የካቲት-01

< Back

የካቲት 2002

                                               የሰበር መ/ቁ 42078

የካቲት 8 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

        ሐጐስ ወልዱ

        ሂሩት መለሰ

        ብርሃኑ አመነው

        አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- ወ/ሮ በላይነሽ ዲማ - ወኪል ራሄል ተፈሪ ቀረበች

ተጠሪ፡- አቤሴሎም ዝቄ ቀረበ

 

      መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

      ጉዳዩ የውርስ ሃብት መብት ይከበርልኝ በሚል ክስ መነሻነት የተደረገውን ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ የአሁንዋ አመልካች እና ወ/ሮ አሰለፈች አንዳርጌ የተባለች ሰው ከሣሾች አቶ ናደው ዘውዴ የተባለ ሰው ተከሳሽ፣ ተጠሪ ደግሞ ጣልቃ ገብ በመሆን በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክርክር ጀምረዋል፡፡ ከሣሾች የነበሩት በክሳቸው የጠየቁት የሟች ወንድማቸው አቶ ሕዝቅያስ ዝቄ ንብረት የሆኑትን መኖሪያ ቤት እና ንግድ ቤት እንዲሰጣቸው እንዲሁም የቤት ኪራይ ከነወለዱ እንዲከፈላቸው ነው፡፡ ተከሳሽ የነበረው አቶ ናደው ዘውዴ ለክሱ በሰጠው መልስ ቤቱ በኪራይ መያዙን በአንድ በኩል ሲገልጽ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቤቱ ሟች ሕዝቅያስ ዝቄ ከአባቱ በውርስ ያገኘው የግሉ ንብረት መሆኑን፣ ከሳሾች የሟች የእናት ወገን በመሆናቸው ለሟች ከአባት ወገን በመጣ ንብረት ላይ የወራሽነት መብት የሌላቸው እንደሆነ በመግለጽ ክሱ ይዘረዝር ዘንድ ጠይቆአል፡፡ ጣልቃ ገብ የነበረው ተጠሪም በተመሣሣይ ሁኔታ ከሣሾች በቤቱ ላይ መብት የላቸውም የሚል ክርክር አቅርቦአል፡፡ በመጨረሻም ፍ/ቤቱ የሁሉንም ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ፣ የተከሳሹን እና የጣልቃ ገቡን ክርክር በመቀበል ከሣሾች በቤቱ ላይ መብት የላቸውም በማለት ወስኖአል፡፡ በቤቱ ላይ ያወጡት የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተርም ለተጠሪ እንዲያስረክቡ አዞአል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አመልካች ውሳኔውን በመቃወም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ በማቅረብዋ በእስዋ እና በሥር ተከሳሽና በአሁኑ ተጠሪ መካከል ክርክር ተደርጎአል፡፡ ክርክሩ ከተሰማ በኋላም ፍ/ቤቱ አመልካች በቤቱ ላይ የባለቤትነት (የመውረስ) መብት የላትም፡፡ የባለቤትነት መብት ያለው ተጠሪ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የመጠቀም መብት ስላላት በሕይወት እስካለች ድረስ የእናትዋን ግማሽ ድርሻ ሳታስረክብ በአይነት ወይም በኪራይ ልትጠቀምበት ይገባል (ትችላለች)፡፡ የቤቱን ኪራይ ግን በሙሉ ብቻዋን ልትጠቀምበት ስለማይገባ ግማሹን ለተጠሪ ታስከፍል በማለት ወስኖአል፡፡ በዚህ አይነትም በሥር ፍ/ቤት የተሰጠውን ውሳኔ አሻሽሎአል፡፡ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበችው በዚህ መልክ በተሰጠው ውሳኔም ስለማትስማማ ነው፡፡

