Site icon Ethiopian Legal Brief

ደጋጋሚነት (recidivism) እና የቅጣት አወሳሰን

ደጋጋሚነት (recidivism) እና የቅጣት አወሳሰን

3.1.1. ደጋጋሚነት በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ

አንድ ሰው ቀደም ሲል ወንጀል መፈፀሙ ወይም ከዚሁ የተነሳ መቀጣቱ ብቻ ደጋጋሚ ወንጀለኛ አያሰኘውም፡፡ አንድ ሰው ደጋጋሚ ወንጀለኛ ነው ማለትና በተደጋጋሚ ወንጀል የፈፀመ ነው ማለት የሚያስከትለው ውጤት የተለያዬ ነው፡፡ ደጋጋሚ ወንጀለኛት ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በተደጋጋሚ የተቀጣ መሆን ወይም የወንጀል ሪኮርድ ያለው መሆን ግን ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በዚህም መሰረት አንድ ሰው በተደጋጋሚ ወንጀል የፈፀመ በመሆኑ ምክንያት ቅጣቱ የሚከብድበት ቢሆንም በመጨረሻ ለፈፀመው ወንጀል በሕጉ ልዩ ክፍል ከተመለከተው ቅጣት ጣራ በማለፍ ቅጣት ሊጣልበት አይችልም፡፡ ሆኖም ደጋጋሚ ወንጀለኛ ሆኖ ከተገኘ ግን በሕጉ ልዩ ክፍል ጥፋተኛ ለተባለበት ወንጀል ከተደነገገው ጣራ በላይ ቅጣት ሊወሰንበት ይችላል፡፡ አንድን ሰው ደጋጋሚ ወንጀለኛ ነው ለማለት በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉም ሆነ በአዲሱ የወንጀል የተቀመጡ መሟላት ያለባቸው መመዘኛዎች አሉ፡፡

ከወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 82(1)(ለ) ድንጋጌ ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው ደጋጋሚ ወንጀለኛ ለማለት የመጀመሪያው መመዘኛ በወንጀለኛው ላይ ከዚህ ቀደም የወንጀል ክስ ቀርቦበት ቅጣት የተወሰነበት መሆን አለበት፡፡ አዲሱን ወንጀል በፈፀመበት ወቅት ቀደም ሲል ፈፅሞት በነበረው የወንጀል ድርጊት ምክንያት የወንጀል ክስ ያልቀረበበት ወይም ክስ ቢቀርብበትም ገና በጉዳዩ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔና ቅጣት ያልተጣለበት ከሆነ የደጋጋሚ ወንጀለኛነት መስፈርት አልተሟላም ማለት ነው፡፡ አዲሱ የወንጀል ሕግ በዚህ የመጀመሪያ መስፈርት ላይ ያደረገው ለውጥ ወንጀለኛው ከዚህ ቀደም ጥፋተኛ በተባለት ወንጀል የተቀጣው በእስራት መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ሰው በመጀመሪያው ወንጀል የተፈረደበት የገንዘብ መቀጮ፣ የግዴታ ሥራ ወይም ወቀሳና ማስጠንቀቂያ ከሆነ ለደጋጋሚነት ማሟያ ነጥብ አይሆንም ማለት ነው፡፡

አንድን ሰው ደጋጋሚ ወንጀለኛ ለማለት ሁለተኛው መመዘኛ ወንጀለኛው ከዚህ ቀደም የተወሰነበትን ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ከፈፀመበት፤ ወይም በምህረት ወይም በአዋጅ ምህረት ቅጣቱ ከቀረለት ጊዜ ጀምሮ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሌላ ወንጀል የፈፀመ መሆን አለበት፡፡ አዲሱ የወንጀል ሕግ በዚህ መመዘኛ ላይም አንዳንድ ለውጦችን አድርጓል፡፡ ይኸውም በመጀመሪያው መስፈርት ላይ እንደተገለፀው ከዚህ ቀደም የተቀጣበት ወንጀል በእስራት የሚያስቀጣ መሆን ያለበት በመሆኑ ማንኛውንም ቅጣት ሳይሆን ይህን የእስራት ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ከፈፀመበት፣ ወይም ቅጣቱ በይቅርታ ከቀረለት ጊዜ ጀምሮ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሌላ ወንጀል የፈፀመ መሆን አለበት (አንቀጽ 67)፡፡ እዚህ ላይ ከእንግሊዝኛው አገላለፅ ጋር እንዲስማማ ተብሎ በአዲሱ የወንጀል ሕግ በቀድሞው ሕግ “ምህረት” በሚል ተመልክቶ የነበረው ”ይቅርታ” በሚል የተተካ ሲሆን “የአዋጅ ምህረት”  የሚለው ደግሞ “ምህረት” ተብሎ መመልከቱ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ስለሆነም በቀድሞው ሕግ መሠረት አንድ ሰው የአዋጅ ምህረት (ምህረት ለማለት ነው) በተሰጠው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ አዲስ ወንጀል ቢፈፅም ለደጋጋሚነት ማሟያ  ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በአዲሱ ሕግ መሠረት ግን ምህረት የተደረገለት ሰው አዲስ ወንጀል ቢፈፅም ምህረት ያገኘበት ከዚህ ቀደም የፈፀመው ወንጀል ለደጋጋሚነት ማሟያ ነጥብ አይሆንም ማለት ነው፡፡   

