Site icon Ethiopian Legal Brief

ሰ/መ/ቁ 37313 የጋራ ንብረት የውል መፍረስ

የሰ/መ/ቁ 37313

ግንቦት 18 ቀን 2001

 

ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

በላቸው አንሺሶ

ሱልጣን አባተማም

 

አመልካቾች፡- 1. አቶ መሐሪ ተክለማርያም    ጠበቃ ቀረቡ

  1.      ወ/ሮ መድህን ወልዱ

ተጠሪዎች፡- የወ/ሮ ገነት መኮንን ወራሾች

  1. ወ/ት ሜሮን ብርሃኑ ቀረበች
  2. “   ህሊና ብርሃኑ አልቀረቡም

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሠጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሆኖ ተጠሪዎች ከሳሾች ሲሆኑ አመልካቾች ተከሳሾች ነበሩ፡፡ ክሱም የሟች ብርሃኑ ጫላና የእኔ የባልና ሚስት የጋራ ሀብት የሞግዚት አድራጊዎቼ የውርስ ንብረት የሆነውን በወረዳ 25 ቀበሌ 01 ቁጥሩ 714 የሆነውን መኖሪያ ቤት ከሕግ ውጪ የያዙበት ውል ፈራሽ ሆኖ ቤቱን እንዲያስረክቡ ይወሰንልን የሚል ነው፡፡

አመልካቾችም የባልና ሚስት የጋራ ሀብት መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ አላቀረቡም፡፡ ክርክር በተነሳበት ቤት ላይ ኖረው አያውቁም ሚስት ወ/ሮ ዘቢደር አናውጤ እንጅ ከሳሽ አይደሉም ተጠቃሹ ቤት ወ/ሮ ገነት መኮንን ጋበቻ መሠረትን ከሚሉት ከ1973 ዓ.ም በፊት አቶ ብርሃኑ ጫላና ባለቤታቸው ወ/ሮ ዘቢደር አናውጤ 1966 ዓ.ም የገዙት ለመሆኑ ማስረጃ አለ፡፡ ስለዚህ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 33(2) መሠረት ለመክሰስ ስለማይችሉ ክሱ ይሠረዝ በማለት መልስ በመስጠት ተከራክረዋል፡፡

ግራ ቀኙን ያከራከረው የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 06185 በ8/2/2000 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወ/ሮ ገነት መኮንን የሟች አቶ ብርሃኑ ጫላ ሚስት መሆናቸው በፍ/ቤት በመ/ቁጥር 01783 ከተወሰነ በኋላ ወ/ሮ ዘብይደሩ አናውጤ ተቃዋሚ ሆነው ገብተው ተከራክረው ፍ/ቤቱ ወ/ሮ ገነትን ሚስትነት ስላፀናው ይግባኝ ቀርቦ የፌ/ከ/ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 17437 ላይ በ30/5/98 ዓ.ም በዋለው ችሎት የወ/ሮ ዘቢደሩ ምሥክሮች ተሰምተው እንደገና በመቃወሚያ አቤቱታው ላይ ውሳኔ እንዲሠጥበት ጉዳዩን ለታች ፍ/ቤት የላከው ሲሆን ወ/ሮ ዘብይደሩ በክርክሩ ሳይቀጥሉ ቀርተዋል፡፡ በመሆኑም የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ወ/ሮ ገነት መኮንን የሟች ብርሃኑ ጫላ ሚስት ናቸው ሟች ወ/ሮ ገነት እና ሟች አቶ ብርሃኑ ሲጋቡ በ6-10-73 ዓ.ም ባደረጉት የጋብቻ ውል ላይ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤት የጋራ እንዲሆን ብለዋል፡፡ የእሳቸው ድርሻ ላይ ፈቃድ ሳይጠየቅ የተደረገ ውል ሊሠረዝ ይገባል በማለት የሽያጩ ውል ተሠርዞ ቤቱን ያስረክቡ በማለት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍ/ቤትም በመ/ቁጥር 59947 በሆነው መጋቢት 24 ቀን 2000 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሚስትነት ዙሪያ ያለው ክርክር ሁለቱም ተከራካሪዎች በሕይወት የሌሉ በመሆኑ አመልካቾች ወ/ሮ ገነት ሚስት አይደሉም ወ/ሮ ዘቢደር ሚስት ናቸው የሚል ክርክር የሕግ መሠረት የለም፡፡ ውልም በፍ/ሕ/ቁጥር 1723 መሠረት በሕግ ፊት የሚፀና አይደለም በማለት ውሳኔውን በማጽናቱ የቀረበ የሰበር አቤቱታ ነው፡፡