      በበኩላችንም አመልካች ታሕሣሥ 13 ቀን 2001 ዓ.ም በጻፈችው ማመልከቻ ያቀረበችውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ተጠሪን አስቀርበን ክርክሩን ሰምተናል፡፡ በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ በሕግ የተሰጠኝን የመውረስ መብት ያሳጣኝ በመሆኑ በሕጉ አተረጓጎም ረገድ መሠረታዊ ስህተት ያለበት ነው በማለት ነው አመልካች እየተከራከረች ያለችው፡፡ ተጠሪ ደግሞ አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ ሕጉን ተከትሎ የተሰጠው በመሆኑ ስህተት ነው ለማለት የሚያስችል አግባብ የለም በማለት ተከራክሮአል፡፡ በመሆኑም በዚህ መልክ የቀረበውን የግራ ቀኝ ወገኖች ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን ተመልክተናል፡፡

      እንደምንመለከተው አመልካች እና ተጠሪ የውርስ ይገባኛል ክርክር ያነሱበት ቤት ለሁለቱም ወንድም የሆነው የሟች ሕዝቅያስ ዝቄ ንብረት የነበረ ነው፡፡ አመልካች ለሟች እህት የሆነችው በእናት በኩል ሲሆን፣ ተጠሪ ደግሞ በአባት በኩል የሟች ወንድም ነው፡፡ ይህ ግንኙነትም ነው በውርሱ ክፍፍል ረገድ ለክርክር መንስኤ የሆነው፡፡ ተጠሪ ቤቱ በሃብትነት ለአመልካች ሊሰጥ አይገባም የሚለው ከመሠረቱ አመጣጡ ከአባት ወገን ማለትም ከእሱ (ተጠሪ) ወንድ አያት ነው፤ ሟች አቶ ሕዝቅያስ ዝቄ ቤቱን ከአባቱ በውርስ ያገኘው በመሆኑ በሃብትነት መተላለፍ ያለበት የወንዱን መስመር ተከትሎ ነው በማለት ነው፡፡ አመልካች ደግሞ ሁለታችንም እየወረስን ያለነው የወንድማችን ንብረት በመሆኑ በመብት ረገድ ልዩነት ሊፈጠር አይገባም የሚል አቋም በመያዝ ነው የተከራከረችው፡፡ ክርክሩ እንግዲህ ውርስን መሠረት ያደረገ በመሆኑ እልባት ሊያገኝ የሚችለው በውርስ ሕጉ በተቀመጡት አግባብነት ባላቸው ድንጋጌዎች መሠረት ነው፡፡

      ሟች ሕዝቅያስ ዝቄ ኑዛዜ ትቶአል አልተባለም፡፡ አመልካች እና ተጠሪ እየተከራከሩ ያሉት ኑዛዜን መሠረት በማድረግ ሳይሆን የውርስ ሕጉን ብቻ በመያዝ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሟች ልጆች አልተወም አባት እና እናቱም በሕይወት የሉም፡፡ ይህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር ስለአወራረሱ ሥርዓት መልስ የሚሰጠው በፍ/ብ/ሕግ ቁ.844(2) የተቀመጠው ድንጋጌ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ተተክተው ይወርሳሉ፡፡ የአመልካች እና የተጠሪ የወራሽነት መብት የሚታየው ከዚህ አንጻር ነው፡፡ በዚህ አካሄድም ጉዳዩን ካየነው አመልካችም በእህትነቷ ማለትም እናትዋን በመተካት ትወርሳለች ወደሚለው መደምደሚያ እንደርሳለን፡፡ በሕጉ መሠረት ወራሽ ሊሆን የሚችል ወገን ከውርሱ ሃብት ተካፋይ እንዳይሆን ከሚደረግባቸው ሁኔታዎች አንዱ አውራሹ ከውርሱ ሲነቅለው ነው፡፡ ይህ በሆነ ጊዜም ከፍ/ብ/ሕግ ቁ.937 እስከ ቁ. 939 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች መሠረት የሚፈጸም ይሆናል፡፡ በያዝነው ጉዳይ ሟች ኑዛዜ ያልተወ መሆኑ ከመገለጹ በቀር አመልካች ከውርሱ ተነቅላለች ለማለት የሚያስችል ክርክርም ሆነ ምክንያት የለም፡፡ ከዚህ የተነሳም አመልካች ከውርሱ ሃብት አትካፈልም ለማለት አይቻልም፡፡ በእርግጥ ሟች ሳይናዘዝ በሞተ ጊዜ ለሟች በውርስ ወይም በስጦታ ከአባቱ መስመር ወገን የመጣለትን የማይንቀሳቀስ ንብረት የእናት መስመር ወገን ለሆኑ ወራሾች በርስትነት መስጠት እንደማይቻል በፍ/ብ/ሕግ ቁ.849(1) በመደንገጉ አመልካች ከቤቱ ላይ ሊኖራት የሚችለው የውርስ ድርሻ እንዴት ነው የሚሆነው? የሚለውን ጥያቄ በቅድሚያ መመለስ ተገቢ ይሆናል፡፡

