Search Knowledge Base

< Back
You are here:
Print

የጥንቃቄ እርምጃዎች

. የጥንቃቄ እርምጃዎች

በመሠረቱ በወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ ማናቸውም እርምጃዎች አጠቃላይ የሕብረተሰብን ደህንነትና ሰላም ከመጠበቅ ሌላ መሠረታዊ ምክንያት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ይህን ለማስጠበቅ አንዳንድ ጊዜ በወንጀለኛው ላይ ቅጣትን መጣል ብቻ በቂ ላይሆን ወይም ደግሞ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፡፡ የወንጀለኛውን አደገኛ ባህሪ፣ የወንጀሉን ጠባይ፣ ወንጀለኛው ወንጀሉን እንዲፈፅም ያነሳሱትንና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሁኔታው በወንጀለኛው ላይ ከቅጣት በተጨማሪ ወይም በቅጣቱ ምትክ አግባብነት ያላቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች መወሰን አስፈላጊ ነው፡፡

ስለዚህም አንድ ወንጀል አድራጊ ለፈፀመው ወንጀል ከሚወሰንበት ቅጣት በተጨማሪ ወይም በቅጣቱ ምትክ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወሰኑበት ይችላሉ፡፡ ማለትም ለተፈፀመው ወንጀል አግባብነት ያለው ድንጋጌ ላይ ባይመለከትም ፍርድ ቤቶች አስፈላጊ ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሁሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ “ፍርድ ቤቶች አስፈላጊ ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሁሉ” ሲባል በዘፈቀደ ዳኞች የጥንቃቄ እርምጃዎችን መወሰን ይችላሉ ለማለት አይደለም፡፡ ዳኞች ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ ለተገኘበት ወንጀል ተገቢ የሆነውን ቅጣት ከወሰኑ በኋላ ወይም እንደ አግባብነቱ ምንም ዓይነት ቅጣት በወንጀል ፈጻሚው ላይ ሳይጥሉ ተፈፀመ የተባለው ወንጀል የሚሸፈንበት አንቀጽ ላይ ባይመለከትም በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወሰኑ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎችና መስፈርቶች ግምት ውስጥ በማስገባት “አስፈላጊ ሆኖ ባገኙት ጊዜ ሁሉ” በወንጀል አድራጊው ላይ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መወሰን ይችላሉ ለማለት ነው፡፡

የጥንቃቄ እርምጃዎች በመሠረቱ ዋና ወይም ተጨማሪ ቅጣቶች አይደሉም፡፡ ዋና ዓላማቸው ወንጀለኞች እንደ አደገኛነታቸው መጠን በተለዬ ሁኔታ ቅጣታቸውን እንዲፈጽሙ ማስቻልና ወንጀለኞች ወይም ወደፊት ወንጀል ሊፈፅሙ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች ወንጀል እንዳይፈፅሙ መከላከልና መቆጣጠር ነው፡፡ የጥንቃቄ እርምጃዎች ለአጠቃላይ ሕብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ ለወንጀለኛውም ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በዚህም መሰረት ወንጀለኞች ለወደፊት ወንጀል ለመፈፀም እንዳይችሉ ወንጀል ለመፈፀም እድል ይሰጣቸው የነበረ ሁኔታን በማስቀረት ለምሳሌ ወንጀሉ የተፈፀመው በሙያ ስራቸው ላይ ተሰማርተው በሚሰሩበት ጊዜ ከሆነ ሕጉ ያስቀመጠውን መመዘኛ ተከትሎ እንደ አግባብነቱ የሙያ ፈቃዳቸውን በመሰረዝ ወይም በመንጠቅ፣ የወንጀል ተግባር ለመፈፀም ምክንያት ከሆነው ወይም አዲስ ጥፋት ለመሥራት ከሚረዳው ከአንዳንድ ሥፋራዎች ለምሳሌ ከመሸታ ቤት፣ ከሆቴል ቤት፣ ወ.ዘ.ተ እንዳይደርስ በመከልከል እና በመሳሰሉት መንገዶች ወደፊት ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን አስቀድሞ በመከላከል የሕብረተሰቡን ደህንነት ለማያረጋገጥ የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ወንጀል አድራጊው በተለያዩ ምክንያቶች የአዕምሮ መቃወስ የደረሰበት ዓይነት ሰው የሆነ እንደሆነ እንደሁኔታው ተስማሚ በሆነ ተቋም ውስጥ ተለይቶ እንዲቀመጥ ወይም ሕክምና እንዲደረግለት በማድረግ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ወንጀል አድራጊ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ በጠባቂ ስር ሆኖ ቁጥጥር እየተደረገበት ትምህርትና መልካም አስተዳደግ እንዲኖረው በማድረግ ወይም ወደ ሕክምና ወይም ወደ ጠባይ ማረሚያ ተቋም በመላክ በሚደረግ የጥንቃቄ እርምጃ የህብረተሰቡን ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር ወንጀል አድራጊው ከችግሩ ተፈውሶ ወደ ሰላማዊ ኑሮ የሚመለስበት ዕድል የሚፈጠርበት ሁኔታ እንዲኖር ጠቀሜታ አለው፡፡

