Site icon Ethiopian Legal Brief

የወንጀል ቅጣት እና ሕገ መንግሥቱ

1.2. የወንጀል ቅጣት እና ሕገ መንግሥቱ

ምንጭ፡ የወንጀል ሕግ እና ሕገ መንግሥቱ  (ክፍል ሁለት)

አዘጋጅና አቅራቢ ዩሱፍ ጀማው

 ሀምሌ 2000 ዓ/ም

1.2.1. ቅጣት የመጣል ሥልጣን ያለው አካል

ከመንግሥት አካላት ውስጥ ድርጊቶችን በወንጀልነት ለመፈረጅ ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን ያለው ሕግ አውጭው አካል ነው፡፡[1] እያንዳንዳቸው በወንጀልነት ተፈርጀው በሕግ ተዘርዝረው የተቀመጡት ድርጊቶች የሚያስከትሉት ቅጣት ምን ያህል እንደሆነ የመወሰን ሥልጣን ያለውም እንዲሁ ሕግ አውጭው አካል ነው፡፡ ሕግ አውጭው ድርጊቶችን በወንጀልነት ለመፈረጅ የወንጀል ሕጉን ባወጣበት ወቅት በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን ማህበራዊና የግብረ ገብነት እሴቶች ግምት ውስጥ ያስገባል ተብሎ የሚገመት ሲሆን እያንዳንዱ ወንጀል የሚያስቀጣውን የቅጣት መጠን ለመደንገግም እንዲሁ ሕብረተሰቡ ስለወንጀልና ወንጀለኞች ያለውን አመለካከት እንዲሁም በዘመኑ አስተሳሰብ ተቀባይነት ያላቸውን የቅጣት ዓላማዎች ግምት ውስጥ ያስገባል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም ሕግ አውጭው ወንጀለኞችን በአካል አስቀርቦ የሚመረምርና የእያንዳንዱን ወንጀለኛ የአደገኛነት ዝንባሌ፣ ያለፈ ሕይወት ታሪክ፣ ወንጀል ለመፈፀም ያነሳሱትን ምክንያቶች፣ወ.ዘ.ተ. ለማረጋግጥ የሚያስችለው ሁኔታ የሌለ በመሆኑ የተወሰኑ መመዘኛዎችን በተለይም እያንዳንዱ የወንጀል ድርጊት በሕብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለውን የአደጋ ወይም የጉዳት መጠን ሚዛን ውስጥ በማስገባት ለተለያዩ ወንጀሎች የተለያዩ ቅጣቶችን ይደነግጋል፡፡

በሌላ በኩል ግን አንድ የወንጀል ድርጊት በሕብረተሰቡ ላይ ያስከትለው የአደጋ ወይም የጉዳት መጠን ተመሳሳይ ቢሆንም አንድ ወንጀለኛ የሚቀጣው የቅጣት መጠን ሊወሰን የሚገባው የወንጀለኛው አደገኛነትና የጥፋተኛነቱ መጠን ግምት ውስጥ ገብቶ መሆን ስላለበት ለአንድ የወንጀል ድርጊት በሕግ አውጭው አማካኝነት የሚደነገገው የቅጣት መጠን አብዛኛውን ጊዜ ቁርጥ ያለ አንድ ቅጣት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም ብዙ ጊዜ በሕግ አውጭው የሚደነገገው ቅጣት መነሻና ጣራ ቅጣቱን ወይም አማራጭ ቅጣቶችን የሚያስቀምጥ ይሆናል፡፡

የወንጀል አድራጊውን የተለያዩ የግል ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት እና ሕግ አውጭው በሕግ የደነገጋቸውን መስፈርቶች በመጠቀም ለእያንዳንዱ ወንጀለኛ ተገቢውን ቅጣት መወሰን የሚችሉት ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በመርህ ደረጃ ለእያንዳንዱ በወንጀልነት ለተፈረጀ ድርጊት ቅጣት የመጣል ሥልጣን የሕግ አውጭው አካል ቢሆንም ፍርድ ቤቶች ሕግን ለመተርጎም በተሰጣቸው ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን መሰረት ሕግ አውጭው ያስቀመጣቸውን ገደቦች ሳያልፉ በሕግ የተቀመጡ መመዘኛዎችን በመጠቀም ለእንዳንዱ ወንጀለኛ ተገቢ ወይም ተመጣጣኝ ነው ያሉትን ቅጣት ይወስናሉ (ይፈርዳሉ)፡፡ ስለዚህ በቅጣት አወሳሰን ላይ ሕግ ተርጓሚውም የራሱ የሆነ ሚና አለው ማለት ነው፡፡