      የውርስ ሃብት በሚከፋፈልበት ጊዜ በውርስ ድርሻ አመዳደብ ረገድ የሚኖረው አፈጻጸም በእኩልነት መርህ ላይ የተመሠረተ ሊሆነ እንደሚገባ በፍ/ብ/ሕግ ቁ.844(1) እና 1087 ከተቀመጡት ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በያዝነው ጉዳይ አመልካችም ሆነች ተጠሪ ከሟች ጋር ያላቸው ዝምድና የሚበላለጥ አይደለም፡፡ በውርስ ሃብቱ ክፍፍል ረገድ ሊኖር የሚችለው ልዩነት ቤቱን በባለሃብትነት ሊይዘው የሚገባው የትኛው ነው የሚለው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አመልካች ከቤቱ ምንም የምታገኘው የውርስ ድርሻ የለም የሚባልበት የሕግ አግባብ የለም፡፡ በክፍያው አደላደል ሊኖር ስለሚገባው ስርዓትም በፍ/ብ/ሕግ ቁ.1088 የተመለከተውን ድንጋጌ መከተሉ አግባብ ይሆናል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ለክርክር ምክንያት የሆነው የማይንቀሳቀስ ንብረት በመሆኑ በፍ/ብ/ሕግ ቁ.1088 የተቀመጠው የድልድል ስርዓት በፍ/ብ/ሕግ ቁ.849(1) ከተቀመጠው መርህ ጋር የሚስማማ ነው፡፡ በመሆኑም ተጠሪ ቤቱን እወስዳለሁ የሚል ቢሆን በውርስ ድርሻዋ ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ ለአመልካች መክፈል (መስጠት) ይኖርበታል፡፡ ገንዘቡ የሚከፈለው ከላይ በተቀመጠው የእኩልነት መርህ በመከተል ሲሆን፣ መጠኑም በአፈጻጸም የሚታይ ይሆናል፡፡ ሲጠቃለል የሥር ፍ/ቤቶች አመልካችን ከውርሱ ክፍፍል ውጪ በማድረግ የሰጡት ውሳኔ ሕጉን የተከተለ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በመሆኑም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ በሕጉ አፈጻጸም ረገድ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ችለናል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ 60817 ሐምሌ 17 ቀን 99 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 58696 ህዳር 17 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 348(1) መሠረት ተሽረዋል፡፡
  2. አመልካች ለክርክሩ መነሻ በሆነው ቤት ላይ እኩል የመውረስ መብት አላት ብለናል፡፡
  3. ቤቱን በባለሃብትነት የሚወስደው ተጠሪ ነው፡፡ ሆኖም በቅድሚያ ለአመልካች በድርሻዋ መጠን በገንዘብ ይሰጣት ብለናል፡፡
  4. በዚህ ሰበር ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ በሚመለከት ግራ ቀኝ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቶአል፡፡ ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ራ/ታ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.