Site icon Ethiopian Legal Brief

የቅጣት አወሳሰን መሠረታዊ ዓላማዎችና ሕገ መንግስቱ

1. የቅጣት አወሳሰን መሠረታዊ ዓላማዎችና ሕገ መንግስቱ

ምንጭ፡ የወንጀል ሕግ እና ሕገ መንግሥቱ  (ክፍል ሁለት)

አዘጋጅና አቅራቢ ዩሱፍ ጀማው

 ሀምሌ 2000 ዓ/ም

የቅጣት መሠረታዊ ዓላማዎችና ግቦች

ወንጀል የሕብረተሰቡን ግንኙነት የሚያዛባ ተግባር ሲሆን ቅጣት ደግሞ ይህን የተዛባ ግነኙነት መልሶ ማስተካከያ መንገድ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሆኖም አንድ የወንጀል ድርጊት የሚያስከትለው ጉዳት ሁሌም ቢሆን በገንዘብ ሊተመን የሚችል አይደለም፡፡ በተጨማሪም የወንጀል ሕጉ ጥበቃ የሚያደርግላቸው አንዳንድ መብቶች በምንም ዓይነት መንገድ ሊካሱ ወይም ወደ ቀድሞ ቦታቸው ሊመለሱ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ከፍትሐብሔር ጉዳዮች በተለዬ በወንጀል ምክንያት የሚጣል ቅጣት በመሠረቱ ጉዳቱን የማስተካከያ መፍትሔ ሳይሆን ሌሎች ማህበራዊ ግቦችን በስራ ላይ ለማዋል የምንጠቀምበት መሳሪያ ነው፡፡ ማለትም ቅጣት የወንጀል ተጎጂውን መካስን ዓላማ ያደረገ አይደለም፡፡

በአጠቃላይ የቅጣት ዓላማዎች አንድ ሕብረተሰብ በወንጀልና በወንጀለኞች ላይ ያለውን አመለካከት የሚያሳይ እንደሆነ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በዚህም መሰረት በተለያዩ አገሮች እና በተለያዩ ጊዜያት በዋናነት ሕብረተሰቡ በወንጀል እና በወንጀለኞች ላያ ያለው አስተሳሰብ ግምት ውስጥ እየገባ የተለያዩ የቅጣት ዓላማዎች ሲቀመጡ ኖረዋል፤ አሁንም እንዲሁ ቅጣት በአንድ አጥፊ ላይ ሲጣል የተለያዩ የቅጣት ዓላማዎች በታሳቢነት ይወሰዳሉ፡፡

በቀድሞው ጊዜ ወንጀል ፈጽሞ የተያዘ ሰው የሚቀጣው የጥፋተኝነቱ መጠንና የፈፀመው ድርጊት አደገኛነት ግምት ውስጥ ገብቶ ሳይሆን በተበዳዩ ላይ ባደረሰው ጉዳት መጠንና ዓይነት ጭምር ነበር፡፡ ይህም ዓይን ላጠፋ ዓይን፣ጥርስ ለሰበረ ጥርስ እንዲሁም የገደለ ይሙት የሚል አንድ ሰው ድርጊቱ ባስከተለው ጉዳት መጠንና ዓይነት በእርሱም ጉዳት እንዲደርስበት የሚደረግበት በብዙ ማህበረሰቦች ዘንድ ሲሰራበት የነበረ የወንጀል ፍትሕ አካሄድ ነበር፡፡[1]

