨመረ ሲሆን የቀድሞው ሕግ በግልፅ የደነገገው ነገር ባለመኖሩ ምክንያት የነበረውን የተዘበራረቀ አሰራር ወጥ በሆነ አሰራር እንዲተካ የሚያደርግ ነው፡፡

ሐ. ሁለት ወይም ከዚያ የሚበልጡ በገንዘብ የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ፣ /አንቀጽ 184/1//መ/

             አንድ ሰው የፈፀማቸው ተደራራቢ ወንጀሎች በገንዘብ ቅጣት (በመቀጮ) የሚያስቀጡ ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች የሆኑ እንደሆነ ወይም ከሌሎች ቅጣት ጋር ተጣምረው ለተደራራቢ ወንጀሎቹ የገንዘብ ቅጣቶች በጥፋተኛው ላይ የሚጣሉ በሚሆንበት ጊዜ ለእያንዳንዱ በተደራራቢነት ለተፈፀመው ወንጀል ተገቢ የሆነው የገንዘብ ቅጣት ተወስኖ ሁሉም ይደመራል፡፡ ሆኖም ወንጀሉ በአፍቅሮ ንዋይ የተፈፀመ ካልሆነ በቀር ምንጊዜም ቢሆን በወንጀለኛው ላይ የሚጣለው የመቀጮ ቅጣት አጠቃላይ ድምር በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ከተመለከተው ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ወሠን ማለፍ አይችልም፡፡

     የመውረስና የገንዘብ መቀጮ በሚያጋጥምበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው የቅጣት አወሳሰን ዘዴ ምን ሊሆን ይገባል የሚለውን በተመለከተ በቀድሞውም ሆነ በአዲሱ የወንጀል ሕግ የተካተተው ሀሳብ ተመሳሳይ ነው፡፡ ከተደራራቢዎቹ ወንጀሎች በአንዱ ምክንያት የተቀጪው ንብረት እንዲወረስ ከተወሰነ በሌላው ወንጀል ምክንያት መቀጮ በተጨማሪ ሊወሠን አይችልም /ቁጥር 189(ሠ)፣ አንቀጽ 184(1)(ሠ)/

     በዚህም መሠረት ጥፋተኛው ከፈፀማቸው ተደራራቢዎቹ ወንጀሎች ውስጥ በአንደኛው ወንጀል ምክንያት ከሚፈረድበት ከዋናው ቅጣት በተጨማሪ የወንጀለኛው ንብረት እንዲወረስ ከተፈረደበት በሌሎች ተደራቢ ወንጀሎች ምክንያት የገንዘብ መቀጮ መፍረድ አይቻልም ማለት ነው፡፡

መ. ጣምራ ተደራራቢ ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ጊዜ

     በአዲሱ የወንጀል ሕግ መሠረት አንድ ሰው በአንድ ድርጊት የሚጥሰው አንድን የሕግ ድንጋጌ ብቻ ቢሆንም ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ካደረሰ ተደራራቢ ወንጀሎችን እንደፈፀመ እንደሚቆጠር በአንቀጽ 6ዐ(ሐ) ላይ ተደንግጓል፡፡ ቅጣቱ የሚወሰነውም በሌላ አኳኋን ካልተደነገገ በቀር ከዚህ በላይ በተጠቀሠው ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ጊዜ ቅጣት በሚወሰንበት መንገድ ነው (አንቀጽ 184(2))፡፡

ሠ. የተዛመዱ ወንጀሎች በተፈፀሙ ጊዜ

      የተዛመዱ ወይም የተቀራረቡ ወንጀሎች ተፈፀሙ የሚባለው አንዱ የተደረገው ሌላው ወንጀል እንዲፈፀም ለማድረግ፤ ወይም ለማመቻቸት ወይም ለሌላው ከለላ እንዲሆን ለማድረግ ታስቦሲሆን ነው (አንቀጽ 63)፡፡ በመርህ ደረጃ የተዛመዱ ወንጀሎች በተፈፀሙ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ቅጣትን የሚወስነው በአንቀጽ 184 መሰረት ማለትም ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ጊዜ ቅጣት በሚወሰንበት መንገድ ነው /አንቀጽ 185/1//፡፡

       ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የተዛመዱ ወንጀሎች እንደ አንድ ነጠላ ወንጀል የሚቆጠሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም የሚሆነው ወንጀል ፈጻሚው ዋናውን ወንጀል እግብ ለማድረስ ሲል ሌላ ወንጀል የፈፀመ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ሕግ አውጭው አጥፊው ለዋናው ወንጀል ብቻ ተጠያቂ እንዲሆን በሚደነግግበት ጊዜ ወይም ተዛማጅ ወንጀሎችን እንደ አንድ ነጠላ ወንጀል በመውሰድ የሚደነግግ በወንጀል ሕጉ ውስጥ አንድ ድንጋጌ በሚኖርበት ጊዜ ነው፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ለምሳሌ እንደ ከባድ ግድያ ወይም ከባድ ውንብድና የመሳሰሉ /የተዛመዱ ተደራራቢ ግዙፍ ወንጀሎች/ ቅጣት የሚያከብዱ አንድ ወንጀልን የሚያቋቋሙ መሆናቸው በሕጉ ልዩ ክፍል በተደነገገ ጊዜ ተፈፃሚ የሚሆነው ለእነዚሁ ወንጀሎች የተመለከቱት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡

ረ. ተነጣጥለው ተሠጥተው የነበሩ ውሳኔዎችን ስለማጣመር

      ጥፋተኛውተፈርዶበት ቅጣቱን በመፈፀም ላይ ሳለ ወይም ከፈፀመ በኋላ ከፍርዱ በፊት የፈፀመው ተደራቢ ወንጀል መኖሩ ሲደረስበትተደራቢው ወንጀልአስቀድሞ ቢታወቅሊወሰንበት ይችል ከነበረው ቅጣት ሳያልፍ ይወሰናል (አንቀጽ 186(1))፡፡ ከአንድ ፍርድ በፊት የተፈፀመ ሌላ ወንጀል ተደራራቢ ወንጀል በሚለው የሚሸፈን ሲሆን ከፍርድ በኋላ የሚፈፀም ሌላ ወንጀል ግን እንደ ሁኔታው ደጋጋሚ ወንጀለኛ በሚለው ነው ሊሸፈን የሚችለው፡፡

       ተጣምረው መታየት የነበረባቸው ወንጀሎችበተለያዩ ፍርድ ቤቶች ወይም በተለያዩ ችሎቶች ታይተው ውሳኔ አግኝተው ከሆነየጠቅላላ ቅጣቱ አወሳሰን ከዚህ በላይ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት ይሆናል /አንቀጽ 186//3//፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ማለትም ሁለተኛው ወንጀል የተፈፀመው በአንደኛው ወንጀል ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ከሆነ ወንጀሎችቹ ተደራራቢ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ወይም በተለያዩ ችሎቶች ታይተው ቢሆን አንኳን በተናጠል ተሰጥቶ የነበረው ውሳኔ እንደገና በአንድነት ታይቶ ተደራራቢ ወንጀሎች በሚወሰኑበት መንገድ ቅጣቱ ሊወሰን ይገባል፡፡    


[1] የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 90፣

Exit mobile version