ሕብረተሰብ በሚጥላቸው ቅጣቶች ሊያስተላልፍ የሚሞክረው ማንኛውም መልዕክት በትክክል ከወንጀለኛው ሊደርስ የሚችለው ወንጀለኛው አስተዋይ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በአንድ ሰው ላይ የሚፈፀመው ቅጣት ሊያስተውል የሚችለውን ያህል መሆን አለበት፤ የሚሰራውን ለማወቅ የማይችል ወይም የፈፀመው ተግባር ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ለመረዳት የማይችል ሰው የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወሰኑበት ቢችልም ቅጣት ግን ሊፈፀምበት አይገባም፡፡ ስለዚህም በአዕምሮ መቃወስ ምክንያት ፍፁም ኃላፊነት የሌለባቸው ወንጀል አድራጊዎች በቀጣይ ሌላ ወንጀል እንዳይፈፅሙ የጥንቃቄ እርምጃዎች ይወሰኑባቸዋል እንጅ ቅጣት ሊጣልባቸው አይችልም፡፡ በመቀጠል በወንጀል ሕጋችን ውስጥ የተካተቱ አንዳንድ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በአጭሩ እንቃኛለን፡፡

የመልካም ጠባይ ዋስትና –

አንድ ወንጀለኛ ድጋሚ ወንጀል ለመስራት ማሰቡን ካሳወቀ ወይም አዲስ ወንጀል ይሰራል የሚል እርግጠኛ የሆነ ሥጋት ካለ ወንጀለኛው በመልካም ጠባይ የሚመራ ስለመሆኑ የማረጋገጫ ቃል እንዲገባና ቃሉ የሚጠበቅ ስለመሆኑም በቂ የሆነ ዋስትና እንዲሰጥ ፍርድ ቤት ሊያስገድድው ይገባል፡፡ ወንጀለኛው ዋስትናውን የሚሰጠው እንደነገሩ ሁኔታ ንብረት በማስያዝ፣ በሰው ዋስትና ወይም በራሱ ዋስትና ሊሆን ይችላል፡፡

በዚህ መሰረት የመልካም ጠባይ ዋስትና እንዲያቀርቡ በፍርድ ቤት ሊገደዱ የሚችሉት ከአሁን በፊት ወንጀል ሰርተው ለዚህም ጥፋተኛ ሆነው የተገኙና በቀጣይም ሌላ ወንጀል የመፈፀም ሀሳብ ያላቸው ስለመሆኑ በይፋ የገለፁ ወይም አዲስ ወንጀል እንደሚፈፅሙ በእርግጥ የሚያሰጉ ሰዎች ናቸው እንጅ ማናቸውም ወንጀል ሊፈፅም ይችላል ተብሎ የሚታሰብ ወይም ወንጀል የሚፈፅም ስለመሆኑ ያሳወቀ ሰው ለመልካም ጠባይ አመራር ማረጋገጫ ዋስትና እንዲያቀርብ ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ሆኖም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 141 ላይ እንደተደነገገው ማንም ሰው ከመከሰሱ በፊት ወይም ጉዳዩ በፍርድ ቤት በሚታይበት ጊዜ ገና ሳይፈረድበት በጋራ ወይም በግል ፀጥታ ላይ አደጋ ለማድረስ ዝቶ ከተገኘ የመልካም ጠባይ ማረጋገጫ ዋስትና እንዲሰጥ በፍርድ ቤት ሊገደድ ይችላል፡፡

በመልካም ጠባይ ለመመራት የሚሰጥ ዋስትና የሚቆይበት ጊዜና የዋስትናው መጠን በፍርድ ቤት የሚወሰነው የዛቻውን ዓይነት፣ ከባድነትና አደገኛነቱን እንዲሁም የወንጀለኛውንና የዋሶቹን የግል ኑሮ ደረጃና የሀብት ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገበት መሆን አለበት፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በማናቸውም ሁኔታ የዋስትና ማረጋገጫው የሚቆይበት ጊዜ ከአንድ ዓመት ሊያንስ ወይም ከአምስት ዓመት ሊበልጥ አይችልም፡፡[1]