ሆኖም ከሕብረተሰብ የአመለካከት ዕድገትና ስልጣኔ ጋር ተያይዞ ወንጀል በፈፀሙ ሰዎች ላይ ሊወሰድ የሚችለው እርምጃ መጠንና ዓይነት በየጊዜው እየተለወጠ በአሁኑ ወቅት ብቀላን እንደ ዋንኛ የወንጀል ቅጣት ግብ አድርጎ መውሰድ እየቀረ ያለበት ሁኔታ በስፋት የሚስተዋል ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህ ማለት ግን ዘመናዊው ሕብረተሰብ የሚከተለው የወንጀል ቅጣት ዓላማ ጉዳት የደረሰበትን ሰው ስነልቦናዊ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን የተወ ነው ለማለት አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ የቅጣት መሠረታዊ ዓላማዎችና ግቦች ምን ምን ናቸው የሚለውን ለመረዳት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ[2] የመጀመሪያውን አንቀጽ ድንጋጌ በጥንቃቄ መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡ የድንጋጌው የአማርኛ ቅጂ እንደሚከተለው ይነበባል፡-

    “አንቀጽ Á .ዓላማና ግብ

     የወንጀል ሕግ ዓላማ፣ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል  የአገሪቱን መንግስት፣

     የሕዝቦችን፣ የነዋሪዎቹን ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም

     መጠበቅና ማረጋገጥ ነው፡፡

     የወንጀል  ሕግ ግብ  ወንጀል  እንዳይፈፀም  መከላከል ሲሆን  ይህንን

     የሚያደርገው  ስለወንጀሎችና  ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ

     በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ  ወንጀል አድራጊዎቹ

     ተቀጥተው ሌላ ወንጀል  ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ

     እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ  በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች

     እንዳይፈፅሙ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው በማድረግ ነው” ይላል፡፡

ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው ድንጋጌ ይዘት እንደምንገነዘበው የወንጀል ሕጉ ዓላማ የአገሪቱን መንግስት፣ የሕዝቦቿንና የነዋሪዎቿን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም መብትና ጥቅም ማስጠበቅ ሲሆን ይህ የሚደረገውም ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል ነው፡፡ የአንደኛው ለምሳሌ የነዋሪዎች ሰላምና ደህንነት እንዲሁም መብትና ጥቅም መጠበቅና መረጋገጥ ለሌኛው ለምሳሌ ለመንግስት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ሲሆን የአንደኛው ሰላምና ደህንነት አንዲሁም መብትና ጥቅም ሲነካም አንዲሁ የሌላኛው መነካቱ የማይቀር ነው፡፡ በዚህም መሰረት የወንጀል ሕግ የአንደኛውን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም መብትና ጥቅም የሚጠብቀውና የሚያረጋግጠው ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል ነው፡፡ ማለትም በወንጀል ሕጉ የሚጠበቁት የአንደኛው የሕብረተሰብ ክፍል መብቶችና ጥቅሞች ከሌሎቹ የህብረተሰብ ክፍሎች መብቶችና ጥቅሞች ጋር የተቆራኙና ሊነጣጠሉ የማይችሉ ናቸው፡፡

የወንጀል ሕጉን ዓላማ ለማሳካት ዋንኛ ግብ ተደርጎ የሚወሰደውም ወንጀል እንዳይፈፀም የመከላከል ተግባር ሲሆን ይህ አቅጣጫ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ከምንም በፊት ሕብረተሰቡ በወንጀልነት የተፈረጁ ድርጊቶችንና የሚያስከትሉትን ቅጣት አስቀድሞ እንዲያውቅ ሲደረግና ከእነዚህ በወንጀልነት ከተፈረጁ ድርጊቶች እንዲርቅ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም የወንጀል ሕጉ የመጀመሪያው ተግባር የተከለከሉ ድርጊቶችን ለይቶ በማመልከት ሕብረተሰቡ ከእነዚህ በሕግ ከተከለከሉ ድርጊቶች እንዲርቅ ማስጠንቀቅ ነው፡፡ አንድ ድርጊት ሕገ ወጥ መሆኑና በወንጀል የሚያስጠይቅ ስለመሆኑ አስቀድሞ እንዲታወቅ ካልተደረገ ወንጀል የሕብረተሰቡን ጥቅም የሚጻረር ድርጊት መሆኑ አጠቃላይ ግንዛቤ ያለ በመሆኑ ይህን ግንዛቤ በመውሰድ ራሳቸውን የሚጠብቁ ሊኖሩ ቢችሉም አንድ ድርጊት ወንጀል ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ የተተወ ስለሚሆን ሰዎች የወንጀል ድርጊቶች ተብለው የተፈረጁትን ጉዳዮች አስቀድመው አውቀው ድርጊቶቹን ከመፈፀም እንዲቆጠቡ አያስችላቸውም፡ 