አመልካቾች ሚያዝያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ ያቀረቡት ቅሬታ፡-

  • ተጠሪዎች የሟች ብርሃኑ ጫላ ልጆችና ወራሾች መሆናቸው እና የወ/ሮ ገነት መኮንን ሚስትነት የተረጋገጠበት ውሳኔ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ተሰርዞ ጉዳዩ እንደገና ታይቶ እንዲወሰን ተብሎ የታዘዘ ቢሆንም ለሥር ፍ/ቤት እንዲያቀርቡ የታዘዘውን ማስረጃዎች ሳያቀርቡ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው በሕግ ፊት የሚፀና የሚስትነት ውሳኔ አልተሠጠም፡፡
  • ተጠሪዎችም የሟች ብርሃኑ ጫላ ልጆች ብሎም ሕጋዊ ወራሾች መሆን የሚመሠረተው ሟች እናታቸው የሟች አቶ ብርሃኑ ጫላ ሚስት ናቸው ከሚል ከተረጋገጠ ፍሬነገር በመነሳትና በጋብቻ ውስጥ የተወለዱ ልጆች አባት የእናታቸው ባል ነው በሚለው የሕግ ግምት መሠረት ነው፡፡ ሆኖም የእናታቸው ሚስትነት ሳይረጋገጥ የተጠሪዎች ወራሽነት ተረጋግጧል ለማለት ስለማይቻል የሥር ፍ/ቤቶች በዚህ ረገድ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ፈጽሟል በማለት ውሳኔው እንዲሻር የሚጠይቅ ነው፡፡

ቅሬታውን መሠረት በማድረግ የተጠሪዎች እናት የሟች አቶ ብርሃኑ ጫላ ሚስት መሆናቸውና የተጠሪዎች ወራሽነት አልተረጋገጠም እየተባለ ለክርክሩ መንስኤ የሆነው ቤት ያለተጠሪዎች እናት ፈቃድ በሟች የተሸጠው በሕግ     አግባብ አይደለም ውሉም በፍ/ሕ/ቁጥር 1723 ላይ የተቀመጠውን መስፈርት አያሟሉም ተብሎ አመልካቾች ቤቱን ያስረክቡ የመባሉን አግባብነት ለመመርመር ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ ታዞ ግራ ቀኙ በዚህ ፍ/ቤት የጽሑፍና የቃል ክርክር አካሂደዋል፡፡ በተጠሪዎች በኩል የቀረበው ክርክር በአጭሩ በምሥክሮች መስማት ረገድ ለወ/ሮ ዘቢደር መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቁ አጋጣሚ ስለሚፈጠር ምስክሮች ቃል ይሰማ ተብሎ የተሠጠውን ውሳኔ አመልካቾች መከራከሪያ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ እንደገና እንዲታይ መመለስ የመክሰስ መብትንና ጥቅምን አያሳጣም፡፡ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት የጋብቻ ውል ላይ  ተለይቶ የተሠጠ ውሳኔ የለም በማለት ውሳኔው እንዲፀና ተከራክረዋል፡፡