ሦስተኛው የደጋጋሚ ወንጀለኛነት መመዘኛ ወንጀለኛው አዲሱን ወንጀል የፈፀመው አስቦ/intentionally/ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ በዚህ መሰረት በቸልተኝነት የተፈፀመ ወንጀል ደጋጋሚ ወንጀለኛ አያሰኝም፡፡ በዚህ የደጋጋሚ ወንጀለኛነት መስፈርት ዙሪያ የቀድሞውም ሆነ አዲሱ የወንጀል ሕግ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ደጋጋሚ ለመባል ወንጀለኛውን ከዚህ ቀደም ያስቀጣውና አዲስ የተፈፀመው ወንጀል የግድ ተመሳሳይ መሆን የማይኖርባቸው መሆኑ ነው፤ ማለትም መስፈርቶቹ እስከተሟሉ ድረስ የወንጀሎቹ ዓይነት ቢለያይም የሚያከስትለው ለውጥ የለም፡፡

አንድን ሰው ደጋጋሚ ወንጀለኛ ለማለት አራተኛውና የመጨረሻው መመዘኛ ወንጀለኛው የፈፀመው አዲስ ወንጀል “እጅን አሳልፎ ለመስጠት የሚያበቃ” ዓይነት ወንጀል መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ይህ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 82(1)(ለ) ድንጋጌ ላይ ሰፍሮ የነበረው መስፈርት ሲሆን በአዲሱ የወንጀል ሕግ መሰረት ግን ወንጀለኛው ደጋጋሚ ወንጀለኛ ነው የሚባለው አዲስ የፈፀመው ወንጀል ቢያንስ እስከ ስድስት ወር ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል የሆነ እንደሆነ ነው በማለት በቀድሞው ሕግ የነበረውን መመዘኛ ለውጦታል፡፡

3.1.2. በደጋጋሚ ወንጀለኞች ላይ የሚኖረው የቅጣት አወሳሰን

     ደጋጋሚ ወንጀለኛ የሆነ ሰው ከቀድሞ ቅጣቱ ትምህርት ያላገኘ ነው ተብሎ ስለሚገመት ይህ ሁኔታ በወንጀለኛው ላይ የሚጣለው ቅጣት ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ በወንጀለኛው የተፈፀመው አዲስ ወንጀል ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት በህጉ ላይ በተደነገጉት የደጋጋሚነት መስፈርቶች መሰረት ደጋጋሚ ወንጀለኛ ነው የሚያሰኘው ከሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ቁጥር 193(1) መሰረት ፍርድ ቤቱ ለአዲሱ ወንጀል በሕጉ ልዩ ክፍል ወንጀለኛው ጥፋተኛ በተባለበት ድንጋጌ የቅጣት ጣራ ሳይገታ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ጠቅላላ ክፍል ለቅጣቱ ዓይነት እስካሰፈረው ከፍተኛ ቅጣት ድረስ ሊወስን ይችላል፡፡

     በዚህም መሠረት ወንጀለኛው አዲስ የፈፀመው ወንጀል በገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ ከሆነ ጥፋተኛ በተባለበት የወንጀል ድንጋጌ ላይ ባይመለከትም በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ቁጥር 88 ላይ እስከተደነገገው ጣራ ብር አምስት ሺህ ብር ድረስ፣ አዲስ የፈፀመው ወንጀል በቀላል እስራት የሚያስቀጣ ከሆነ በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ቁጥር 105 ላይ እስከተደነገገው ጣራ ሦስት ዓመት ቀላል እስራት ድረስ፣ አዲስ የፈፀመው ወንጀል በፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ከሆነ በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ቁጥር 107 ላይ እስከተደነገገው ጣራ ሀያ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት ድረስ ፍርድ ቤቱ በጥፋተኛው ላይ ቅጣቱን አክብዶ መወሰን ይችላል ማለት ነው፡፡

 እንዲሁም ወንጀለኛው ደጋጋሚና ቅጣት የማይመልሰው ሲሆን ጥፋተኛውን ወደ ፅኑ ግዞት እንዲላክ ፍርድ ቤቱ በቁጥር 128 ድንጋጌ መሠረት እንዲወስን የቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 193(2) ላይ ይደነግግ ነበር፡፡ በእርግጥ ስለ ጥንቃቄ እርምጃዎች በሚገልፀው የዚህ ጽሑፍ ክፍል እንደተመለከተው ፅኑ ግዞት የሚፈፀምበት ቦታና ሁኔታ በኢትዮጵያ ተመቻችቶ የማያውቅ ከመሆኑም ባሻገር የፅኑ ግዞት ውሣኔ በፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ሆኖ የሚያውቅ አይደለም፡፡