ሆኖም ወንጀሎችንና የሚያስከትሉትን ቅጣት ዘርዝሮ ማስፈሩ ብቻ ሕበረተሰቡን ከጉዳት አይከላከልም፡፡ የተከለከሉ ድርጊቶችና ቅጣታቸው አስቀድሞ እንዲታወቅ ቢደረግም በየትኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ውስጥ ክልከላውን ተላልፈው የወንጀል ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ በመሆኑም የወንጀል ሕጉ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በማክበር እንቅስቃሴያቸውን አስተካክለው ከተከለከሉ ድርጊቶች ራሳቸውን ያላራቁ ሰዎች ሲገኙ ተገቢው ቅጣት እንዲጣልባቸው ሊደረግ ወይም በተለያዩ በወንጀል ሕጉ ላይ በተመለከቱ ምክንያቶች ቅጣት ሊወሰንባቸው የማይችል ሲሆን ተጨማሪ ወንጀሎችን እንዳይፈጽሙ አስፈላጊው የጥንቃቄ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ስለዚህ የወንጀል ድርጊት በፈፀሙ ሰዎች ላይ ቅጣት የሚጣለው ከላይ በተጠቀሰው የወንጀል ሕጉ ድንጋጌ ላይ እንደተመለከተው አጥፊዎች ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡ፣ ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ ለማድረግ ነው፡፡ 

በዚህም መሰረት የወንጀል ሕጋችን የወንጀል ድርጊት በፈፀሙ ሰዎች ላይ ቅጣት እንዲጣል ማድረግን በራሱ ግብ አድርጎ አይወስደውም፡፡ በአጥፊዎች ላይ ቅጣት የሚጣለው በቅጣቱ አማካኝነት በዋናነት ሦስት ዓላማዎችን ለማሳካት ነው፡፡ እነርሱም፡-

1.1.1. መቀጣጫ እንዲሆኑ(Deterrence)

በሕጉ ላይ የተጻፈውን የቅጣት ማስፈራሪያ ችላ በማለት ወንጀል የፈፀመ ሰው ተይዞ በሕጉ ላይ የተመለከተው ቅጣት ሲፈፀምበት በማየት ሌላው ሕብረተሰብ ወንጀል ቢፈፅም በተመሳሳይ በሕይወቱ፣ በነጻነቱ ወይም በንብረቱ ዋጋ የሚከፍልበት መሆኑን እንዲገነዘብ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሰረት ወንጀለኛው ለፈፀመው ጥፋት ቅጣት ሲጣልበት ይህ የሚደርስበት ቅጣት ለሌሎች መቀጣጫ ሆኖ መሰል ቅጣት እንዳይደርስባቸው በመፍራት የወንጀል ድርጊቶችን ከመፈፀም ይቆጠባሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ የቅጣት ዓላማ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ አንድ ላይ ቅጣት በአጥፊዎች ላይ የሚጣለው “…ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ…” ነው በሚል ተጠቅሶ የምናገኘው ሲሆን ታሳቢ ያደረገውም ወንጀል የፈፀመ ሰው ላይ ቅጣት ሲወሰን ሌሎች ሰዎችም ወንጀል ከፈፀሙ በተመሳሳይ ቅጣት የሚደርስባቸው ስለመሆኑ ትምህርት ያገኛሉ የሚለውን አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህም በአንድ ጥፋተኛ ላይ ቅጣት በሚጣልበት ጊዜ በወንጀል ሕጉ የሰፈረውን ይህን ዓላማ ከማሳካት አንጻር መታየት አለበት፡፡

1.1.2. መከላከል፣ማስወገድ(Prevention, Incapacitation, Disabling)

