Search Knowledge Base

< Back
You are here:
Print

ሰ/መ/ቁ 38189 የሥራ መደብ ዝውውር

የሠ.መ.ቁ 38189

ግንቦት 27 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

        ታፈሠ ይርጋ

        ፀጋይ አስማማው

        በላቸው አንሺሶ

        አልማው ወሌ

አመልካች፡- ሮፓክ ኢንተርናሽናል ኃላ.የተ.የግል ማህበር – ጠበቃ ያለለት ተሾመ ቀረበ

ተጠሪ፡- ይደርሣል አእምሮ – ቀረቡ፡፡

       መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

       ጉዳዩ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅን መሠረት ያደረገ ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ህዳር 08 ቀን 1999 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ ከሚያዝያ 15 ቀን 1993 ዓ.ም ጀምሮ በወር ብር 1200.00 ደመወዝ እየተከፈላቸው በአመልካች መ/ቤት በዕቃ ግምጃ ቤትነት እስከ 03/13/98 ዓ.ም ድረስ መስራታቸውን ሆኖም ከዚሁ ከተቀጠሩበት የስራ መደብ አመልካች መ/ቤት አንስቷቸው በወር ብር 650.00 በሚከፈልበት የሠዓት ተቆጣጣሪነት የስራ መደብ አዛውሯቸው ቅሬታ ቢያሰሙም ተገቢው ምላሽ በወቅቱ አመልካች ሣይሠጣቸው መቅረቱንና ከስራ ያሠናበታቸው ያላግባብ መሆኑን ዘርዝረው የካሣ፣ የአምስት ዓመት አገልግሎት፣ የዓመት ፈቃድ፣ የህዝብ በዓላት የ14 ቀናት ክፍያ፣ ለዘገየበት ክፍያ እንዲከፍልና የስራ ምስክር ወረቀት እንዲሠጣቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀው በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመሠረቱት ክስ መነሻ ነው፡፡ አመልካች በተከሣሽነቱ ቀርቦም ተጠሪ የተሠናበቱት ከ22/12/1998 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 04/13/1998 ዓ.ም ድረስ በስራ ቦታቸው ላይ ስላልተገኙ መሆኑን ገልፆ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡ የስር ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን ማስረጃዎችን ከሠማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ ከተቀጠሩበት የስራ መደብ ወደ ሌላ ተዛውረው ቅሬታ እያሠሙ ባሉበት ሁኔታ በስራ ቦታቸው አልተገኙም ማለት ተገቢነት የሌለው ነው የሚለውን ነጥብ በምክንያትነት ይዞ የአመልካችን እርምጃ ከህግ ውጪ ነው በማለት የተለያዩ ክፍያዎች ለተጠሪ እንዲከፈሉ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 337 መሠረት ሠርዞታል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ የበታች ፍ/ቤቶችን ውሣኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡

       የአመልካች ጠበቃ ግንቦት 29 ቀን 2000 ዓ.ም በፃፉት 2/ሁለት/ ገፅ የሠበር አቤቱታ በበታች ፍ/ቤቶች ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ የስር ፍ/ቤቶች ተጠሪ ከስራ ገበታቸው ከ10 ቀናት በላይ ስለመቅረታቸው ተረጋግጦ እያለ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1/ለ) ስር ከተመለከተው ውጪ በተሣሣተ ትርጉም ተጠሪ ከስራ የቀሩት በበቂ ምክንያት ነው ማለታቸው ሊታረም ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሣይ ነው፡፡ የአመልካች የሠበር አቤቱታ ተመርምሮም በሠበር ችሎቱ ሊታይ ይገባዋል በመባሉ ተጠሪ ቀርበው መልሣቸውን መስከረም 27 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ማመልከቻ ሠጥተዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ወደተዛወሩበት የስራ መደብ ያልተገኙት የአመልካች ዘበኞች ያረጋገጡት ፍሬ ጉዳይ መሆኑንና የበታች ፍ/ቤቶች ውሣኔም የትርጉም ስህተት ያልተፈፀመበት መሆኑን ዘርዝረው ሊፀና ይገባል በማለት መከራከራቸውን የሚያሣይ ነው፡፡ የአመልካች ጠበቃ በበኩላቸው ህዳር 04 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት የመልስ ማመልከቻ ተጠሪ ወደ አመልካች ግቢ ለመግባት በዘበኛ ተከልክያለሁ የሚሉት ክርክር አዲስ መሆኑን ገልፀው የሠበር አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

       የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን የፁሑፍ ክርክር የሠበር አቤቱታው ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም ተጠሪ የተመደብኩበት የስራ መደብ ካለሙያ ነው በማለት ከስራ ገበታው ላይ ለ10 ተከታታይ ቀናት በላይ በመቅረቱ አመልካች ከስራ ሲያሰናብተው የስራ ውሉ የተቋረጠው ያለበቂ ምክንያት ነው ተብሎ የአመልካች እርምጃ ህገ ወጥ ነው ሲባል መወሠኑ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል፡፡

       ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች የተጠሪን የስራ ውል ያቋረጠው ተጠሪ በተዛወሩበት የስራ መደብ ሣያገኙ ከ10/አስር/ ተከታታይ የስራ ቀናት በላይ መቅረታቸውን መሠረት በማድረግ መሆኑንና ተጠሪ በበኩላቸው የሚከራከሩት በተዛወሩበት የስራ መደብ ያልተገኙት የአመልካች ዘበኞች ግቢ እንዳይገቡ ስለከለከሏቸው እና የስራ መደብ ዝውውሩን በመቃወም ቅሬታ አሰምተው ውጤቱን እየተጠባበቁ ስለነበር መሆኑን በመግለፅ ነው፡፡

       እንግዲህ አመልካች ተጠሪን ከተቀጠሩበት የስራ መደብ ወደ ሌላ የስራ መደብ በማዛወር ተጠሪ ተገቢው ደብዳቤ ከተሠጣቸው በኋላ በተዛወሩበት የስራ መደብ ሣይገኙ ከ10/አስር/ ተከታታይ ቀናት በላይ የቀሩት በአመልካች ጥበቃ ክልከላ ስለመሆኑ በመጥቀስ ይኸው ተግባር በቂ ምክንያት ነው ሲሉ ተጠሪ የሚከራከሩ ሲሆን የአመልካች ጠበቃ ይህንኑ የክርክር ነጥብ በስር ያልተነሣ ስለመሆኑ ጠቅሰው የመልስ መልስ ሠጥተዋል፡፡ ይህ ችሎትም የስር ፍ/ቤትን ዋና መዝገብ በማስቀረብ ጉዳዩን ሲያጣራው በስር ፍ/ቤት ክሱ በተሠማበት ወቅት ተጠሪ ይህንኑ የክርክር ነጥብ አንስተው ምስክሮቻቸውም የሚያስረዱት ጭብጥ መሆኑን ገልፀው ምስክሮቻቸው መስማታቸውን አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የአመልካች ጠበቃ አዲስ ክርክር ነው በማለት ያቀረቡትን ክርክር አልተቀበልነውም፡፡

       በሌላ በኩል ተጠሪ ከላይ የተጠቀሠውን የክርክር ነጥብ በስር ፍ/ቤት ያነሡት ቢሆንም ጉዳዩን ለማስረዳት የተሠሙት ምስክሮች ግን የአመልካች ጠበቃ ተጠሪን ግቢ እንዳይገቡ የከለከሏቸው ስለመሆኑ የሠጡት የምስክርነት ቃል የለም፡፡ የስር ፍ/ቤትም ተጠሪ በስራ ቦታቸው ላይ ያልተገኙት በአመልካች ጥበቃ ክልከላ አለመሆኑን በመገንዘብ ተጠሪ በስራ መደቡ ለውጥ ምክንያት ቅሬታ እያሰሙ ባሉበት ሁኔታ በስራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም ሊባል አይገባም በማለት ነው፡፡ በመሆኑም ተጠሪ በተዛወሩበት የስራ መደብ ከአምስት ተከታታይ የስራ ቀናት በላይ ያልተገኙት በአመልካች ጥበቃ ክልከላ ምክንያት አለመሆኑን ስለተገነዘብን በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ክርክር ውድቅ አድርገናል፡፡