 በአዲሱ የወንጀል ሕግ መሠረት በደጋጋሚ ወንጀለኛ ላይ የሚጣለው ቅጣት አወሳሰን የተወሰኑ ለውጦች ተደርገውበታል፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 188(1) ላይ እንደተደነገገው አዲስ የፈፀመው ወንጀል ወንጀለኛውን ስለ ደጋጋሚነት በተቀመጡት መስፈርቶች መሰረት ደጋጋሚ ወንጀለኛ ነው የሚያሰኘው ከሆነ በመርህ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ለአዲሱ ወንጀል በሕጉ ልዩ ክፍል ወንጀለኛው ጥፋተኛ የተባለበት ድንጋጌ የቅጣት ጣራ እጥፍ እስኪሆን ድረስ ቅጣቱን አክብዶ መወሰን ይችላል፡፡ በመሆኑም እንደ ወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ሁሉ ወንጀለኛው ጥፋተኛ የተባለበትን የሕጉ ልዩ ክፍል ድንጋጌ የቅጣት ጣራ አልፎ ፍርድ ቤቱ መወሰን ይችላል፡፡ ነገር ግን ቅጣቱን ሊያከብድ የሚችለው ጥፋተኛ ለተባለበት ወንጀል ከተመለከተው የቅጣት ጣራ እጥፍ እስኪሆን ድረስ እንጅ በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ለቅጣቱ ዓይነት እስከሰፈረው ከፍተኛ ቅጣት ድረስ ሊወስን አይችልም፡፡ ከዚህ አኳያ ወንጀለኛው አዲስ የፈፀመው ወንጀል እስከ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት ሚያስቀጣ ቢሆንና ወንጀለኛው ደጋጋሚ ቢሆን በአዲሱ የወንጀል ሕግ መሠረት በመርህ ደረጃ ቅጣቱ ሊከብድበት የሚችለው ጥፋተኛ ለተባለበት አዲስ ወንጀል እስከተመለከተው የቅጣት ጣራ አጠፌታ ማለትም እስከ አስር ዓመት ድረስ ነው፡፡ በቀድመው ሕግ መሠረት ግን ለእስራቱ ዓይነት ማለትም ለፅኑ እስራት በሕጉ ጠቅላላ ክፍል እስከተመለከተው ከፍተኛ ቅጣት (ሀያ አምስት ዓመት) ድረስ ሊወስን ይችል ነበር፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሰው በአዲሱ የወንጀል ሕግ የተካተተው ለደጋጋሚ ወንጀለኛ በመርህ ደረጃ የሚኖረው የቅጣት አወሳሰን ዘዴ ነው፡፡ የተደጋገሙት ወንጀሎች ቁጥር ብዛት ያላቸው ከሆነ እንዲሁም የወንጀለኛው የአጥፊነት ደረጃና የድርጊቱ አደገኛነት ከባድ ከሆነ ከወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ለአዲሱ ወንጀል በሕጉ ልዩ ክፍል ወንጀለኛው ጥፋተኛ በተባለበት ድንጋጌ ላይ የተጠቀሰውን የቅጣት ጣራ በማለፍ በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል ለቅጣቱ ዓይነት እስከሰፈረው ከፍተኛ ቅጣት ድረስ ሊወስን ይችላል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 188(2))፡፡ እንዲሁም ወንጀለኛው ልማደኛ ደጋጋሚ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ለመጨረሻው አዲስ ወንጀል የሚጥለው ቅጣት በሕጉ ልዩ ክፍል ወንጀለኛው ጥፋተኛ በተባለበት ድንጋጌ ላይ ከተጠቀሰውን ቅጣት ጣራ የግድ በማለፍ መሆን ያለበት ስለመሆኑ በፍርድ ቤቱ ላይ አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ በዚሁ ንዑስ አንቀጽ ላይ ተደንግጓል፡፡

    እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ በየትኛውም ዘዴ ቢሆን ሕጉ በሚያዘው መሰረት በደጋጋሚ ወንጀለኛው ላይ ቅጣቱ እንዲከብድበት ሲደረግ በምንም ዓይነት ጥፋተኛው አዲስ ለፈፀመው ወንጀል በሕጉ ልዩ ክፍል ከተመለከተው ቅጣት አንጻር በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ለቅጣት ዓይነቱ ከተደነገገው ጣራ ቅጣት በማለፍ ፍርድ ቤቱ ቅጣት ሊጥል የማይችል መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ጥፋተኛ ለተባለበት አዲስ ወንጀል እስከተመለከተው የቅጣት ጣራ አጠፌታ ድረስ ፍርድ ቤቱ በጥፋተኛው ላይ ቅጣቱን ሊያከብድበት የሚችል ቢሆንም በሕጉ ልዩ ክፍል ለወንጀሉ የተቀመጠውን ቅጣት አጠፌታ ሲያደርግ በሕጉ ጠቅላላ ክፍል ለቅጣቱ ዓይነት የተመለከተውን ገደብ የሚያልፍ ከሆነ ቅጣቱን በመቀነስ የጠቅላላ ክፍሉን ጣራ ቅጣት በወንጀለኛው ላይ ተፈጻሚ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

Exit mobile version