ይህ የቅጣት ዓላማ ወንጀለኛው ሁለተኛ ወንጀል ለመፈፅም የሚችልበት ዕድል እንዳይኖረው ወንጀል ለመፈፀም ያስቻሉትን ሁኔታዎች ለማስወገድ እርምጃዎች መውሰድን እንደ አቅጣጫ የተከተለ ሲሆን የሚወሰዱት እርምጃዎች እንደሁኔታው ህብረተሰቡ ውስጥ እንዳይቀላቀል ነጻነቱን ገድቦ ለረጅም ጊዜ ታስሮ እንዲኖር ማድረግ፣ ወይም ጥፋተኛውን በሞት በመቅጣት ጭራሽ ከሕብረተሰቡ እንዲወገድ ማድረግ፣ ወይም ከሙያ ሥራ ጋር በተያያዘ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች ከሙያ ሥራው ማባረር ወይም የሥራ ፈቃዱን መንጠቅ የመሳሰሉትን ሁሉ ያካትታል፡፡ ይህ የቅጣት ዓላማ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ አንድ ላይ ቅጣት በአጥፊዎች ላይ የሚጣለው “…ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡ…” ነው በሚል ተጠቅሶ የምናገኘው ሲሆን ታሳቢ ያደረገውም አንዳንድ ጊዜ ወንጀለኞች ተመልሰው ወደ ሕብረተሰቡ ከተቀላቀሉ ወይም ከአሁን በፊት ወንጀል ለመፈፀም ያስቻላቸውን ሁኔታ በድጋሚ ዕድል ተሰጥቷቸው ካገኙት ወንጀል መፈፀማቸው ስለማይቀር ሕብረተሰቡን ከወንጀል ሥጋት ለማዳን ወንጀለኞቹ መወገድ አለባቸው  ወይም አንደሁኔታው ከአሁን በፊት ወንጀል ለመፈፀም ያስቻላቸውን ሁኔታ መወገድ አለበት የሚል ነው፡

1.1.3. ማረም (Reformative, Rehabilitative)

ይህ የቅጣት ዓላማ በወንጀለኛው ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን መሠረታዊ አቅጣጫውም በወንጀለኛው ላይ የሚጣለው ቅጣት ወንጀለኛው ወደ ሕብረተሰቡ ተመልሶ በሚቀላቀልበት ጊዜ መሰል ወንጀል እንዳይፈፅም የሚያስተምረውና የጥፋተኛውን የግል ሁኔታ ያገናዘበ መሆን ይገባዋል በሚለው አስተሳሳብ ላይ ነው፡፡ በዚህ መሰረት አንድን ወንጀለኛ ወንጀል ለመፈፀም ያነሳሱትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ለፈፀመው ወንጀል የሚጣልበት ቅጣት ወንጀለኛውን አስተካክሎ ወደ ሕብረተሰቡ በመቀላቀል ለሕብረተሰቡን የወንጀል ሥጋት ሳይሆን ጤናማ ሕይወት እንዲመራ የሚያስችለው መሆን አለበት፡፡ ይህ የቅጣት ዓላማ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ አንድ ላይ ቅጣት በአጥፊዎች ላይ የሚጣለው “…እንዲታረሙ ለማድረግ…” ነው በሚል ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡


[1]ፋሲል ናሆም (ዶ/ር)፣ ቅጣትና ኅብረተሰብ፤ዕድገታዊ አመለካከት፣የኢትዮጵያ ሕግ መጽሔት፣ቮልዩም

                  12፣ 1974፣ ገጽ 11

[2]  በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አዲሱ የወንጀል ሕግ፣ የወንጀል ሕግ፣ አንቀጽ ይህን ያህል ተብሎ ሲጠቀስ በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ ማለታችን ሲሆን የቀድሞው የወንጀል ሕግ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ ቁጥር ይህን ያህል ተብሎ ሲጠቀስ ደግሞ በ1949 የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ማለታችን ነው፡፡

Exit mobile version