ሦስተኛው የመንግሥት አካል ተደርጎ የሚወሰደው የሕግ አስፈጻሚው አካልም እንዲሁ በቅጣት አወሳሰን ዙሪያ የራሱ ሚና አለው፡፡ ይህ ሚናው በተለይም ጥፋተኛው አመክሮ እንዲሰጠው በማድረጉ ሂደት ላይ ባለው ተሳትፎ እና ይቅርታ ለመስጠት ባለው ሥልጣን ዙሪያ የሚታይ ነው፡፡ አንድ በእስራት እንዲቀጣ የተፈረደበት ወንጀለኛ የተፈረደበት የእስራት ጊዜ ሳይጠናቀቅ ከእስር እንዲለቀቅ የሚወሰነው በፍርድ ቤት ቢሆንም ጥፋተኛው እስረኛ ሆኖ በቆየበት ወቅት ያሳየውን መልካም ጠባይ መሠረት በማድረግ ማረሚያ ቤቱ የሰጠው አስተያየት የውሳኔው ዋንኛ መሰረት ነው፡፡

እንዲሁም ሕግ አውጭው ያወጣውን ሕግ መሰረት በማድረግ ሕግ ተርጓሚው የሰጠውን የቅጣት ውሳኔ ሕግ አስፈጻሚው አካል በሚሰጠው ይቅርታ ሙሉ በሙሉ ቀሪ ማድረግ፣ መጠኑን መቀነስ ወይም መለወጥ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ሕግ አውጭው አካል በቅጣት አወሳሰን ዙሪያ ያለውን መጠነኛ ሚና ያሳያል፡፡

1.2.2. የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ የማይሰራ መሆኑ

በሕግ በሌላ አኳኋን ካልተገለፀ በስተቀር ለአንድ ወንጀል በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል ከተደነገገው የቅጣት ወለልና ጣራ ውጭ ቅጣት ሊጣል አይችልም፡፡ እንዲሁም ለአንድ የወንጀል ድርጊት ሊጣል የሚችለው ቅጣት የሚወሰነው ወንጀሉ ከተፈፀመበት ወቅት አስቀድሞ በተደነገገ የወንጀል ድንጋጌ በተመለከተው መሠረት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በአገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ የሆነው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 22 “ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈፀመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈፀሙ ወይም አለመፈፀሙ ወንጀል መሆኑ በሕግ የተደነገገ ካልሆነ በስተቀር ሊቀጣ አይችልም፡፡ እንዲሁም ወንጀሉን በፈፀመበት ጊዜ ለወንጀሉ ተፈጻሚ ከነበረው የቅጣት ጣራ በላይ የከበደ ቅጣት በማንኛውም ሰው ላይ አይወሰንም” ይላል፡፡ ይህ ድንጋጌ ሁለት ዓይነት መሠረታዊ ውጤቶችን ያስከትላል፡፡ እነዚህም አንድ ድርጊት በሚፈፀምበት ወቅት ድርጊቱ በጊዜው የማያስቀጣ ከነበረ ይኸው አስቀድሞ የተፈፀመው ድርጊት ከጊዜ በኋላ በወጣ ሕግ ወንጀል ነው ሊባል አይችልም፡፡ በተጨማሪም ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ወንጀል ቢሆንም እንኳ ወንጀለኛው መቀጣት ያለበት ድርጊቱ በሚፈፀምበት ወቅት ተፈጻሚነት የነበረው የወንጀል ሕግ በደነገገው የቅጣት ጣራ መሠረት መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም ከድርጊቱ በኋላ የወጣ ሕግ የቅጣት ጣራውን ከፍ ቢያደርገው ይህ ቅጣት ሕጉ ከመታወጁ በፊት ለተፈፀመ ወንጀል ተፈጻሚ መሆን የለበትም፡፡

አንድ የወንጀል ድርጊት ከተፈፀመ በኋላ የሚወጡ የወንጀል ድንጋጌዎች ለዚያ ዓይነት ወንጀሎች ቀደም ሲል ተደንግጎ የነበረውን ቅጣት በተለያዬ መንገድ ሊያከብዱት ይችላሉ፡፡ ይኸውም ድርጊቱ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን ወንጀል ቢሆንም ከድርጊቱ በኋላ የወጣው የወንጀል ድንጋጌ የቅጣቱን ከፍተኛ ጣራ በማሳደግ፣ ወይም የቅጣቱን ዝቅተኛ ወለል ከፍ በማድረግ ወይም በአማራጭ ተቀምጠው የነበሩ የቅጣት ዓይነቶችን በማጣመር የወንጀል ድርጊቱ በተፈፀመበት ጊዜ ሕጉ ላይ ተመልክቶ የነበረውን ቅጣት አክብዶት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በየትኛውም መንገድ ቅጣቱ እንዲከብድ የተደረገበት ሁኔታ ቢኖር ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ከተቀመጠው የቅጣት መጠን ውጭ በወንጀለኛው ላይ ቅጣት ሊወሰንበት አይችልም፡፡