እኛም የግራ ቀኙን ክርክር እንደሚከተለው መርምረናል፡፡

በቀዳሚነት ሊታይ የሚገባው የሕግ ነጥብ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ጉዳዩን መጀመሪያ ያየው ፍ/ቤት እንደገና መልሶ እንዲያይ ጭብጥ ይዞ መመለስ የቀድሞውን ውሳኔ የመሻር ውጤት ይኖረዋል ወይንስ አይኖረውም የሚለው ነጥብ መታየት የሚገባ ነው፡፡ የተጠሪዎች ክርክር በጥቅሉ ሲታይ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ ቢመለስም የሚስትነትን ውሳኔ አልሻረውም የሚል ነው፡፡ የአመልካቾች ክርክር ደግሞ የቀድሞ ሚስትነት ውሳኔ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ክርክር ተካሂዶ ውሳኔው ተሠርዞ ጉዳዩ እንደገና ታይቶና ማስረጃ ተሰምቶ እንዲወሰን በተባለው መሠረት እንዲያቀርቡ የታዘዙትን ምስክሮች ሳያቀርቡ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው በሕግ ፊት የሚፀና የሚስትነት ውሳኔ የለም በማለት ነው፡፡ እንግዲህ አንድ ፍ/ቤት የሠጠው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ክርክር ተሰምቶ ጉዳዩ እንደገና መጀመሪያ ያየው ፍ/ቤት መልሶ እንዲያየው ከተደረገ የቀድሞ ውሳኔ እንዳልተወሰነ ወይም በውሳኔው የተገኘው መብት እንደሌለ ወይም እንደተሻረ የሚቆጠር ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ የተጠሪዎች እናት ሚስት ናቸው ተብሎ የተሠጠው ውሳኔ ማስረጃ ተሰምቶ እንዲወሰን በወሰነው ፍ/ቤት ተመልሷል፡፡ በተመለሰው ውሳኔ መሠረት ክርክር ሳይደረግና የተባለው ምሥክሮች ክርክርም ሳይካሄድ የሚስትነታቸው ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ ቀርቷል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁኑ ተጠሪዎች እናት ሞግዚትነት የተገኘው የሟች ሚስት ነበሩ ልጆችም የተወለዱት ከሚስትነታቸው ነው ተብሎ በፍ/ቤት በተረጋገጠው ውሳኔ መሠረት ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ደግሞ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት እንዳልተወሰነ ተደርጐ እንደገና ምሥክሮች ተሰምቶ እንዲወሰን ከተደረገና ክርክር ተካሂዶበት ውሳኔ ካልተሠጠ በስተቀር በእንጥልጥል ላይ ያለ ጉዳይ ከሚሆን በስተቀር በሕግ ፊት የሚፀና ሚስትነትን የሚያረጋግጥ ውሳኔ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ የጽሑፍ የጋብቻ ውልን ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ለይቶ አልወሰነውም የሚለውን ክርክር በተመለከተ የውሳኔው ይዘት ሲታይ በጽሑፍ ውል ላይ ብቻ ተንተርሶ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሠጠው ውሳኔ ያለአግባብ በመሆኑ የምሥክሮች ቃል በመስማት እንዲወሰን መባሉ የጽሑፍና የሰው ማስረጃዎች ሁለቱም ተመዝኖ ሊወሰን የሚገባ መሆኑን የሚያመለክት እንጅ ውልን አልነካውም የሚያስብል የሕግ መሠረት አይኖርም፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ለውሳኔው መሠረት ያደረገው በከፍተኛ ፍ/ቤት የሚስትነት ውሳኔ አልተሻረም በማለት ነው፡፡ ለሽያጩም ውል መፍረስ ምክንያት የሆነው ያለሚስት ፈቃድ የተደረገው የሽያጭ ውል ሊሠረዝ ይገባል በማለት የውሳኔው መሠረት ሚስትነት ነው፡፡ የሚስትነት ውሳኔ አልተሻረም የተባለው ውሳኔ ከፍ ሲል እንደተመለከተው እንዳልተወሰነ ወይም እንደሌለ የሚቆጠር ውሳኔ ነው፡፡ ውሳኔው እንደሌለ ወይም እንዳልተወሰነ የሚቆጠር ከሆነ ደግሞ ከዚህ የሚመነጭ መብትም ሆነ ጥቅም ሊኖር አይችልም፡፡ የሽያጩ ውል እንዲሠረዝ ለመቃወም መብት የተገኘው ከሚስትነት ነው፡፡ ሚስትነት ከሌለ ደግሞ መቃወሚያ ማቅረብ አይቻልም፡፡ በመሆኑም አመልካቾች በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 33(2) መሠረት ተጠሪዎች የመክሰስ መብት የላቸውም በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍ/ቤቱ ባለመቀበል የሠጠው ውሳኔ ከፍተኛ ፍ/ቤትም ይህን ማረም ሲገባው በማጽናት የሠጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ብለናል፡፡

 

 

 

ው ሳ ኔ

  1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 06185 በ8/2/2000 ዓ.ም እንዲሁም የከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 59947 መጋቢት 24 ቀን 2000 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሠጠው ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡ የፃፍ፡፡
  2. ተጠሪዎች የመክሰስ መብት የላቸውም ብለናል፡፡
  3. ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡ መዝገቡን ዘግተናል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ራ/ታ

Exit mobile version