       የስር ፍ/ቤት ተጠሪ በስራ ላይ ያልተገኙት ዝውውሩን ተቃውመው ቅሬታ ሲያሠሙ በነበረበት ወቅት መሆኑን ጠቅሶ ተጠሪ ያለበቂ ምክንያት ከስራ ቀርተዋል ሊያስብላቸው አይችልም፡፡ ሲል የደረሠበትን ድምዳሜ ህጋዊነቱን ተመልክተናል፡፡

       በመሠረቱ በቂ ምክንያት ሣይኖረው በተከታታይ ለአምስት የስራ ቀናት በስራ ገበታው ያልተገኘ ሠራተኛን ማስጠንቀቂያ መስጠት ሣያስፈልግ የስራ ውሉን ለማቋረጥ ለአሠሪው ህጉ የሠጠው ስልጣን መሆኑን የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1/ለ) ድንጋጌ ያሣያል፡፡ ሠራተኛው የአሠሪውን እርምጃ ሊቃወመው የሚችለው በቂ ምክንያት ያለው ስለመሆኑ በማስረዳት ነው፡፡ በቂ ምክንያት የሚለው ሀረግ መመዘኛው ደግሞ ሠራተኛው ከስራ ቦታው ሊገኝ የማይችልበት ሁኔታ ስለመኖሩ ሊያመላክቱ የሚችሉ ምክንያቶች ስለመሆኑ ከአዋጁ አጠቃላይ ዓላማና ከተጠቃሹ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ለመገንዘብ የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ከስራ የቀረ ሠራተኛ በቂ ምክንያት ኑሮት ከስራው ቀርቷል ለማለት የሚቀርበው ማስረጃ ሠራተኛው በስራ ቦታው ለመገኘት የሚያስችል መሰናክል የነበረ መሆኑን የሚያስረዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም ሠራተኛው ባልተገባ ምክንያት ከስራው በመቅረት በምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡

       ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪ በስራ ገበታቸው ያልተገኙት ምክንያት የስራ መደብ ዝውውሩን በመቃወም ቅሬታ እያሰሙ በነበሩበት ወቅት ስለመሆኑ የስር ፍ/ቤት ገልጿል፡፡ ሆኖም የስራ መደብ ዝውውር መደረግና ሠራተኛው ቅሬታውን በማሠማት ላይ መሆኑ በስራ ቦታ ላለመገኘት እንደ በቂ ህጋዊነት ምክንያት የሚወሠድ አይደለም፡፡ የስራ መደብ ዝውውሩ ሠራተኛው በስራው ቦታ እንዳይገኝ መሠናክል የሚሆንበት ሁኔታ የለምና፡፡ ሠራተኛው በዝውውሩ ላይ ቅሬታ ካለውም ስራውን እየሠራ በህጉ በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት መብቱን ማስጠበቅ አለበት እንጂ ከስራው ሊቀር አይገባም፡፡ ስለሆነም የበታች ፍ/ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሠጡት ውሣኔ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሁኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም መሠረት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

  1. በፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ቁ 32745 ጥር 05 ቀን 2000 ዓ.ም ተሠጥቶ በፌ/ከ/ፍ/ቤት በመ/ቁ 62988 መጋቢት 01 ቀን 2000 ዓ.ም በትዕዛዝ የፀናው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡
  2. የአመልካች የስራ ውሉን ያቋረጠው በህጉ መሠረት ነው ብለናል፡፡
  3. ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Table of Contents