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 ድንጋጌ መሠረት አስቀድሞ ወንጀል መሆኑ ባልተደነገገ ድርጊት ማንኛውም ሰው ሊቀጣ አይችልም፤ እንዲሁም ወንጀሉ በተፈፀመበት ጊዜ ከነበረው የቅጣት ጣራ በላይ ሊቀጣ አይችልም፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ መርሕ በአ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 5 ላይም ተካትቶ እናገኘዋለን፡፡ ከዚህም አንጻር የአዲሱ የወንጀል ሕግ ተፈጻሚነት ሕጉ ሥራ ላይ ከዋለበት ከግንቦት 01 ቀን 1997 ዓ.ም ጀምሮ ለተፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች ነው ማለት ነው፡፡

በዚህም መሰረት አንድ ድርጊት በአዲሱ የወንጀል ሕግ ወንጀል ነው ቢባልም በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት ግን በወንጀልነት ያልተፈረጀ ድርጊት የነበረ ከሆነ ድርጊቱ የተፈፀመው ከግንቦት 01 ቀን 1997 ዓ.ም በፊት ከሆነ በወንጀል ሊያስጠይቅ አይችልም፡፡ እንዲሁም ድርጊቱ በቀድሞውም ሆነ በአዲሱ የወንጀል ሕግ ወንጀል ስለመሆኑ የተደነገገ ቢሆንም እንኳን ወንጀለኛው መቀጣት ያለበት ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ተፈጻሚነት የነበረው የወንጀል ሕግ በደነገገው የቅጣት ጣራ እና የቅጣት ወለል መሰረት መሆን አለበት፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ማለትም አንድ የወንጀል ሕግ ከመውጣቱ በፊት ለተፈፀመ ድርጊት ተፈጻሚነት የለውም የሚለው አጠቃላይ መርሕ ቢኖርም በተለዩ በሕግ በተፈቀዱ ልዩ ሁነታዎች (exceptions) ግን የወንጀል ሕጉ ወደ ኋላ ተመልሶ ሊሰራ ይችላል፡፡ እነርሱም፡-

  1. አዲሱ የወንጀል ሕግ ከቀድሞው ሕግ ይልቅ ለተከሳሹ ቅጣትን የሚያቃልልለት በሚሆንበት ጊዜ ተከሳሹ ወንጀሉን በፈፀመበት ወቅት ሥራ ላይ ያልነበረ ሕግ ቢሆንም ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

1.2.3. ለአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት ስለመከልከሉ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 23 ላይ “ማንኛውም ሰው በወንጀል ሕግና ሥነ ሥርዓት መሠረት ተከሶ የመጨረሻ በሆነ ውሳኔ ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነጻ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና አይከሰስም ወይም አይቀጣም” በማለት ተደንግጓል፡፡ በአዲሱ የወንጀል ሕግም እንዲሁ በተመሳሳይ አንድ ሰው በአንድ ወንጀል ሁለት ጊዜ ሊከሰስም ሆነ ሊቀጣ እንደማይችል ተመልክቷል፡፡

       አንድ ወንጀል ከአንድ ጊዜ በላይ እንደማያስቀጣ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በመሠረታዊ የወንጀል ሕጉ ውስጥ እንዲደነገግ ያስፈለገበት በቂ ምክንያት አለ፡፡ በአንድ የወንጀል ሕግ ውስጥ እያንዳንዱ ወንጀል ምን ዓይነት ቅጣት እንደሚያስከትል በዝርዝር የተደነገገ በመሆኑ አንዴ ለተፈፀመ ወንጀል የተለያዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ሕግ አውጪው በቂ ወይም ተመጣጣኝ ነው ብሎ የገመተውን ቅጣት በግልፅ አስቀምጣùል፡፡ ስለዚህም አንድ ወንጀለኛ በአንድ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ቅጣት ተወስኖበትና ቅጣቱንም ፈፅሞ እያለ ያንኑ ሰው ለዚያው ወንጀል መልሶ መክሰሱ ወይም መቅጣቱ በሕብረተሰቡ ኑሮ ላይ ከፍ ያለ ቀውስን መጋበዝ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት በአንድ ወንጀል ተከሰው ቅጣታቸውን የጨረሱ ወይም ተከሰው ነፃ የወጡ በዚያው ጉዳይ እንደገና ይከሰሱ ቢባል የወደፊት ኑሯቸውን ያለ ሥጋት መምራት አይችሉም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ መሠረታዊ የሰው ልጆች መብቶች መጣሱ ስለማይቀር መርሁን በሕገ መንግሥቱና በመሠረታዊ የወንጀል ሕጉ ላይ መደንገጉ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡ ዜጎችም በሕጉና በሥርዓቱ ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡[2]


[1] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55(5)

[2] የወንጀል ሕግ መሠረታዊ መርሆች፣ፀሐይ ወዳ፣ 1994፣ገጽ 29-30

Exit mobile version