Site icon Ethiopian Legal Brief

ሰ/መ/ቁ. 38152 የውርስ ሀብት ክፍፍል

የሠ/መ/ቁ. 38152

29/ዐ8/2ዐዐ1

ዳኞች፡– አብዱልቃድር መሐመድ

ሒሩት መለሠ

ታፈሰ ይርጋ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- የወ/ሮ ገነት ዳምጤ ወራሾች – ጠበቃ ቀረቡ፡፡

ተጠሪ፡– እነ አቶ ይስማ አስፋው – ጠበቃ ቀረቡ፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ቀጥሎ የተመለከተው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ይህ ጉዳይ የውርስ ሀብት ክፍፍልን የሚመለከት ሲሆን ተጠሪዎች በአመልካች ላይ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 11 ቀበሌ 17 ክልል የሚገኘውን ቁጥር 847 የሆነውን ቤት ጥቅምት 19 ቀን 1962 ዓ.ም. ሟች ወ/ሮ ተካበች ሀብተወልድ ባደረጉት ኑዛዜ ለከሣሾችና የተከሣሽ ባለቤት ለሆነው ወንድማችን ሠጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አውራሻችን ወ/ሮ ተካበች ሀብተወልድ በባንክ ያስቀመጡትን ብር 4666 ወንድማችንና የተከሳሽ ባለቤት የሆኑት ወስደው አላካፈሉንም፡፡

ስለዚህ ተከሣሽ ከላይ የተጠቀሰውን ቤትና አብረውት ያሉትን ቤቶች እንደዚሁም ከገንዘቡ እንዲያካፍሉን ይወሰንልን በማለት ጠይቀዋል፡፡

ተከሣሽ /የአሁን አመልካቾች አውራሽ/ ቀርበው በሰጡት መልስ ከሳሾች አውራሻችን የሚሏቸው ወ/ሮ ተካበች ሀብተወልድ ከሞቱ በኋላ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1ዐዐዐ ላይ እንደተቀመጠው በ3 ዓመት ጊዜ የውርስ ሀብት ይገባናል በማለት ጥያቄ ያላቀረቡ ስለሆነ አቤቱታው በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት የተከራከሩ ሲሆን ለፍሬ ጉዳዩም ሙሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤትም የይርጋ ክርክሩ ተቀባይነት የለውም ካለ በኋላ ክስ የቀረበበት ቤት የግራ ቀኙ የጋራ ሀብት ስለሆነ 2/3ኛውን ከሣሾች ቀሪውን 1/3 ደግሞ ተከሣሽ እንዲወስዱ በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

ተከሣሽ በዚሁ ውሣኔ ቅሬታ አድሮባቸው የይግባኝ ቅሬታቸውን ለፌዴራል ከ/ፍ/ቤት አቅርበው ፍ/ቤቱም በበኩሉ ግራ ቀኙን አከራክሮ የሥር ፍ/ቤት ውሣኔ ጉድለት የሌለው ነው በማለት ይግባኙን ባለመቀበል ውሣኔውን አጽንቷል፡፡

የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህንኑ በመቃወም ሲሆን ይህም ችሎት አቤቱታውን መርምሮ በሥር ፍ/ቤት በአመልካቾች አውራሽ በኩል የተነሳው የይርጋ መቃወሚያ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ተጠሪዎች ባሉበት ለሰበር ቀርቦ ሊታይ እንደሚገባው በማመኑ ተጠሪዎችን በመጥራት ግራ ቀኙን አከራክሯል፡፡

በአጠቃላይ የክርክሩ ይዘት ከፍ ብሎ የተመለከተው ሲሆን የሰበር አቤቱታው ያስቀርባል ከተባለበት ነጥብ አኳያ እንደሚከተለው ተመርምሯል፡፡

ከክርክሩ መገንዘብ እንደተቻለው ለክሱ ምክንያት የሆነው ቤት ተጠሪዎች ሟች ወ/ሮ ተካበች ሀ/ወልድ በኑዛዜ ሠጥተውናል የሚሉት በ1962 ዓ.ም. ሲሆን ወ/ሮ ተካበች ሀ/ወልድ ደግሞ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ1968 ዓ.ም. ነው፡፡ የውርስ ንብረቱ ድርሻችንን የአመልካቾች አውራሽ ሊያካፍሉን ይገባል በማለት ክስ የመሠረቱት በ1994 ዓ.ም. ነው፡፡

በፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት ክርክር ሲደረግ አቤቱታው በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት የአመልካቾች አውራሽ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረቡት በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1ዐዐዐ ላይ የተመለከተውን በመጥቀስ ነው፡፡ የዚህ ድንጋጌ ተፈፃሚነት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በውሣኔው ላይ እንዳሰፈረው አንድ እውነተኛ የሆነ ወራሽ ትክክለኛው ወራሽ መሆኑ ታውቆለት ዋጋ ያለው የወራሽነት ማስረጃ ሳይኖረው የውርሱን ንብረት በእጁ ያደረገው ሰው የውርሱን ንብረት እንዲለቅ ክስ በሚያቀርብበት ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን በተያዘው ጉዳይ በአመልካቾች አውራሽ ላይ ክስ ቀርቦ የነበረው ምንም ዓይነት መብት ሳይኖራቸው ይዘውት የሚገኘውን የውርስ ሀብት ድርሻችንን ትልቀቅልን በማለት ስለሆነ የተጠቀሰው ድንጋጌ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት አይኖረውም፡፡

ተጠሪዎች በዚህ መልኩ ያቀረቡት አቤቱታ በምን ያሕል ጊዜ መቅረብ እንዳለበት በውርስ ሕጉ ላይ አልተመለከተም፡፡ የውርስ ሕጉ በዚህ ረገድ ክፍተት ካለበት ወደ ጠቅላላ ሕግ በመሄድ ለጉዳዩ እልባት መስጠት በሕግ አተረጓጎም መርህ /principles of legal interpretation/ የተፈቀደ ነው፡፡ በዚሁ መሠረትም ጉዳዩን በፍትሐብሔር ሕጉ ጠቅላላ ስለውሎች ከተደነገገው አንፃር ተመልክተነዋል፡፡ በዚህ ክፍልም ግዴታዎች ከውል የተገኙ ባይሆንም በውል ሕግ ላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት እንዳላቸው በቁጥር 1677/1/ ላይ ተመልክቷል፡፡ በውል ሕግ ደግሞ ዋናው የይርጋ ድንጋጌ በቁጥር 1845 ላይ የተመለከተው የ1ዐ ዓመት የይርጋ ጊዜ ነው፡፡

በተያዘው ጉዳይ ተጠሪዎች በውርስ የተላለፈልንን ድርሻ ንብረታችንን ሊለቁልን ይገባል በማለት በአመልካቾች አውራሽ ላይ ክስ የመሠረቱት ከላይ እንደተመለከተው በ1994 ዓ.ም. ሲሆን ኑዛዜውን አድርገዋል የተባሉት ግለሰብ በሞት የተለዩት ደግሞ በ1968 ዓ.ም. ነው፡፡ ኑዛዜው ከሟች ሞት በኋላ ውጤት የሚኖረው እንደመሆኑ መጠን ሟች ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ በ1ዐ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠሪዎች አቤቱታውን ማቅረብ ሲገባቸው ከ26 ዓመት በኋላ ጥያቄውን ማቅረባቸው በይርጋ የማይታገድበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ስለሆነም የሥር ፍ/ቤቶች የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1ዐዐዐ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት አይኖረውም ማለታቸው ተገቢ ቢሆንም ነገር ግን ከ26 ዓመት በኋላ የቀረበን የውርስ ንብረት ክፍያ ጥያቄ ከጠቅላላ ሕግ አኳያ በይርጋ የታገደ ሆኖ ሳለ ከዚህ አንፃር የይርጋ ክርክሩን ሳይመለከቱት መቅረታቸው መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ው ሣ ኔ

  1. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 18669 በ24/ዐ1/2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ እንደዚሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 61155 በ21/9/2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡
  2. ተጠሪዎች ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል ተብሎ ተወስኗል፡፡
  3. ግራ ቀኙ ወጭና ኪሣራ ይቻቻሉ፡፡
  4. መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መ/ቤት ተመልሷል፡፡

የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

የሃሣብ ልዩነት

እኔ በአምስተኛው ተራ ቁጥር የተሰየምኩት ዳኛ፣ ተጠሪዎች የወ/ሮ ተካበች ሀብተወልድ ወራሽ መሆናቸውን በማረጋገጥ ንብረቱን ከሟች መካሽ ጌታነህ የአመልካች ባል ጋር በጋራ የያዙትና የባለቤትነት ደብተር በጋራ ያወጡ መሆኑን ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ የተገለፀ በመሆኑ ይህም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1ዐ53 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የወራሾቹ የጋራ ንብረት እንደሆነ ስለሚቆጠርና ተጠሪዎች ይህንን የጋራ ሀብታቸውን በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1272 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት በማንኛውም ጊዜ ለመከፋፈል ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉ በመሆኑ ተጠሪዎች ንብረት ለመካፈል ያቀረቡት ጥያቄ በይርጋ እይቋረጥም በማለት የልዩነት ሀሳቤን አስፍሬያለሁ፡፡

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

 

ነ/ዓ

Exit mobile version