አደገኛ የሆኑ ነገሮችን መውረስ –

ለወደፊት ወንጀል ለመስራት ሊያገለግሉ የሚችሉ ወይም ወንጀል ለመፈፀም ተግባር የዋሉ ነገሮች ወይም የአንድ ወንጀል ተግባር ፍሬ የሆኑ ማናቸውም ነገሮች የሕዝብን ሰላማዊ ኑሮ፣ ሥርዓት፣ ጤና ወይም መልካም ጠባይ ሊጎዱ የሚችሉ ከሆኑ ፍርድ ቤት ንብረቶቹ በመንግሥት እንዲወረሱ ማዘዝ ይኖርበታል፡፡

እንዲሁም ማንም ሰው ሊከሰስ ወይም ሊፈረድበት ባይችልም እንኳ በእጁ የተገኘ አደገኛ ነገር ሁሉ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ በመንግሥት እንዲወረስ ፍርድ ቤቱ ሊያዝ ይችላል፡፡[2]

የግል ነጻነትን መገደብ –

ለአንድ ወንጀል መፈፀም መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉት ምክንያቶች አንዱ ከወንጀለኛው የግል ባህሪ አንጻር በተወሰኑ ቦታዎች መገኘት ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም አንድ ወንጀለኛ ወደ ተወሰኑ ቦታዎች በነጻነት ቢሄድ ወይም ቢመላለስ ሌላ አዲስ ወንጀል ይፈፅማል ተብሎ ከተገመተ ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት ድረስ ከነዚህ ስፍራዎች እንዳይደርስ ሊከለከል ይችላል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 145(2))፡፡

       እንዲሁም በአንድ በሆነ ስፍራ ባይኖር ወይም በአንድ በተወሰነ ሥፍራ ብቻ ቢኖር ወይም መደበኛ ሥራውን እየሰራ በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ ወይም በተጠራ ቁጥር በአንድ ባለስልጣን ፊት እየቀረበ ሪፖርት ቢያደርግ፣ ለወንጀለኛው በሚመለከታቸው አካላት ተሰጥተው የነበሩ ወረቀቶች ወይም የፓስፖርት ሰነዶችን ለጊዜው ቢያዙ (ቢነጠቅ) ወይም ከአገር እንዲወጣ ቢደረግ ወደፊት ወንጀል ሊሰራ የሚችልባቸውን አጋጣሚዎች መቀነስ ወይም ማስቀረት ይቻላል ተብሎ በፍርድ ቤቱ ዘንድ ከተገመተ እንደ ነገሩ ሁኔታ ከነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎች አንዱን ወይም ሁለቱን ፍርድ ቤቱ በጥፋተኛው ላይ ሊወስን ይችላል፡፡

       አንድ ወንጀለኛ በእንድ በተወሰነ ከተማ፣ መንደር፣ ወይም በአንድ የተወሰነ አካባቢ እንዳይኖር ወይም ውሎ እንዳያድር በፍርድ ቤት የሚወሰን የክልከላ የጥንቃቄ እርምጃ በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት ለዘወትር ማለትም እስከ ወንጀለኛው ዕድሜ መጨረሻ ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ተደንግጎ ነበር፡፡ በአዲሱ የወንጀል ሕግ መሰረት ግን እንዲህ ዓይነት የእገዳ ውሳኔ ሊቆይ የሚችለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንጅ ለዘወትር (ለዕድሜ ልክ) ሊሆን አይችልም፡፡ ድንጋጌው እንዲሻሻል በምክንያት የተነሳው እንዲህ ዓይነት ለዘወትር የሚጣል ክልከላ በተከለከለው ወንጀለኛ ነጻነት እና ለመታረም ባለው ዕድል ላይ ከባድ ችግር ያስከትላል የሚል ነው፡፡[3] በዚህም መሰረት በእንድ በተወሰነ ቦታ እንዳይኖር ወይም ውሎ እንዳያድር በወንጀለኛው ላይ የሚጣለው የእገዳ ትእዛዝ ከአንድ ዓመት እስከ አስር ዓመት ድረስ ብቻ ሊቆይ እንደሚችል ተደንግጓል(የወንጀል ሕግ አንቀጽ 146(2))፡፡

የሥራ እንቅስቃሴን መገደብ –

የሕግ ሰውነት ያላቸውን ድርጅቶች ጨምሮ ማናቸውም ሰው ልዩ ልዩ ሥራዎችን ለማካሄድ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተሰጠውን ፍቃድ በመጠቀም በሚያከናውነው ስራ ከፍ ያለ አደጋ የሚያደርስ ወይም የተደጋጋመ ከባድ ወንጀል የሰራ እንደሆነ ለፈፀመው ወንጀል ከሚጣልበት ቅጣት ጋር ተጨማሪ በማድረግ ሥራውን ለመካሄድ የተሰጠው ፈቃድ እንደሁኔታው ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ሊያዝበት (ሊታገድበት) ይችላል፡፡ የተፈፀመው ወንጀል ብዙ ጊዜ የተደጋገመ ወይም በተለይ ከባድ ከሆነ ደግሞ የተሰጠው ፈቃድ እስከ መጨረሻው ሊወሰድበት ይችላል፡፡

አንድ የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ወንጀል ለመፈፀም ወይም የወንጀል ዓላማን ለማራመድ ጥቅም ላይ የዋለ እንደሆነና ወንጀሉም በሕዝብ ፀጥታ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ድርጅቱ ሥራ እንዲያቆምና እንዲዘጋ ፍርድ ቤቱ መወሰን ይችላል፡፡ እንዲሁም በሕግ ሰውነት ባለው ድርጅት አማካኝነት የተፈፀመው ወንጀል ከአንድ ዓመት በበለጠ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ዓይነት ከሆነ ድርጅቱ እንዲፈርስና ንብረቱም እንዲጣራ ፍርድ ቤቱ ማዘዝ ይችላል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 143)፡፡

የፅኑ ግዞት/internment/- ፅኑ ግዞትበእስራት ቅጣት ሥር ሊመደብ የሚችል ቢሆንም ለየት የሚያደርገው የራሱ የሆነ ባህሪ አለው፡፡ ይኸውም እስራቱ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ ልዩ የግዞት ቦታ የሚፈፀም መሆኑ ነው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 129 ላይ እንደተመለከተው ይህ የግዞት ቦታ ጥብቅ ቁጥጥር ያለበትና እስረኞችም የጉልበት ስራ እንዲሰሩ የሚገደዱበት ቦታ ነው፡፡ የፅኑ ግዞት በአንድ ወንጀለኛ ሊወሰን የሚችለው ወንጀለኛው ከዚህ በፊት ወንጀል ፈፅሞ የተጣለበትን የእስራት ቅጣት አጠናቆ ከወጣ በኋላ አስቦ ሌላ አዲስ ወንጀል ከፈፀመና የወንጀል አፈጻፀሙ የወንጀል አድራጊውን አደገኛነት የሚያመለክት ከሆነ ወይም ወንጀለኛው ልማደኛ ደጋጋሚ ወንጀለኛ ከሆነ ነው፡፡

ምንም እንኳን የፅኑ ግዞት በወንጀለኛ መቅጫ ሕጋችን ውስጥ እንደ አንድ የጥንቃቄ እርምጃ ተመልክቶ የነበረ ቢሆንም አዲሱ የወንጀል ሕጋችን ግን ይህን የጥንቃቄ እርምጃ አስመልክቶ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ከቁጥር 128-132 ተመልክተው የነበሩትን ድንጋጌዎች ሰርዟቸዋል፡፡ለመሰረዙ ምክንያቶች ተብለው የተጠቀሱት ጉዳዮችም የፅኑ ግዞት ውሣኔ በፍርድቤቶች ተግባራዊ ሆነው የሚያውቅ ባለመሆናቸው፣ ፅኑ ግዞት የሚፈፀምበት ቦታና ሁኔታ በኢትዮጵያ ተመቻችቶ ስለማያውቅና በቅርብ ጊዜም ይህን ለማመቻቸት ይቻላል ተብሎ ስላልተገመተ እና በስዊዘርላንድና በስዊድን አገሮች ከሚሠራበት በቀር በሌሎች አገሮች የማይታወቅ የጥንቃቄ እርምጃ ዓይነት በመሆኑ ምክንያት ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡[4]


[1] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 135

[2] የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 141

[3] የወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት፣መስከረም 1998፣ገጽ 82(ያልታተመ)

[4] የወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት፣መስከረም 1998፣ገጽ 74(ያልታተመ)

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Table of Contents